ፈልግ

ኑር-ሱልጣን፣ ር. ሊ. ጳጳሳትን እና ሌሎች የሃይማኖት መሪዎችን በክብር ለመቀበት መዘጋጀቱ ተገለጸ

የእምነቶች እና የባሕሎች ማዕከል የሆነች የካዛኪስታን መዲና ኑር-ሱልጣን የቀድሞ ሶቪዬት ኅብረት አባል አገራትን ጨምሮ ሌሎች የእስያ አገራት እርስ በእርስ የሚገናኙባት ዋና ከተማ ለመሆን ጥረት ላይ መሆኗ ታውቋል። በካዛኪስታን በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ የጋራ ውይይት ተጨባጭ የሕይወት ክፍል መሆኑን ብጹዕ አቡነ ፒዮትር ፒትሎዋኒ አስገንዝበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዘመናዊቷ የምትታወቅ የካዛኪስታን ዋና ከተማ ኑር-ሱልጣን ውስጥ ከተለያዩ የእስያ አገራት የመጡ እና ከቦታ ወደ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች በካቴድራሉ ዙሪያ በርከት ብለው የሚገኙባት ከተማ መሆኗ ታውቋል።  የምትገኝበትን አካባቢ የሚገልጹ የዘመናዊ ሕንፃዎች ንድፎች በስፋት የሚታዩባት ከተማ መሆኗ ታውቋል። ከተማዋ የቀድሞ የሶቪዬት ኅብረት እና የምዕራባውያን ተጽዕኖ ቅይጥ ያለባት ከተማ መሆኗ ተመልክቷል።

የቀድሞ ሶቪዬት ኅብረት ተጽዕኖ እና የወደፊት እድገት አቅጣጫ

በካዛኪስታን መዲና ኑር-ሱልጣን ውስጥ የሚካሄደውን የዓለም ሃይማኖቶች እና እምነቶች መሪዎች ጉባኤን ምክንያት በማድረግ በከተማዋ ጎዳናዎች የካዛኪስታን፣ የቅድስት መንበር እና የቻይና ሰንደቅ ዓላማዎች በስፋት ሲውለበለቡ ታይተዋል። ከከተማዋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ በመካከለኛው የእስያ አገራት ውስጥ ትልቁ እና ግንባታው በቅርቡ እስከ ተጠናቀቀው ሰማያዊው መስጊድ ድረስ ሰንደቅ ዓላማዎች ተሰቅለው ታይተዋል። ከዋና ከተማዋ ሃምሳ ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ የሚገኘው የቀድሞ ሶቪዬት ኅብረት የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ማረሚያ ቤት የአሳዛኝ ታሪክ መገለጫዎች መሆናቸው ታውቋል።  

በአገሪቱ ውስጥ ሁሉም ሰው በሚያስብል ደረጃ የራሽያ ቋንቋ የሚናገሩ ሲሆን፣ ካዛክ የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ነው ማለት እንደሚያዳግት ተገልጿል። የካዛኪስታን መዲና ኑር-ሱልጣን በኢሺም ወንዝ ለሁለት የተከፈለች ከተማ ስትሆን፣ የተቆረቆረችው እና ያደገችው በቀድሞው ፕሬዝዳንት ናዛርቤዬቭ ጥረት መሆኑ ታውቋል። አስታና የሚለውን ጥንታዊ መጠሪያ ስሟን ለመመለስ የሚደረገው ክርክር በስፋት የሚነገር መሆኑ ታውቋል።  

የከተማው ገጽታዎች

በዋና ከተማዋ ውስጥ የሚታዩ ሕንፃዎች በታዋቂ የሕንጻ ተቋራጮች፣ ከፎስተር እስከ ኩሮሳዋ ድረስ ባሉ የሥነ-ሕንጻ ባለሞያዎች የተገነቡ ሲሆኑ፣ 100 ሜትር ከፍታ ያለው እና የሕይወት ዛፍ በመባል የሚታወቀው የባይቴሬክ ግንብ እ. አ. አ. 2003 የመጀመሪያው የዓለም ሃይማኖቶች እና ባሕላዊ እምነቶች መሪዎች ጉባኤ የተካሄደበት ሥፍራ መሆኑ ይታወሳል።

ወርቃማው ሉል የቆመበት በካዛክ ኤሊ ዓምድ አናት ላይ ያለው የቅዱስ ወፍ ሐውልትም ለአገሪቱ ነፃነት እና ክብር እንዲሁም ለዘላቂ ልማት እና ዕድገት ያለውን ምኞት የሚገልጽ መሆኑ ታውቋል። በየቦታው የተገነቡት ሕንጻዎች ለሥነ-ጥበብ የተሰጠውን ከፍተኛ ሥፍራ የሚገልጹ ሲሆን፣ በከተማዋ ውስጥ የከፍተኛ ፈጠራ ውጤት የሆነው ትልቁ የሥነ-ጥበብ ማዕከል በሰማያዊ ቀለም የተዋበ እና የቀለበት ቅርጽ ያለው መሆኑ ተመልክቷል። በኑር-ሱልጣን ከተማ ውስጥ የሚገኘው እያንዳንዱ ሃይማኖታዊ ማኅበረሰብ እና ቤተሰብ የትናንሽ ቡድኖች ቅይጥ ሲሆን፣ በዚህ መሠረት ቀድሞ የሩሲያ ጦር ሠፈር የነበረው የኑር-ሱልጣን ከተማ ከዓመት ወደ ዓመት መልኩን በመለወጥ፣ ልዩ ተሰጥኦ ባላቸውን ዓለም አቀፍ የሥነ-ሕንጻ ባለሞያዎች ፈጠራን ከሚጠቀሙ አበዳሪ ድርጅቶች በሚገኘው ብድር በመተማመን ከተማዋን ወደ የት እንደሚወስዷት ገና ግልፅ አይደለም ተብሏል።

የእስያ ቤተ ክርስቲያን "ቡቃያነት"

ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በካዛኪስታን ለማካሄድ የሚመጡትን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለመቀበል የተደረገውን ዝግጅት ያስተባበሩት የመካከለኛው እስያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ፒዮትር ፒትሎዋኒ፣ በካዛኪስታን ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ የሃይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረግ የጋራ ውይይት ተጨባጭ እንደሆነ አስገንዝበዋል። የካዛኪስታን ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ የሆኑት ኢየሱሳዊ ካኅን ክቡር አባ አንቶኒ ጄምስ በበኩላቸው ከቅዱስነታቸው ጋር ለመገናኘት ባላቸው ከፍተኛ ፍላጎት ካቶሊካዊ ምዕመናንን ጨምሮ በጎረቤት አገራት የሚገኙ የልዩ ልዩ ሃይማኖት ተቋማት ምዕመናን ወደ ካዛኪስታን መዲና ኑር-ሱልጣን ከተማ ይዘው መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በእስያ ውስጥ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን በማደግ ላይ ያለች መሆኗን ክቡር አባ አንቶኒ ገልጸው፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ድጋፍ፣ ብርታት እና ማፅናኛ የሚያስፈልጋት መሆኑን ገልጸው፣ ከቅዱስነታቸው ጋር መገናኘት ትልቅ ዋጋ ያለው እና ሰላምን ለማሳደግ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል። የሃይማኖት ተቋማቱ ለጋራ ውይይት ያላቸውን ፍላጎት እንዲገልጹ፣ ለሌላው የእምነት ተቋም ያላቸውን አክብሮት በተግባር ማሳየት እንደሚገባ አሳስበዋል።

“የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የብርሃን ጊዜ የሚታይበት"

"ጦርነት ምን ጊዜም አሳዛኝ ነው" በማለት አስተያየታቸውን የገለጹት ክቡር አባ ኮርኮራን፣ ከሩስያ በኩል የተወሰኑ ካቶሊካዊ ነጋዲያን አስከትለው ወደ ካዛኪስታን ዋና ከተማ ኑር-ሱልጣን የመጡ ሲሆን፣ የምዕመናኖቻቸው ቁጥር ለጊዜው ጥቂት ቢሆኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ በቁጥር እያደጉ መሆናቸውን እና ነገር ግን የሚፈለገው የእውነተኛነት መንፈስ መጠበቅ እንደሆነ አስረድተዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት የተስፋ ብርሃን የሚታይበት፣ በተለይም ለዩክሬን ሕዝብ ልዩ የሰላም ተልዕኮ መልዕክት የሚደርስበት እና የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ዘወትር ደስታን የሚያጎናጽፍ መሆኑን ክቡር አባ ኮርኮራን አስረድተዋል።

14 September 2022, 17:05