ፈልግ

በደቡብ ጣሊያን የሚገኝ የቅዱስ ፌርዲናንዶ የስደተኞች መቀበያ ማዕከል በደቡብ ጣሊያን የሚገኝ የቅዱስ ፌርዲናንዶ የስደተኞች መቀበያ ማዕከል   (ANSA)

በደቡብ ጣሊያን የሚገኝ አንድ የስደተኞች መጠለያ እንዲፈርስ መወሰኑ ተነገረ

በደቡብ ጣሊያን፣ ካላብሪያ ክፍለ ሀገር የሚገኝ የቅዱስ ፌርዲናንዶ የስደተኞች መቀበያ ማዕከል የሚፈርስ መሆኑን የክፍለ ሀገሩ አስተዳዳሪ አቶ ማሲሞ ማሪያኒ በትናንትናው ዕለት አስታወቁ። የስደተኞቹ መጠለያ ማዕከ በክፍለ አገሩ ውስጥ ጆያ ታውሮ ተብሎ በሚጠራ እርሻ ጣቢያ ተሰማርተው የሚሠሩ በርካታ ስደተኞች የሚኖሩበት ማዕከል እንደነበር ታውቋል። ስደተኞች ሠፈሩን እንዲለቁ የተደረገው መሬቱ በማን ይዞታነት እንደሚገኝ ባለመታወቁ፣ የሀገረ ስብከቱ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስደተኞቹ ሜዳ ላይ እንዳይወድቁ፣ ሰብዓዊ ክብራቸው እንዲጠበቅላቸው ጠይቃለች። በአካባቢው “ካሪታስ” የተባለ የካቶሊካዊት ቤተክስቲያን ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅት ተወካይ አቶ ኦሊቪዬሮ ፎርቲ፣ ምንም ባልተመቻቸበት ሁኔታ ስደተኞቹ አካባቢውን እንዲለቁ የሚደረግ ከሆነ ስደተኞቹ በከፍተኛ አደጋ እንደሚወድቁ አስጠንቅቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በደቡብ ጣሊያን ውስጥ ካላብሪያ ክፍለ ሀገር የሚገኝ የቅዱስ ፌርዲናንዶ የስደተኞች መቀበያ ማዕከል እንዲፈርስ ትዕዛዝ ቢተላለፍም፣ ጉዳዩ ገና መታየት እዳለበት፣ ስደተኞቹ የሚገቡበት ሌላ ምቹ መኖሪያ ማዕከል ለመገንባት የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ የካላብሪያ ክልል እየተወያየበት መሆኑ ታውቋል። ይህን ያስታወቁት በደቡብ ጣሊያን የሬጂዮ ካላብሪያ አስተዳዳሪ ማሲሞ ማሪያኒ ሲሆኑ፣ በክልሉ ከሚገኝ ቅዱስ ፌርዲናንዶ የስደተኞች መጠለያ ማዕከል፣ ከጆያ ታውሮ ማዘጋጃ ቤት እና ስደተኞችን ለመርዳት ከሚንቀሳቀሱ ማኅበራት ጋር ከተወያዩ በኋላ መሆኑ ታውቋል።

የካሪታስ እና የስደተኞች ተወካዮች

በአካባቢው የነበሩ አንዳንድ የስደተኞች መጠለያ ማዕከላት እንዲፈርሱ መወሰኑ በስደተኞች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ መምጣቱ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ታውቁል። የስደተኞች መጠለያዎች የነበሩባቸው ቦታዎች የማን ይዞታ እንደሆኑ በውል አለመታወቁን በጣሊያን ውስጥ የሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ማሳወቁ ታውቋል። መጠለያ ማዕከሉ ያለ መብራት እና ያለ ውሃ መመስረቱ ከዚህ በፊትም ሲያወዛግብ መቆየቱን የገለጸው ኮንፌዴሬሽኑ፣ የመኖሪያ ቤቶች መመዘኛዎችን፣ የመብራት እና የውሃ አገልግሎቶችን የማያሟላ፣ ለደህንነትም ዋስትና የማይሰጥ ሥፍራ መሆኑን አስታውቋል። መጠለያ ማዕከሉ ቢበዛ 300 ሰዎችን ብቻ ሊያስተናግድ የሚችል ቢሆንም እስካሁን ድረስ ከ350 ሰዎች በላይ ይኖሩበት እንደነበር፣ በመጠለያው ይኖሩ የነበሩ ስደተኞች ከአፍሪካ የመጡ፣ መደበኛ ባልሆነ የጉልበት ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ስደተኞች መሆናቸውን ኮንፌዴሬሽኑ አስታውቋል። ከሁለት ቀናት በፊት ሥፍራውን እንዲለቁ ወደ ተነገራቸው ስደተኞች ዘንድ ደርሰው ሁኔታውን የተገነዘቡት “ካሪታስ” የተሰኘ ካቶሊካዊ ዕርዳታ ሰጭ ድርጅት፣ በሀገረ ስብከቱ የሚገኝ የስደተኞች ፋውንዴሽን እንዲሁ ሁለት ብጹዓን ጳጳሳት ሞንሲኞር ጁሴፔ ሺላቺ እና ሞንሲኞር ፍራንቸስኮ ሚሊቶ፣ ስደተኞቹ “ተቀባይነት በሌለበት የሕይወት ደረጃ ላይ ይገኛሉ” በማለት ሁኔታውን አውግዘዋል። በአካባቢው ከሚኖሩት ስደተኞች ጋር ያላቸውን አጋርነት በመግለጽ የስደተኞችን ክብር ለማረጋገጥ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

ያልተመቻችይ የመኖሪያ ሥፍራዎች

ስደተኞቹ ይኖሩባቸው የነበሩ መጠለያዎችን መጠለያ ብሎ መጥራት አይቻልም ያሉት በጣሊያን ካቶሊካዊ እርዳታ ሰጭ ድርጅት ውስጥ የስደተኞች አገልግሎት መምሪያ ተጠሪ የሆኑት አቶ ኦሊቬሪ ፎርቲ፣ መጠለያ ማዕከሉ ለኑሮ ምቹ ካለመሆናቸው የተነሳ የስደተኞቹ ሕይወታቸው በከፍተኛ አደጋ ውስጥ የጣሉ መሆኑን ገልጸዋል። ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ በስደተኞቹ መጠለያዎች ላይ ምንም ዓይነት ተሻሽሎ ባለመደረጉ ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት መምጣቱን ገልጸው፣ ለተመለከተው ሁሉ ቦታው “የምድር ላይ ገሃነም ይመስላል” ብለዋል።

ፖለቲካዊ እና ተቋማዊ ኃላፊነቶች

የቅዱስ ፌርዲናንዶ የስደተኞች መጠለያ እውነታ ብቸኛው አይደለም ያሉት አቶ ኦሊቬሪ፣ በደቡብ ጣሊያን ካላብሪያ ክፍለ ሀገር እና በሌሎች ክልሎችም ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸው፣ በጣሊያን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች አስቸኳይ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ስለዚህ የሁኔታው ጭብጥ በካቶሊካዊ እርዳታ ሰጭ ድርጅት እና እንዲሁም በሌሎች አካላት ጣልቃ ገብነት ላይ የቆመ ሳይሆን ነገ ግን ፖለቲካዊ እና ተቋማዊ ኃላፊነት መጥፋት መሆኑን በግልጽ መመልከት ይቻላል ብለው፣ በአካባቢው ስደተኞችን በክብር ተቀብሎ በመልካም ሁኔታ የማስተናገድ ሥርዓት መጥፋት እና አማራጭ መፍትሄዎችን የማግኘት ችሎታ እንደሚጎድል ገልጸዋል።

አስተዋይ ሸማቾች ያስፈልጋሉ

ያለማቋረጥ የእሳት ቃጠሎ የሚነሳበትን እና ሕይወት የሚጠፋበትን እንደ ቅዱስ ፌርዲናዶ ያሉ የሰደተኞች መጠለያ ካምፖችን በዝምታ መመልከት አንችልም” ያሉት የካቶሊካዊት ቤተክስቲያን ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅት ተወካይ አቶ ኦሊቪዬሮ ፎርቲ፣ በአካባቢው እንዲታይ የሚፈለገው ሰፊ የረጅም ጊዜ እቅድ እንደሆነ ገልጸው፣ ቢሮክራሲውን የሚያቃልል፣ ከአካባቢው የንግድ ድርጅቶች ጋር የሚወያይ፣ ስደተኞች በሚኖሩባቸው ማኅበረሰቦች ውስጥ በመረጃ የተደገፈ የፍጆታ ዕቃዎች ግብይት ሃላፊነት እንዲኖር ጠይቀዋል።

27 January 2022, 16:10