ፈልግ

በዩክሬን የሚካሄደውን ጦርነት የሚሸሹ ሰዎች ቁጥር በመጨመር ላይ ይገኛል በዩክሬን የሚካሄደውን ጦርነት የሚሸሹ ሰዎች ቁጥር በመጨመር ላይ ይገኛል  (ALEKSANDRA SZMIGIEL)

በዩክሬን ከሁለት ሚሊዮን ተኩል በላይ ሰዎች መሰደዳቸው ተነገረ

በሩሲያ ከበባ ስር የምትገኘውን ዩክሬን በመሸሽ ወደ ፖላንድ፣ ሃንጋሪ እና ሌሎች ጎረቤት አገራት የተሰደዱት የዩክሬን ስደተኞች ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን ተኩል በላይ መድረሱን በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት “UNHCR” አስታውቋል። ዩክሬናውያን ከጦርነጡ አደጋ ለመትረፍ ወደ ጎረቤት አገራት የሚያደርጉት ሽሽት ተጠናክሮ መቀጠሉን ድርጅቱ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሁለቱ የዩክሬን ጎረቤት አገራት፣ ሮማኒያ እና ሞልዳቪያ ከፍተኛ የስደተኞች መተላለፊያ መስመሮች የሚገኙባቸው አገራት መሆናቸው ታውቋል። በጣሊያን ሮም ከተማ የሚገኝ ማኅበራዊ ፖሊሲዎች ማስተባበሪያ ክፍልም፣ “ወደ ጣሊያን እንኳን ደህና መጣችሁ!” ከሚል የስደተኞች አገልግሎት መስጫ ማዕከል ጋር በመተባበር፣ ወደ ጣሊያን የሚገቡ የዩክሬን ስደተኞችን ለመቀበ መዘጋጀቱ ታውቋል። በጣሊያን አሲያጎ ከተማ የሚገኙ “የታላቁ ጦርነት” መታሰቢያ የቀድሞ ሆስፒታሎች በጊዜያዊ የስደተኞች መጠለያነት እንደሚያገለግሉ ታውቋል። 

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ፣ "የሰብዓዊ ዕርዳታ ማቅረቢያ ኮሪደሮችን በመጠቀም ወደ 125,000 የሚጠጉ ስደተኞችን ወደ ጎረቤት አገራት ማስወጣት ችለናል" ማለታቸውን የኪዬቭ ኢንዲፔንደንት ዘገባ ገልጾ፣ "ባሁኑ ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ጥረታችን ወደ ማሪዮፖል ከተማ ዕርዳታን ማድረስ ነው" ማለታቸውን ዘገባው አስታውቋል።

ስደተኞቹ ከሁለት ሚሊዮን ተኩል በላይ ደርሰዋል

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን፣ ቅዳሜ መጋቢት 3/2014 ዓ. ም. ባወጣው መረጃ በ24 ሰዓት ውስጥ ወደ 100,000 የሚጠጉ ስደተኞች በዩክሬን ያለውን ጦርነት ከሸሹት ተፈናቃዮች ጋር መቀላቀላቸውን ገልጾ፣ ከሁለት ሳምንታት ወዲያ ሩሲያ በዩክሬን ያካሄደችውን ወረራ ተከትሎ ከዩክሬን የተደዱት ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር በግምት ወደ 2,698,280 መድረሱን በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አስታውቋል። “ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ፈጣን ፍሰት አልታየም” ያሉት ፊሊፖ ግራንዲ፣ በጠቅላላው አራት ሚሊዮን ሰዎች ሀገሪቱን ለቀው እንደሚወጡ ይጠበቃል ብለው፣ ይህ አሃዝ በሚቀጥሉት ቀናትም ከፍ እንደሚል አስረድተዋል።

ከዩክሬን ጎረቤት አገራት የሚደረጉ ፍሰቶች

ከዩክሬን ስደተኞች መካለል ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን ፖላንድ እንደምታስተናግድ ሲነገር፣ የፖላንድ ድንበር ጠባቂዎች እስካሁን ወደ 1,675,000 የሚሆኑ የዩክሬን ስደተኞች ወደ ጎረቤት አገራት መግባታቸውን ገልጸዋል። ከቀውሱ አስቀድሞ በፖላንድ ውስጥ ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ዩክሬናውያን እንደሚገኙ የተነገረ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ በአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ውስጥ ለሥራ የሄዱ መሆናቸው ታውቋል።

በሮም፣ የእንኳን ደህና መጣችሁ ቤተሰቦች መዝገብ

በዩክሬን የሚካሄደውን ጦርነት ሸሽተው ከየትኛውም አቅጣጫ ወደ ጣሊያን ለሚመጡ ስደተኞች ቁሳዊ እና ስነ ልቦናዊ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል የ “እንኳን ደህና መጣችሁ!” የአብሮነት አገልግሎት ዝግጅት መጠናቀቁ ታውቋል። በሮም የማኅበራዊ ፖሊሲዎች እና ጤና መምሪያ “እንኳን ደህና መጣችሁ!” የቤተሰብ አገልግሎት ማዕከል የተቋቋመ ሲሆን፣ ከጣሊያን መንግሥት የስደተኞች አገልግሎት መስጫ ክፍል ጋር በመተባበር ጦርነቱን ሸሽተው ለሚመጡ የዩክሬን ስደተኞች በጣሊያን ውስጥ መስተንግዶ እና ድጋፍ የሚደረግላቸው መሆኑ ታውቋል። በጣሊያን መንግሥት የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ወ/ሮ ባርባራ ፉናሪ፣ የዩክሬን ስደተኞችን በራሳቸው ቤት ተቀብለው ለማስተናገድ የተዘጋጁ ከ300 በላይ ጣሊያናዊ ቤተሰቦች መኖራቸውን አስታውቀዋል።

የአሲያጎ ጊዜያዊ የስደተኞች ማረፊያ

በሰሜን ጣሊያን፣ አሲያጎ ከተማ “የታላቁ ጦርነት” መታሰቢያ የቀድሞ ሆስፒታሎች ከዩክሬን የመጡ ስደተኞች ተቀብሎ በጊዜያዊነት ለማኖር ምቹ ከሆኑት መዋቅሮች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸው ታውቋል። እቅዱ አንዳንድ አገልግሎት የማይሰጡ ሆስፒታሎችን በመጠቀም አስፈላጊውን የሕክምና ዕርዳታዎችን ለመስጠትን እና የመጀመሪያ ዕርዳታ አገልግሎቶችን ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑ ታውቋል። በዚህ ሳምንት ውስጥ ፈጣን የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች እንደሚሠሩ፣ ከመጋቢት 8/2014 ዓ. ም. ጀምሮም የመጀመሪያዎቹን የዩክሬን ስደተኞች ለመቀበል ዝግጅቱ እንደሚጠናቀቅ የከተማው ከንቲባ አቶ ሪጎኒ ስተርን አስታውቀዋል።

14 March 2022, 14:31