ፈልግ

ወደ ስፔን ያቀና የስደተኞች የባሕር ላይ ጉዞ ወደ ስፔን ያቀና የስደተኞች የባሕር ላይ ጉዞ 

ከአዲሱ የአውሮፓውያኑ ዓመት ጀምሮ በቀን አራት ስደተኛ እንደሚሞት ተገለጸ

ስለ “ሥልጣኔ መቋረጥ” በመናገር ከሰሜን አፍሪካ ወደ አውሮፓ በሚያደርጉት የባሕር ላይ ጉዞ የሚሞቱትን በርካታ ስደተኞችን በማስታወስ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ስደተኞች የሰው ልጆች መሆናቸውን እንጂ ብዛታቸውን መመልከት ተገቢ አይደለም!” በማለት ማስገንዘባቸው ይታወሳል። ባሁኑ ጊዜ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት የስደተኞችን ጉዞ ይቀንስ እንጂ የምይገታው መሆኑን፣ በሰሜን ጣሊያን፣ ሚላን ከተማ በሚገኝ የቢኮካ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የስደት ጉዳይ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ላውራ ቴሬራ አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ያለፈው ቅዳሜ መጋቢት 24/2014 ዓ. ም. በሊቢያ የባሕር ዳርቻ በደረሰው የመርከብ አደጋ 90 ሰዎች ሲሞቱ አራቱ ብቻ በሕይወት ተርፈዋል። ከሦስት ሳምንታት በፊት በሞሮኮ የባሕር ዳርቻም 44 ሰዎች ሞተዋል ። ከእነዚህ የመጨረሻዎቹ ሁለት አሳዛኝ ሁኔታዎች በፊት፣ ከዓመቱ መጀመሪያ አንስቶ ማዕከላዊ ሜዲትራኒያንን ለመሻገር ሲሞክሩ የሞቱት ወይም የጠፉ ስደተኞች ቁጥር 299 መድረሱ ሲነገር እ. አ. አ በ2021 ዓ. ም. የሞቱት ስደተኞች ቁጥር 1,553 እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማልታ ደሴት ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ከተመለሱ በኋላ “የሥልጣኔ መርከብ መሰበር” በሚል ርዕሥ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሜዲትራኒያን ባሕር ጦርነትን፣ ድህነትን እና ድርቅን ሸሽተው ለሚሰደዱ ሰዎች መቃብር መሆኑን በሐዘን ገልጸዋል። አራተኛ ወሩን ከያዘው የአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ ማዕከላዊ የሜዲትራኒያ ባሕር ሲያቋርጡ በሚያጋጥም አደጋ የሚሞቱ ስደተኞች ቁጥር በቀን ከአራት በላይ እንደሚሆን ተገምቷል።

በሌላ ወገንም ሩሲያ ባለፈው የካቲት 17/2014 ዓ. ም. በዩክሬን ላይ የከፈተችው ጥቃትም ቀጣይነት ባለው መልኩ ሰላማዊ ዜጎችን ወደ ጎረቤት ሀገራት በተለይም ወደ ፖላንድ እንዲሸሹ አድርጓቸዋል። ከአፍሪካ የሳህል ሀገራት የሚወጡ ስደተኞች በጉዞአቸው ወቅት ሊደርስባቸው ስለሚችል ጉዳት ማብራሪያ እንዲሰጡ በሚላኖ የቢኮካ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ፍልሰት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ላውራ ተጠይቀዋል።

ፖለቲካዊ መፍትሄ ያሻዋል

በተለያዩ አካባቢዎች ጦርነቶች መካሄዳቸው ስደትን እንደማያግድ በእርግጠኝነት የተናገሩት ፕሮፌሰር ላውራ፣ በዓለማችን ደቡባዊው ክፍል የሚታየው የስደተኞች ጉዳይ ቀደም ሲል ለዓመታት ያህል የታዩ እንደነበር ገልጸው፣ በሶርያ እና በየመን ውስጥ ለዓመታት የዘለቀው ጦርነት ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚደረገውን የስደተኞች ጉዞን ያልገታው መሆኑን አስረድተዋል። እንደ ፕሮፌሰር ላውራ ገለጻ መሠረት፣ የስደት ቀውስን በአግባቡ ለመቆጣጠር የሚያስችል የተደራጀ እና የተባበረ ፖለቲካዊ ፍላጎት ሊኖር እንደሚያስፈልግ የታመነበት ቢሆንም፣ ይህ ግን እስከ ዛሬ በግልጽ አልታየም ብለዋል።

ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር አዲስ መፍትሄ

ከሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ የወንጀል ድርጅቶች በኩል ብዙ ተለዋዋጭነት ይታል ያሉት ፕሮፌሰር ላውራ፣ እነዚህ ድርጅቶች የበለጠ ምቹ እና ቀላል መንገዶችን ለመለየት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፣ በዚህ ደረጃ ጦርነቱን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ሕገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ከአፍሪካ ለሚወጡ ስደተኞች የባልካን አገራት መንገዶችን ለማስከፈት ሲሞክሩ እናያለን ብለው፣ በዩክሬን በኩል ያለው ግንባር ሕገ ወጥ የሰዎች ስውውርን ለማካሄድ ምቹ መንገድ መሆኑን አስረድተዋል። በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ ከፍተኛ የስደተኞች እንቅስቃሴ በምዕራቡ አቅጣጫ መኖሩን እንመለከታለን ያሉት ፕሮፌሰር ላውራ፣ በሞሮኮ የባሕር ዳርቻ የታየው የመርከብ አደጋ በምዕራቡ በኩል መከሰቱን አስታውሰዋል። የውቅያኖሱ ምዕራቡ በኩል እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ የስደተኞች እንቅስቃሴ ያልታየበት ቢሆንም ካሁን በኋላ የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል። ይህ ማለት በግሪክ እና በቱርክ በኩል ያለው የስደተኞች እንቅስቃሴ ይቆማል ማለት እንዳልሆነ ያስረዱት ፕሮፌሰር ላውራ፣ ፖለቲካዊ ችግሮቹን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ብዙ ፍላጎቶች ተጽዕኖ እንዳያደርጉ፣ በአውሮፓ አገራት መካከል አንድነት ሊኖር ይገባል ብለዋል።

06 April 2022, 14:27