ፈልግ

ከሰሃራ በታች ባሉት የአፍሪቃ አገራት እና በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ የንጹሕ ውሃ አቅርቦት ችግር ከሰሃራ በታች ባሉት የአፍሪቃ አገራት እና በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ የንጹሕ ውሃ አቅርቦት ችግር 

ንጹሕ የመጠጥ ውሃን ለዓለም ለማዳረስ ለአሥር ዓመታት ጥረት ሲደረግ መቆየቱ ተነገረ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከ 2004 ዓ. ም. ጀምሮ በማደግ ላይ ባሉ 13 አገራት ውስጥ አርባ ሰባት የዕርዳታ ውጥኖችን ተግባራዊ ካደረጉት የበጎ ፈቃደኞች ተወካዮች ጋር መጋቢት 12/2014 ዓ. ም. በቫቲካን ተገናኝተዋል። የበጎ ፈቃደኛ ተወካዮቹ ጣሊያንን ጨምሮ በሌሎች አገራት ውስጥ የተከሰተውን የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የጎርፍ አደጋ እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀውስን ለማስወገድ ጥረት ያደረጉ መሆናቸው ታውቋል። ከተወካዮቹ አንዱ፣ በዩክሬን ያለው ጦርነት እና ያስከተለው የኃይል አቅርቦት ቀውስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ. አ. አ እስከ 2030 ድረስ ለሁሉም ሰው ንጹህ ውሃን ለማቅረብ የያዘውን ዕቅድ አደጋ ላይ መጣሉን ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከአሥር ዓመት በፊት የንጹሕ ውሃ እጥረትን ለማስወገ ከሰሜን ጣሊያን፣ ሞዴና ከተማ የተነሳው የበጎ ፈቃደኞች ማኅበር፣ ከሰሃራ በታች ባሉት የአፍሪቃ አገራት እና በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ የንጹሕ ውሃ አቅርቦት ችግርን ለማቃለል ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ታውቋል። “ተጠምቼ ነበር” የሚል መጠሪያ ስም ያለው እና በቁጥር 60 የሚደርሱ አባላት ያሉት የበጎ ፈቃደኞች ቡድን መጋቢት 12/2014 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ተገናኝቷል።

ከ2004 ዓ. ም. ጀምሮ አገልግሎት ሲያቀርብ ቆይቷል

በጓደኛሞች መልካም ፈቃድ የተጀመረው የልማት ሥራ ጣሊያንን ጨምሮ በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች በችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ከችግራቸው ለማውጣት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ታውቋል። የበጎ ፈቃደኞች ማኅበሩ በጣሊያን ውስጥ እ. አ. አ. በ 2012 በሰሜን ጣሊያን በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ለደረሰባቸው፣ እ. አ. አ በ2014 በጄኖቫ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ለተጎዱት ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል። አሁን ደግሞ ከሁለት ዓመታት ጀምሮ የተዛመተው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ ለተጎዱት ሰዎች ዕርዳታን በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል። ባሁኑ ጊዜ በ13 አገራት ውስጥ ሰብዓዊ ዕርዳታውን በማቅረብ ላይ የሚገኘው የበጎ ፈቃደኞቹ ማኅበር፣ በአፍሪቃ ውስጥ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባት ቡርኪና ፋሶ እና እ. አ. አ በነሐሴ ወር 2020 ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ ለደረሰበት የቤይሩት ከተማ ሕዝብ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ ታውቋል።

የመጠጥ ውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ እና የጤና ትምህርት አቅርቦት

ከጊዜ ወደ ጊዜ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ማግኘት የሚቻልባቸውን ሥፍራዎችን በማነጽ የአካባቢው ሕዝብ በቂ ውሃን እንዲያገኝ ያመቻቸው ማኅበሩ፣ ከዚህም በተጨማሪ የተላላፊ በሽታዎች ስርጭትን ለማስወገድ የኅብረተሰቡን የንፅህና አጠባበቅ ግንዛቤ ለማሳደግ እንደሚሰራ፣ መሠረታዊ የሆኑ የዕለት ተዕለት ተግባራትን፣ ትክክለኛ የውሃ እና የምግብ አጠቃቀም ሥርዓትን ጨምሮ የውሃ ማጠራቀሚያ መንገዶችን፣ የቤት ውስጥ ጽዳት እና የቆሻሻ ማስወገጃ መንገዶችን ሲያስተምር መቆየቱ ታውቋል።

የአካባቢ ማኅበረሰቦች እና ተቋማት ተሳትፎ

በበጎ ፈቃደኞቹ ማኅበር የታነጹ እያንዳንዱ የንጹሕ ውሃ መቅጃ ጣቢያ ለ 1,500 ሰዎች የመጠጥ ውሃ ዋስትና እንደሚሰጥ ታውቋል። ውሃ እንዳይባክን ወደ ማጠራቀሚያው እንዲፈስ መንገድ በማዘጋጀት ከተጠራቀመው በኋላም እንስሳቱ እንዲጠጡ በማድረግ፣ የአካባቢውን እውነታዎች በማጤን ፕሮጀክቶቹን የሚከታተል የራሱ ሠራተኞች ባይኖሩትም ሃላፊነትን ለሚስዮናውያን፣ ለበጎ አድራጊ ድርጅት እና ለአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሰጥ ታውቋል።

በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ስም የተገነባ የውሃ ጉድጓድ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በቫቲካን ካገኟቸው መካከል በቡርኪና ፋሶ የተንኮዶጎ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፕሮስፔር ኮንቲዬቦ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ከተገነቡት የንጹሕ ውሃ ማደያ ጣቢያዎች መካከል አንዱን በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ስም በማነጽ ለአካባቢው ነዋሪዎች በስጦታ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

የጤና እንክብካቤ ፕሮጀክቶች

በጤናው መስክ ከሚከናወኑ ፕሮጀክቶች መካከል በቡርኪና ፋሶ ውስጥ በ “ሄፐታይተስ ቢ” ላይ የሚደረግ የግንዛቤ ማስጨባጭ ሥራ እና የክትባት መርሃ ግብር፣ እንዲሁም በማላዊ ውስጥ በቺቺሪ ከተማ በሚገኝ እስር ቤት የሚካሄድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ እና የሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ማስወገጃ ተቋም ግንባታን የሚመለከት መሆኑ ታውቋል። ማኅበሩ በጣሊያን ውስጥ እ. አ. አ ከመጋቢት ወር 2020 ጀምሮ በነበረው ከፍተኛ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት፣ ቅዳሜንና እሁዶችን ጨምሮ በየቀኑ ከሰዓት በኋላ በስልክ የምክር እና የማነቃቂያ አገልግሎትን ሲሰጥ እንደነበር ታውቋል።

ለወጣቶች የትምህርት ፍላጎት ትኩረት መስጠት

በትምህርት መስክም እንደዚሁ የቅርብ ጊዜ ዕቅዶችን በማውጣት እ. አ. አ ከ 2018 - 2019 ባሉት ጊዜያት ውስጥ በማላዊ ብላንታየር ሀገረ ስብከት በሚገኝ የቺኩሊ ካቶሊክ ትምህርት ቤት የኬሚስትሪ እና ፊዚክስ የምርምር ማዕከልን ከ 400 በላይ ተማሪዎች ማስገንባቱ ታውቋል።

23 March 2022, 17:26