ፈልግ

የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት  (AFP or licensors)

አሜሪካ በሩሲያ የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ምርቶችዋ ላይ ማዕቀብ መጣሏን አስታወቀች

በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ጦርነት ከተጀመረ ከሁለት ሳምንታት በኋላ በሩሲያ ኢኮኖሚ ላይ አዳዲስ እርምጃዎች መወሰዳቸው ታውቋል። የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ፣ የእንግሊዛዊው ደራሲ የዊሊያም ሼክስፒርን አባባል በመጥቀስ ለምክር ቤታቸው ባደረጉት ንግግር፣ "ሆኖ መገኘት ወይም አለመሆን? እኛ መኖርን እንመርጣለን" ብለው፣ ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገራት የሚደረግ የዜጎቻቸው ስደት ሳያቋርጥ መቀጠሉን አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሌላ ወገን በዩክሬን ላይ የተከፈተው ጦርነት አሥራ አራተኛ ቀኑን በያዘበት ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ በሩሲያ ኢኮኖሚ ላይ ያልተለመዱ እርምጃዎችን ከመውሰዷ ጋር፣ አዲስ የሚሳኤል ጥቃት ሊሰነዘር ስለሚችል ዩክሪናዊያን በመጠለያዎች ውስጥ እንዲቀመጡ ያስጠነቀቀች ሲሆን፣ ትናንትና በስቲያ ፀረ አውሮፕላን መሣሪያ ፍንዳታ በኪዬቭ እና አካባቢዋ መሰማቱ ታውቋል። እንደ ፔንታጎን ዘገባ መሠረት የሩስያ ወታደሮች ከኪየቭ ከተማ በስተሰሜን በኩል ሊያካሂዱት የነበረው የጥቃት ዘመቻ የተቋረጥ መሆኑን እና በደቡብ ዩክሬን ግን መጠነኛ እንቅስቃሴዎች ማሳየታቸውን ገልጿል። እንደ አሜሪካ መከላከያ ገለጻ መሠረት፣ ሩሲያውያን የዩክሬይን ዋና ከተማ ኪዬቭን ከምስራቅ በኩል ለማጥቃት እየሞከሩ መሆናቸውን ገልጾ፣ የሩሲያ ጦር ሠራዊት ከዋና ከተማዋ ኪዬቭ አሁንም በ60 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት እንደሚገኙ አስታውቋል።

የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ማዕከላት

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ኢንተርፋክስ የዜና ወኪል የሩሲያ ብሔራዊ ጥበቃ ዋቢ በማድረግ ባሰራጨው ዘገባው በዩክሬን የሚገኝ የዛፖሪዚያ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ማዕከል ሙሉ በሙሉ በሩሲያ ወታደራዊ ኃይሎች  ቁጥጥር ስር መሆኑን አስታውቋል። ከሞስኮ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመላክቱት፣ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ማዕከልን የሚጠብቁ ወደ 240 የሚጠጉ ሰዎች ለሩሲያ ጦር ሠራዊ እጃቸውን መስጠታቸውን አስታውቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሩሲያ ቁጥጥር ስር የሚገኝ የቼርኖቤል ኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ቁሳቁሶች የርቀት መቆጣጠሪያ ሥርዓቶች መረጃዎችን ማስተላለፍ አቁመዋል ሲል ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ማዕከል ዘግቧል።

በማሪዮፖል የቦምብ ፍንዳታ አይሏል

ከሌሎች የዩክሬን ግዛቶች ተገልላ የሚትገኝ የማሪዮፖል ከተማ የሚሰነዘርባትን ጥቃት አሁንም ለመከላከል እየሞከረች ሲሆን፣ በቋሚነት የሚሰነዘርባት የበቦምብ ጥቃት በሲቪሎች ላይ በተለይም በሕጻናት ላይ የሚደርስ ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ታውቋል። ሞስኮ የኦዴሳን ወደብ ከመሬት ለማጥቃት ወስናለች የሚለው መላምት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ታውቋል። ይህ በንዲህ እንዳለ ለሰብዓዊ ዕርዳታ መስጫ በተዘጋጁ መስመሮች በኩል ከዩክሬን የተፈናቀሉ የመጀመሪያዎቹ ሲቪሎች "በአስተማማኝ ሁኔታ" በአገሪቱ መካከለኛው ክፍለ ሀገር ወደሚገኝ ከሱሚ ከተማ መድረሳቸው ታውቋል። "ተፈናቃዮችን ያሳፈሩ የመጀመሪያዎቹ 22 አውቶብሶች ወደ ፖልታቫ ከተማ የገቡ ሲሆን፣ ሌሎች 39 አውቶቡሶች አሁንም ጉዞ ላይ መሆናቸው ታውቋል። በሩስያ ላይ የተጣሉ ኤኮኖሚያዊ እና የፋይናንስ እቀባዎች እንደቀጠሉ ሲሆን፣ የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች፣ ኮካ ኮላን የመሳሰሉ ሌሎች በርካታ ግዙፍ የንግድ ድርጅቶች መታገዳቸው ታውቋል።

"መኖር እንፈልጋለን"

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዮሴፍ ባይደን በሩሲያ የኢነርጂ ማዕቀብ አሜሪካ የሁለትዮሽ ስምምነት ማድረጓን ገልጸው፣ ነገር ግን ብዙ አጋሮቻቸው ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻላቸውን አስረድተዋል። "ፑቲን ሊያሸንፍ አይችልም” ያሉት ዮሴፍ ባይደን፣ አንዳንድ ከተሞችን አሸንፎ መያዝ ቢችልም፣ ነገር ግን ይህ ማለት ደግሞ ሙሉ አገርን አሸንፏል ማለት አይደለም" ብለዋል። እንዲሁም የብሪታንያ ፓርላማ፣ የዩክሬኑ ርዕሠ መስተዳድር ዘሌንስኪ ያደረጉትን ንግግር በጭብጨባ መቀበሉ ታውቋል። “በዘመናት ውስጥ የፓርላማው ምክር ቤት እንደዚህ ዓይነት ንግግር ሰምቶ አያውቅም” ያሉት የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆንሰን፣ እኛ ሁልጊዜ ከዩክሬናውያን ጎን እንሆናለን" በማለት ተናግረዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ በንግግራቸው፥ "ከዚህ በፊት በናዚ ወረራ ወቅት ተስፋን እንዳልቆረጣችሁ ሁሉ፣ እኛም የኛ የሆነውን ነገር ማጣት አንፈልግም" ብለው፣ "ቢያንስ 50 ህጻናት በሩሲያውያን መገደላቸውን ገልጸው፣ ሩሲያ አሸባሪ መንግስት ስለመሆኗ እውቅና እንዲሰጣት እና የዩክሬንን ደኅንነት ለማስጠበቅ ምዕራባውያን አገራት ዕርዳታ ያስፈልገናል" በማለት አጽንዖት ሰጥተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን በዩክሬን ተኩስ እንዲቆም ያቀረቡትን ሃሳብ የሚደግፉት መሆናቸውን ገለጸው፣ "የተቀናጀ ሰብዓዊ ዕርዳታን ለማቅረብ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀረበውን ሃሳብ የሚጋሩት መሆኑን ገልጸዋል። 

10 March 2022, 16:07