ፈልግ

በሮም ከተማ የሚገኝ የአስታሊ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች አገልግሎት መስጫ ማዕከል በሮም ከተማ የሚገኝ የአስታሊ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች አገልግሎት መስጫ ማዕከል  (Francesca Napoli)

የስደተኞች ቁጥር እና በሴቶች ላይ የሚደርስ በደል በእጥፍ መጨመሩ ተገለጸ

ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው ስደተኞች ከለላን የማግኘት መብት የሚከለክል አካሄድን በጽኑ እንደሚያወግዝ፣ በጣሊያን የሚገኝ የኢየሱሳውያን ማኅበር የስደተኞች አገልግሎት ማስተባበሪያ ማዕከል በዓመታዊ ሪፖርቱ አስታውቋል። የሜዲቴራንያን ባሕርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ የሚደርሱ ስደተኞች ቁጥር በእጥፍ እንደጨመረ ያስታወቀው ሪፖርቱ፣ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ሸሽተው የሚሰደዱትን ጨምሮ በዓለማች ውስጥ የሚገኝ የስደተኛ ቁጥር ወደ ዘጠና ሚሊዮን መድረሱን በሮም ከተማ የሚገኝ የአስታሊ ስደተኞች አገልግሎት ማስተባበሪያ ማዕከል መረጃን ዋቢ በማድረግ የማዕከሉ ፕሬዚደንት ክቡር አባ ካሚሎ ሪፓሞንቲ አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የሚፈናቀሉትን ጨምሮ በዓለማችን የሚገኙ ስደተኞች ቁጥር ወደ ዘጠና ሚሊዮን መድረሱን በሮም የሚገኝ የኢየሱሳውያን ማኅበር የስደተኞች አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በ2022(እ. አ. አ) ሪፖርቱ አስታውቋል። በ2021 (እ. አ. አ) ወደ ጣሊያን ከገቡት ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚበልጡ የዩክሬን ስደተኞች በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደ ጣሊያን መድረሳቸውን ሪፖርቱ አስታውቋል። በዩክሬን የሚካሄደውን ጦርነት ሸሽተው ወደ ጣሊያን የሚገቡ ስደተኞች ለአገሪቱ ደኅንነት አስጊ አለመሆናቸውን ዓመታዊ ሪፖርቱ ገልጿል። “በዩክሬን እያጋጠመን ያለው ድንገተኛ አደጋ በዓለም ውስጥ የሚታዩ ሌሎች በርካታ ድንገተኛ አደጋዎችን እንደሚያስታውሳቸው፣ በሮም ከተማ የሚገኝ የአስታሊ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች አገልግሎት መስጫ ማዕከል ፕሬዚደንት ክቡር አባ ካሚሎ ሪፓሞንቲ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት ገልጸዋል። እ. አ. አ. በነሐሴ 2021 ዓ. ም. በአፍጋኒስታን ውስጥ የነበረው ሁኔታ እና እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ አገሮች ያለው ጦርነት የተዘነጋ መሆኑን የገለጹት አባ ካሚሎ፣ የዓለም ጦርነት አካል የሆኑ ብዙ ድንገተኛ አደጋዎች እንዳሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ደጋግመው መናገራቸውን አስታውሰዋል።

በባሕር በኩል የሚመጡ ስደተኞች

ባሕርን አቋርጠው ወደ ጣሊያን የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር (እ. አ. አ.) በ2021 ዓ. ም. በእጥፍ መጨመሩን እና በጠቅላላው ከ 67,000 በላይ መሆኑን ዓመታዊ ሪፖርቱ ገልጾ፣ ከእነዚህም መካከል ያለ ቅርብ ረዳት ብቻቸውን የቀሩ ታዳጊ ሕጻናት ቁጥር ወደ 9,500 እንደሚጠጋ ገልጿል። ስደተኞችን የሚደርስ ስቃይ እና እንግልት እንደጨመረ የገለጸው ሪፖርቱ፣ ወደ አስታሊ የስደተኞች ማዕከል ከሚመጡት ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ በትውልድ አገራቸው ወይም በጉዞ ላይ ስቃይ የደረሰባቸው፣ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት የተፈጸመባቸው እና ሊቢያ ውስጥ በእስር ቤት ውስጥ የቆዩ መሆናቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል። ሪፖርቱ አክሎም እ. አ. አ በ2021 ዓ. ም. በማዕከሉ ውስጥ የማህጸን ሕክምና ዕርዳታን የተከታተሉ ከ200 በላይ ሴቶች መኖራቸውን አስታውቋል።

የአስቸኳይ ዕርዳታ አቅርቦት

እ. አ. አ. በ 2021 ዓ. ም. በአውሮፓ ውስጥ ስደትን በተመለከተ ሁሉን አቀፍ የጋራ ፖሊሲ ማዘጋጀት ካልተቻለ ከደኅንነት እና ከድንገተኛ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር የተዛመዱ ችግሮች በስደተኞች ላይ ተጋላጭነትን እና ማኅበራዊ መገለል ሊያስከትል እንደሚችል በጣሊያን የሚገኝ አስታሊ የስደተኞች አገልግሎት ማስተባበሪያ ማዕከል አስታውቋል። ዛሬም ቢሆን ከሦስት ስደተኞች መካከል ሁለቱ በማዕከላት ውስጥ እንደሚስተናገዱ የገለጸው ሪፖርቱ፣ ይህም ወረርሽኙን ለመግታት ያሚወሰድ እርምጃን የበለጠ እንዲወሳሰብ ማድረጉን እና አቅመ ደካማ የሆኑ ተረጂዎች ችግር ከግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑን አስታውቋል።

ፍርሃትን ለመዋጋት በጋራ መወያየት

ፍርሃትን ለማስወገድ የበለጠ እውቀት እና የውይይት ዕድል እንደሚያስፈልግ የገለጸው ሪፖርቱ፣ እ. አ. አ በ2021 ዓ. ም. የአስታሊ የስደተኞች አገልግሎት መስጫ ማዕከል 17,000 ስደተኞችን ተቀብሎ እንዳስተናገደ እና ከነዚህም መካከል 10,000 የሚደርሱት በሮም ከተማ ውስጥ የሚኖሩ መሆናቸውን ገልጿል። የአገልግሎት ድርሻን በመወጣት እና ለሰዎች የጋራ ሕይወት ትኩረትን በመስጠት ሰፊ የመስተንግዶ እና የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት፣ ስደተኞችን በኅብረት የሚኖሩባቸውን ቦታዎች ማመቻቸት፣ ይህም ተማሪዎች በየዩኒቨርሲቲው አብረው እንደሚማሩ ሁሉ ስደተኞችም በኅብረት የሚሆኖሩበትን አጋጣሚ በማመቻቸት፣ አብሮ የመኖር ባሕል ተግባራዊ የሚሆንበትን መንገድ ስደተኞች እንዲጀምሩ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን፣ በሮም ከተማ የሚገኝ የአስታሊ ስደተኞች አገልግሎት ማስተባበሪያ ማዕከል ፕሬዚደንት ክቡር አባ ካሚሎ ሪፓሞንቲ ገልጸዋል።    

13 April 2022, 16:28