ፈልግ

የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን አገራት ኅብረት ጠቅላይ ጸሐፊ አቶ ጄንስ ስቶልተንበርግ የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን አገራት ኅብረት ጠቅላይ ጸሐፊ አቶ ጄንስ ስቶልተንበርግ   (ANSA)

አቶሚክ መሣሪያን ለጦርነት መጠቀም ከፍተኛ ጉዳትን ሊያስከትል እንደሚችል ተነገረ

ማንኛውንም የኒውክሌር ጦር መሣሪያን መጠቀም ሩሲያ ላይ ከባድ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል፣ የሰሜን አታላንቲክ ቃል ኪዳን ሀገሮች ድርጅት “NATO” ጠቅላይ ጸሐፊ አቶ ጄንስ ስቶልተንበርግ በአንድ ቃለ መጠይቅ ገልጸው፣ የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን የኒውክሌር ጦር መሣርያን በማስመልከት ያደረጉት ንግግሮች "አደገኛ" እና "ግዴለሽነት" የታዩባቸው ናቸው ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን ወታደሮች በኬርሰን ክልል እና በሀገሪቱ ምስራቃዊ አካባቢዎች ድል እየቀናቸው መሆኑ ተነግሯል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሩሲያ ከዩክሬን በኃይል የወሰደቻቸውን ግዛቶች ደኅንነት ለማስጠበቅ በኒውክሌር የጦር መሣሪያዎች ለመደገፍ የምታደርገውን ሙከራ በማስመልከት፣ የሰሜን አታላንቲክ ቃል ኪዳን ሀገሮች ድርጅት “NATO” ጠቅላይ ጸሐፊ ክቡር አቶ ጄንስ ስቶልተንበርግ፣ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን አደገኛ ንግግሮች ከባድ መዘዞችን በማስከተል ጦርነቱን ወደ ሌላ አቅጣጫ ሊመራው እንደሚችል ተናግረዋል።  

የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን አገራት ኅብረት ጠቅላይ ጸሐፊ አቶ ጄንስ ስቶልተንበርግ የኒውክሌር ጦርነትን ማሸነፍ እንደማይችል እና መሣሪያውንም መጠቀም እንደማይገባ ገልጸው፣ የአትላንቲክ ቃል ኪዳን አገራት በመሠረተ ልማት አውታሮቹ ላይ ለሚሰነዘር ማንኛውም ዓይነት ጥቃት ጠንካራ የጋራ አጽፋ እንደሚወስዱ ግልፅ አድርገዋል። ጠቅላይ ጸሐፊው ከዚህም በተጨማሪ የዩክሬን የኔቶ አባልነት ጥያቄ በኅብረቱ አባል አገራት ዘንድ አዎንታዊ አስተያየት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዩክሬን ወደ ኔቶ ኅብረት ለመግባት ያቀረበችው ጥያቄ

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዘጠኝ የቀድሞ ኮሚኒስት አገራት ዩክሬን ወደ ሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን አገራት አባልነት እንድትገባ ድጋፋቸውን መግለጻቸው ታውቋል። የቀድሞ ኮሚኒስት አገራት የሚባሉት ቼክ ሪፐብሊክ፣ ኢስቶኒያ፣ ላትቪያ፣ ሊትዌኒያ፣ ሰሜን መቄዶኒያ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ፖላንድ፣ ሮማኒያ እና ስሎቫኪያ በጋራ በገለጹት ድጋፍ፡- ዩክሬንን ከሩሲያ ወረራ ለመከላከል ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸው፣ ሩሲያ በኃይል ከያዘቻቸው የዩክሬን ግዛቶች በሙሉ በአስቸኳይ እንድትወጣ ጠይቀዋል። አክለውም ሁሉም አጋር አገራት ለዩክሬን የሚያደርጉትን ወታደራዊ ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር እንደሚያግዟት አስታውቀዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት አቶ ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በበኩላቸው ለሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን አገራት አባልነት ያቀረቡት ጥያቄ በጎ ምላሽ እንደሚያገኝ እርግጠኛ ነኝ ብለዋል። የፕሬዝደንት ዜለንስኪ ብሩህ ተስፋ የሚመነጨው በደቡብ የአገሪቱ ክፍል በሚገኝ ኬርሰን አቅራቢያ ያሉ በርካታ ሠፈሮች እና በአገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል የላይማን ከተማን ከሩሲያ ጦር ኃይል መልሰው በእጃቸው በማስገባታቸው ሲሆን፣ ጀርመን ፣ ኖርዌይ እና ዴንማርክ አዲስ የጦር መሣሪያ ዕርዳታን ለኪየቭ መንግሥት መላካቸውን አስታውቀዋል።

በኃይል በተያዙት አካባቢዎች የግዳጅ ምዝገባዎችን ማካሄድ

የሩሲያ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ከዩክሬን በኃይል የተገነጠሉ ሪፐብሊኮችን ከሩሲያ ጋር መቀላቀልን ሕጋዊ የሚያደርግ ሲሆን፣ ከእነዚህ አዳዲስ ግዛቶች ወታደሮችን በግዳጅ መመልመሉን ዘገባዎች ጠቁመዋል።በዛፖሪዝዝሂያ ክልል ሩሲያ በኃይል በያዘቻት የሜሊቶፖል ከንቲባ እንደተናገሩት፣ ሰዎች ከከተማቸው ጎዳናዎች እየተለቀሙ ወደ አስተዳደር ቢሮ በመወሰድ በግድ እንዲመዘገቡ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

03 October 2022, 17:34