ፈልግ

ኔልሰን ማንዴላ በደ. አፍሪካ እ. አ. አ በ1994 ምርጫ ድምጻቸውን ሲሰጡ ኔልሰን ማንዴላ በደ. አፍሪካ እ. አ. አ በ1994 ምርጫ ድምጻቸውን ሲሰጡ  

የደቡብ አፍሪካ ዴሞክራሲ የአገሪቱን እውነታ በትክክል አይገልጽም ተባለ

በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ሥርዓት ካበቃ ከ28 ዓመታት በኋላም የሰብዓዊ መብት ረገጣ መቀጠሉን፣ በደቡብ አፍሪካ የኢየሱሳውያን ማኅበር ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አባ ራስል ፖሊት ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገሪቱ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ሁኔታዎችን በማስታወስ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸው፣ የደቡብ አፍሪካ ዴሞክራሲ የአገሪቱን እውነታ በትክክል የማይገልጽ መሆኑ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የመጀመሪያው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ከተካሄደበት የአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 27/1994 ዓ. ም. በኋላ 28 ዓመታት መቆጠራቸውን የመንግሥት ድረ-ገጽ አስነብቧል። በወቅቱ በተካሄደው ምርጫ ኔልሰን ማንዴላ መመረጣቸውም ይታወሳል። “ዕለቱን ብዙ ሰዎች አክብረውት ስለመዋላቸው እርግጠኛ አይደለሁም!” ያሉት ክብር አባ ራስል፣ አገሪቱ ቀድሞ ከነበረችበት መለወጧን እና ዛሬ ሁሉም ሰው የመምረጥ መብት እንዳለው ገልጸው፣ ከ28 ዓመታት በኋላም ቢሆን ድሃውን ማኅበረሰብ የሚቀጣ ሥርዓት በስፋት መዘርጋቱን፣ ሙስና፣ ዘረፋ እና በመንግሥት ላይ እምነት ማጣት ማደጉን መመልከት ይቻላል ብለዋል።

ምርጫ ከተካሄደ ጥቂት ዓመታት በኋላ የተከሰተ አሳዛኝ ሁኔታን ያስታወሱት ክቡር አባ ራስል፣ ይህም በደቡብ አፍሪካ ጋውቴንግ ግዛት የአእምሮ ሕክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ከረሃብ እና ከብቸኝነት ጋር በተያያዙ ምክንያቶች 144 ሰዎች መሞታቸውን አስታውሰዋል። “በአስከሬኖቹ የተካሄደው ምርምርራ ከሟቾቹ መካከል አንዳንዶቹ በሆዳቸው ወረቀት መያዛቸውን አሳይቷል” ብለዋል። ክቡር አባ ራስል አክለውም፣ እነዚያ አረጋውያን እና የግንዛቤ ችግር ያለባቸው ሰዎች የሚፈልጉትን ለማግኘት እንኳን ጥያቄ ማቅረብ የማይችሉ እንደነበር ገልጸዋል።

በወረርሽኙ ወቅት የነበረው ሙስና

በቅርቡ ከሥራ ገበታቸው የተሰናበቱት የአገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር፣ እርሳቸው እና ቤተሰቦቻቸው በወረርሽኙ ወቅት ከስርቆት ያገኙት ጥቅም፣ “ድሆችን ለማገዝ የታቀዱ የሕክምና መሣሪያዎች ስርቆት" የሚለውን እውነታ አጉልቶ ማሳየቱን ክቡር አባ ራስል ገልጸዋል። አባ ራስል ቀጥለውም፣ “ይህ የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስን ጨምሮ ብዙ ድርጅቶች የፈለጉትን የሚያደርጉበት የእብሪተኝነት ተግባር ሌላው ምሳሌ ነው” ብለው፣ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የፖለቲካ ልሂቃን ጥሩ ኑሮ ሲመሩ ድሆች ግን እየደኸዩ መጥተዋል” ብለዋል።

በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በማሳበብ ለትራንስፖርት፣ ለመጠለያ፣ ለሆቴሎች እና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውል ከ1.4ቢሊየን ዶላር በላይ መንግሥት ያገኘ ቢሆንም፣ ብዙ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ የሕክምና አገልግሎት እንኳን ማግኘት አለመቻላቸውን አባ ራስል አስረድተዋል። በሰብዓዊ መብት አያያዝ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ከፍተኛ እውቅናን እንዳገኘ ቢነገርለትም እውነታው ግን ሌላ መሆኑን ገልጸዋል።

ደቡብ አፍሪካ ለዩክሬን ቀውስ ምላሽ አለመስጠት

በዩክሬን እየተካሄድ ላለው ጦርነት የደቡብ አፍሪካ መንግሥት መልስ መንፈጉን የገለጹት አባ ራስል፣ ምንም እንኳን ደቡብ አፍሪካ ትንሽ ሀገር በመሆኗ ብዙ ለውጥ ማምጣት ባትችልም በዩክሬን እየተፈጸመ ባለው የሰብዓዊ መብት ረገጣ ላይ ጠንከር ያለ አቋም ለመያዝ ፈቃደኛ አለመሆኗን ገልጸዋል። 

የሚፈለገው ተግባር እንጂ የቃላት ድርድር አይደለም

ደቡብ አፍሪካ አስደናቂ ሕገ መንግሥት እና በቂ ሕግ እንዳላተ ክቡር አባ ራስል ገልጸው፣ ትልቁ ችግር ግን በተግባር አለመተርጎማቸው ነው ብለው፣ መሬት ላይ በተቀመጡ ደንቦች እና አተገባበር መካከል ትልቅ ክፍተት እንዳለ፣ ሀገሪቱ በመብት ማስጠበቅ ላይ ያላት አቋም ያልተለወጠ ቢሆንም ነገር ግን በሚነገረው እና በተጨባጭ በሚታየው ሃቅ መካከል ከፍተኛ ልዩነት እንዳለ፣ በደቡብ አፍሪካ የኢየሱሳውያን ማኅበር ተቋም ዳይሬክተር፣ ክቡር አባ ራስል ፖሊት አስተያየታቸውን ደምድመዋል።

28 April 2022, 16:29