ፈልግ

የዩክሬን ጦርነት ያስከተለወ የረሃብ ቀውስ የዩክሬን ጦርነት ያስከተለወ የረሃብ ቀውስ 

የአውስትራሊያ በጎ አድራጊ ድርጅት በአፍሪካ ቀንድ የረሃብ አደጋ ስጋት መኖሩን አስታወቀ

“ካሪታስ አውስትራሊያ” የተሰኘ ካቶሊካዊ በጎ አድራጊ ድርጅት፣ ኢትዮጵያን፣ ሶማሊያን እና ኤርትራን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ አገራት ከፍተኛ የረሃብ አደጋ ስጋት መኖሩን አስታውቆ፣ ለእነዚህ አገራት አስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደረግላቸው በማለት አሳስቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ ቀንድ አገራት የሚኖሩ ሕዝቦች ዝቅተኛ የዝናብ መጠን እንደነበራቸው፣ በአሥርት ዓመታት ውስጥ ከተከሰቱት እጅግ በከፋ ሁኔታ በአንበጣ መንጋ መጠቃታቸው፣ ቀጣይነት ባላቸው ግጭቶች ምክንያት መፈናቀል እንደነበር እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመጎዳታቸው አሁን በክልሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለርሃብ አደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን “ካሪታስ አውስትራሊያ” አስታውቋል።

የካሪታስ አውስትራሊያ፣ የአፍሪካ ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅት ተጠሪ አቶ አሎይስ ካኔቴ፣ በጅቡቲ፣ በኤርትራ፣ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕዝቦች አስከፊ የረሃብ አደጋ እንዳጋጠማቸው ገልጸው፣ ይህም በዘመናችን ከታየው አደጋ እጅግ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

“ከሁሉም በላይ የሚያሳስበው፣ በዩክሬን ያለው ጦርነት ቀድሞውንም ቢሆን በችግር ውስጥ የሚገኙ የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ለተጨማሪ አደጋ ዳርጎአቸዋል” ያሉት አቶ አሎይስ፣ በአካባቢው አገራት የምግብ ዋጋ መጨመሩን እና አገራቱ በአብዛኛው የሚመኩት ከዩክሬን እና ከሩሲያ በሚመጡት ህሎች እና ማዳበሪያ ውጤቶች እንደሆነ ገልጸው፣ ምርቶቹ በአሁኑ ጊዜ ወደ አካባቢው መድረስ ያቋረጡ መሆኑን አስረድተዋል።

የምግብ ዕርዳታ ጥሪ

በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ሁኔታ አሳሳቢ የሚያደርገው፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚመራው የዓለም ምግብ ፕሮግራምም 50% የሚሆነውን የስንዴ እና የበቆሎ እህሎችን የሚያገኘው ከዩክሬን እና ከሩሲያ እንደሆነ አቶ አሎይስ አስታውሰው፣ "ድርጅቱ የሚያቀርበው የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት የበለጠ ውድ እና ውስብስብ የሚሆነው በተለይ አሁን ያለው የእህል ክምችት ሲያልቅበት ነው” ብለው፣ ፈጣን የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ከሌለ ነገሮች አስቸጋሪ እንደሚሄዱ አስረድተዋል። 

ወደ ካሪታስ አውስትራሊያ የአፍሪካ የምግብ ቀውስ አስወጋጅ ድርጅት የሚደርሱ የተለያዩ ዕርዳታዎች፣ በአጋር ድርጅቶች አማካይነት፣ በገንቢ ምግብ እጥረት ለተጎዱ ህፃናት፣ ለንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ፣ ለድህነት ለተጋለጡት እና በጦርነት ምክንያት ለተፈናቀሉ ቤተሰቦች እንደሚደርሳቸው፣ የካሪታስ አውስትራሊያ፣ የአፍሪካ ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅት ተጠሪ፣ አቶ አሎይስ ካኔቴ አስታውቀዋል።

21 May 2022, 18:50