ፈልግ

የሞት ቅጣት ፍርድ የሞት ቅጣት ፍርድ  (Copyright © Ken Piorkowski 2012)

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፥ “ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ መትጋት አልቻላችሁምን?” አላቸው

በአሜሪካ የዎል ስትሪት የገንዘብ ተቋም ጠበቃ የነበሩት አቶ ዳሌ ሬሲኔላ ከባለቤቻቸው ወ/ሮ ሱዛን ጋር ሆነው ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቆይታን አድርገዋል። አቶ ሬሲኔላ ባሁኑ ወቅት በፍሎሪዳ ውስጥ በሚገኝ ወህኒ ቤት፣ ለታራሚዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማቅረብ ላይ ሲሆኑ፣ ከዜና አገልግሎቱ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በሞት ሰዓት መቃረብ ላይ ክርስቲያናዊ አመለካከት ምን እንደሚመስል አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሞት ቅጣት ፍርድን በማውገዝ የምታቀርበውን አስምህሮን መሠረት በማድረግ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ሬሲኔላ፣ የሞት ቅጣት ፍርድ የተበየነበት ወዳጃቸውን በማስታወስ እንደተናገሩት፣ የሞት ሰዓትን ከሕማማት ቀናት መካከል አንዱ ከሆነው ዓርብ ዕለት ጋር በማመሳሰል፣ ይህ ቀን  የኢየሱስ ክርስቶስን ሕማማት ለማስታወስ ቤተ ክርስቲያን በአምልኮ ሥርዓት የምትገልጸው እና በቅዱስ ወንጌል ውስጥም ተጽፎ የሚገኝ መሆኑን አስታውሰዋል።

ቅዱስ ማቴዎስ የጻፈውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እንመለከት ያሉት አቶሬሲኔላ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በነበረበት ጊዜ፣ ከመጨረሻው እራት በኋላ ለጸሎት ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ እንደሄደ እና ይሁዳ እንደከዳው እና እርሱን ለመግደል አሳልፈው የሚሰጡ ሰዎችን ለመጥራት መሄዱ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ተጽፎ እንደሚገኝ አስታውሰዋል።

“በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከእርሱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ሥፍራ ሄደ። ደቀ መዛሙርቱንም ወደዚያ ሄጄ እስክጸልይ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው። ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስን ልጆች ይዞ ሄደና ማዘንና መጨነቅ ጀመረ። ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝናለች፤ እዚህ ቆዩ፤ ከእኔም ጋር ትጉ”  (ማቴ. 26: 36-38)

በዕለተ ሞቱ ይታይ የነበረው ሐዘን እና ስለ እርሱ የሚጨነቁት ከእርሱ ጋር ሆነው እንዲጠብቁ የጠየቃቸው ያ ጊዜ የኢየሱስ ክርስቶስ የሞት ሰዓት እንደነበር አቶ ሬሲኔላ አስረድተዋል። የሞት ሰዓት አስጨናቂ እና ከባድ ቢሆንም የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርትን ለምን እንደወሰዳቸው ቅዱስ ማቴዎስ አለመግለጹን አስታውሰው፣ ምናልባት ብዙ ምግብ በልተው ስለደከማቸው ወይም ከተፈረደባቸው ሰዎች ጋር ከፍተኛ ብጥብጥ እና ጭንቀት ስላጋጠማቸው ሊሆን እንደሚችል ተናግረው፣ ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ የነበሩበትን ሁኔታ በማስመልከት የሰጠውን ምላሽ እንዳለ ተናግረዋል። “ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመጣ ጊዜ ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም አንዲህ አለው፥ ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ መትጋት አልቻላችሁምን?” (ማቴ. 26: 40-41)

ከዚያም ኢየሱስ እንደገና ሄዶ መጸለዩን እና ደቀ መዛሙርቱም እርሱ የጠየቃቸውን መፈጸም አለመቻላቸውን አቶ ሬሲኔላ በመናገር የሚከተለውን የወንጌል ክፍል ጠቅሰዋል። “ከዚህ በኋላ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥቶ እንዲህ አላቸው፥ ‘ከእንግዲህስ ተኙ፣ ዕረፉም፤ እነሆ ሰዓቱ ቀርቧል፤ የሰው ልጅ በኃጢ አተኞች እጅ ተላልፎ ይሰጣል” (ማቴ. 26: 45)  

የሉቃስ ወንጌል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በሞት ሰዓት የተሰማውን ስሜት እና የደረሰበትን አካላዊ ጉዳት በዝርዝር መዘገቡን አቶ ሬሲኔላ በመግለጽ የሚከተለውን የቅዱስ ወንጌል ክፍል ጠቅሰዋል። “በስቃይ ጣር ውስጥ ሆኖ በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ላቡም ወደ መሬት እንደሚንጠባጠቡ የደም ጠብታዎች ሆኑ። ከጸሎትም ተነስቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣና ከኅዘን የተነሳ ተኝተው ሲያገኛቸው ‘ለምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሱና ጸልዩ’ አላቸው።” (ሉቃ. 22: 44-46)

የደም ማላብ ሂደት በጭንቀት ወቅት እንደሚከሰት ይታመናል ያሉት አቶ ሬሲኔላ፣ ቆዳችን ደምን ወደ ላብ እጢዎች በመውሰድ በሥቃይ ውስጥ የሚገኝ ሰው ለሞት ሲቃረብ ከደም ጋር የተቀላቀለ ላብ እንደሚልበው ገልጸው፣ በሞት ሰዓት የኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይም ጥልቅ እንደ ነበር አስታውሰዋል። ቅዱስ ሉቃስ ሐኪም እንደመሆኑ የስሜት መቃወስ ምልክቶችን ጠንቅቆ እንደሚያውቅ እና የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትን እንቅልፍ የወሰዳቸው ለዚህ እንደነበር ተናግረው፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው፣ ከወንድሞቹ መካከል አንዱ በሞት አፋፍ ላይ ሲሆን፣ ልክ ደቀ መዛሙርቱ በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ እንደነበሩ፣ በሞት ሰዓትም ከኢየሱስ ጋር እንደነበሩ ግልጽ ነበር” ብለዋል።

“ጻድቃኑም እንዲህ ሲሉ ይመልሱለታል፥ ጌታ ሆይ መቼ ተርበህ አየንህና አበላንህ? መቼ ተጠምተህ አየንህና አጠጣንህ? መቼ እንግዳ ሆነህ አየንህና ተቀበልንህ? መቼ ታርዘህ አየንህና አለበስንህ? መቼ ታመህ ወይም ታስረህ አየንህና ጠየቅንህ? ንጉሡም እንዲህ ሲል ይመልስላቸዋል፥ እውነት እላችኋለሁ፤ ከሁሉ ለሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ያደረጋችሁት ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው።” (ማቴ. 25: 36-40)

28 January 2023, 16:33