ፈልግ

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሕፃን ጋር የሚያሳይ ሐውልት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሕፃን ጋር የሚያሳይ ሐውልት  (ANSA)

የሕይወትን ውበት እና ቅድስና ለመግለጽ የታሰበ የሐውልት ሥራ ተመረቀ

በቫቲካን የሥነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ፣ እሑድ ግንቦት 21/2014 ዓ. ም. “የሕይወት ሐውልት” የሚል ስያሜ የተሰጠውን ሐውልት መርቀው ለተመልካች ይፋ ባድረጋቸው ታውቋል። በካናዳዊው አርቲስት ጢሞቴዎስ ፖል ሽማልዝ የተቀረጸው የነሐስ ሐውልት፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በማኅጸኗ ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን ልጅ መጽነሷን የሚያሳይ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ካናዳዊው የሥነ ጥበብ ሰው ጢሞቴዎስ ፖል ሽማልዝ በተለይ “የቤት አልባው ኢየሱስ” ሐውልትን እና መላዕክት የማያውቁ የስደተኞች እና በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለእይታ የተቀመጠውን የስደተኞች ምስል የቀረጸ ሲሆን፣ በቅርብ ጊዜ ሥራው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሕፃን ጋር የሚያሳይ ሐውልት ሰርቶ ማቅረቡ ታውቋል።

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሐውልት በከፊል
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሐውልት በከፊል

ውበት ሕይወትን ሊያድን ይችላል

የስነ ጥበብ ሰው ጢሞቴዎስ ፖል ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ “ይህ ሐውልት መቅረጽ እጅግ አስደሳች ሆኖ አግኝቼዋለሁ” ለሥራው ያነሳሳውም፣ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የሐዋርያዊ እንደ ራሴ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ሊቀ ጳጳስ ክሪስቶፈር ፒየር “ውበት ዓለምን ሊያድናት ይችላል” በማለት በዶስቶየቭስኪ የሰጡት ጥቅስ መሆኑን አስውሶ፣ ጥቅሱን በሐውልት መልክ ቢሰራው አስደሳች ሊሆን እንደሚችል እና ሕይወትን ውበት የሚያረጋግጥ ሐውልት መሥራት እንደሚችል መረዳቱን ገልጿል። ከጢሞቴዎስ ፖል የሥነ ጥበብ ሥራዎች መካከል አብዛኛው ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በማትኮር፣ የመኖሪያ ቤት እጦትን፣ ስደትን እና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ በማኅበራዊ ፍትህ ላይ የሚያተኮሩ መሆናቸው ታውቋል። “እነዚህ ማኅበራዊ ርዕሠ ጉዳዮች በሥነ ጥበብ ሥራ ውስጥ መገለጽ ባለባቸውን ጉዳዮች ላይ ትኩረት እየሰጡ እንደሆነ ይሰማኛል" ያለው ጢሞቴዎስ፣ "የሥነ ጥበብ ሥራ አንድን ርዕሠ ጉዳይ የማስተዋወቅ እና ግንዛቤን የማስጨበጥ ተስፋ እንዳለው አምናለሁ” ብሏል።

“የሕይወት ውበትን የሚገልጽ ሐውልት”
“የሕይወት ውበትን የሚገልጽ ሐውልት”

'የማይታዩ' ርዕሠ ጉዳዮችን ወደ ብርሃን ማውጣት

በሥነ ጥበብ ኃይል እምነት እንዳለው የተናገረው የሥነ ጥበብ ሰው ጢሞቴዎስ፣ በጥሩ ሁኔታ፣ ስውር እና ውብ በሆነ መንገድ መላውን ማኅበረሰብ ግንዛቤ ማስጨበጥ ይቻላል” ብሏል። ሥነ ጥበብ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ሲባል ጥበብን በመጠቀም “በማኅጸን ውስጥ እንዳለው ጽንስ፣ ብዙውን ጊዜ የማይታዩ ጉዳዮችን ገሃድ ለማውጣት እንደሚያግዝ ገልጾ፣ “ይህ ሐውልት በሮም ከተማ እና በሌሎች ቦታዎችም የሕይወት ውበት እና ቅድስና ግንዛቤን በማምጣት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል” ሲል አስረድቷል።

ከዘመናችን ባርነት ነፃ ለመውጣት የምትረዳ የቅድስት ባኪታ ሐውልት
ከዘመናችን ባርነት ነፃ ለመውጣት የምትረዳ የቅድስት ባኪታ ሐውልት

ለአደጋ የተጋለጡትን ከጉዳት የመጠበቅ አስፈላጊነት

በ“ጣሊያን የሕይወት እንቅስቃሴ” ማኅበር በኩል በስጦታ የቀረበውን አዲሱን ሐውልት እሑድ ግንቦት 21/2014 ዓ. ም.  መርቀው ይፋ ያደረጉት፣ በቫቲካን የሥነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ መሆናቸው ታውቋል። ብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ፓሊያ፣ በሥነ ሥርዓቱ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የሐውልቱ ምረቃ ሥነ ሥርዓት የተካሄደ “ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ሕይወት የመጠበቅ አስፈላጊነት ግንዛቤ እያደገ ባለበት ወቅት ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ሊቀ ጳጳስ ፓሊያ አክለውም፣ የሚናገሩት ርዕሠ ጉዳይ ሚስት ከባሏ ጋር ጽንስን ከማስወረድ ይልቅ ልጅን መውለድ እና ለማሳደግ የሚገጥመውን የገንዘብ አቅምን ጨምሮ ሁሉንም የድህነት ዓይነቶችን በማሸነፍ የሚቻለውን ጥረት ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት ጭምር እንደሆነ አስረድተዋል። በሮም ውስጥ በቅዱስ ማርቼሎ አል ኮርሶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚቀመጥ ከዚህ አዲስ ሐውልት በተጨማሪ ቅጂው ተመሳሳይ ሐውልት በሌሎች በርካታ የሰሜን አሜሪካ ከተሞች ውስጥ ለእይታ ከቀረበ በኋላ በዋሽንግተን ዲሲ በቋሚነት የሚቀመጥ መሆኑ ታውቋል።

30 May 2022, 18:46