ፈልግ

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በሕክምና ዕርዳታ አገልግሎት ላይ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በሕክምና ዕርዳታ አገልግሎት ላይ 

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ሃምሳ ዓመት የሕክምና አገልግሎቱን አስታወሰ

በፈረንሳይ አገር በሕክምና ባለሞያዎች እና ጋዜጠኞች ኅብረት እ. አ. አ ታኅሳስ 22/1971 ዓ. ም. የተቋቋመው ድንበር የለሽ የሕክምና ቡድን ላለፉት ሃምሳ ዓመታት እጅግ አስቸጋሪ በተባሉት የዓለማችን ክፍሎች አገልግሎት ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውሷል። ጾታ፣ ዘር፣ ቋንቋ፣ ሐይማኖት፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን ሳይመለከት በሰማንያ ስምንት አገራት ውስጥ ስልሳ አምስት ሠራተኞችን አሰማርቶ የሕክምና አገልግሎቱን ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወስል። የሐኪሞች ቡድኑ ያለፈው ዓመት ብቻ ወደ ዘጠኝ መቶ ሺህ ለሚጠጉ ሕሙማን የሕክምና አገልግሎት መስጠቱ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን የሕክምና አገልግሎትን ያገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሕሙማን፣ በጦርነት እና በአመጽ፣ በተላላፊ በሽታዎች፣ በተፈጥሮ አደጋዎች የተጠቁት እና የሕክምና አገልግሎትን የተነፈጉ መሆናቸው ታውቋል። ለትርፍ ያልተቋቋመ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በዛሬው ዕለት 50ኛ ዓመቱን ያከበረ ሲሆን በ88 አገሮች ውስጥ የዘር፣ የሃይማኖት እና የፖለቲካ ልዩነት ሳያደርግ፣ በአደጋ ውስጥ ለሚገኙ፣ የተፈጥሮ እና ሰው ሰው ሠራሽ አደጋዎች ሰለባ ለሆኑ ሕዝቦች የሕክምና ዕርዳታ ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል።

ባለፈው ዓመት የአውሮፓዊያኑ ዓመት 65,000 ሐኪሞችን በማሳተፍ ወደ 10 ሚሊዮን ለሚጠጉ ተመላላሽ ታካሚዎች የምክር አገልግሎትን እና ለ112,000 የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጠቂዎች ዕርዳታን ማድረጉ ሲነገር፣ ለ877,300 ታካሚዎች የሆስፒታል ውስጥ ዕርዳታን መስጠቱ ታውቋል። ይህ ለትርፍ ያልተቋቋመ የግል ድርጅት በ23 ዋና ዋና ብሔራዊ መሥሪያ ቤቶቹ እና በ9 ድርጅቶቹ አማካይነት ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን፣ የሕክምና ምርምሮችን ላካሄድ፣ የገንዘብ ዕርዳታዎችን ለማሰባሰብ፣ የሕክምና መሣሪያዎች ለአስተዳደር፣ በሰብዓዊ እና ማኅበራዊ እርምጃዎች ላይ ምርምሮችን ለማካሄድ፣ እ. አ. አ ታኅሳስ 22 ቀን 1971 ዓ. ም. በፈረንሳይ አገር የተመሠረተ ድርጅት መሆኑ ታውቋል። በሕክምና ዶክተሮች እና በጋዜጠኞች ቡድን ተነሳሽነት የድንገተኛ ጊዜ ሕክምና ዕርዳታን በፍጥነት፣ በብቃት እና በገለልተኝነት ለማቅረብ ዓላማ ያለው መሆኑ ታውቋል።  

ይህን ዓላማ ለማሳካት የሕክምና ዶክተሮችን፣ ነርሶችን እና ጋዜጠኞችን ጨምሮ 300 በጎ ፈቃደኞች፣ ሕይወትን ለማዳን፣ ለመፈወስ እና ሪፖርት ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል። ዋና ዓላማቸው የሕክምና ፍላጎቶችን የአገር ድንበር ሳያግዳቸው፣ አገልግሎቱ መቅረት አለበት ብሎ በሚያምንባቸው አካባቢዎች ያለ ምንም ልዩነት ለሰው ልጅ በሙሉ የጤና እንክብካቤን ለማረጋገጥ መቋቋሙ ታውቋል።

ተልእኮዎቹ

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በ50 ዓመታት ሰብዓዊ ዕርዳታ ታሪኩ የግማሽ ክፍለ ዘመን በሕክምናው ዘርፍ የጤና አገልግሎቱን ሲያቀርብ መቆየቱ ሲታወስ የመጀመሪያው ተልዕኮን ያካሄደው እ. አ. አ በ1972 በመሬት መንቀጥቀጥ 5,000 ሰዎች በሞቱባት፣ 20,000 ሰዎች በቆሰሉባት እና 250,000 ሰዎች ቤት አልባ በሆኑባት የመካከለኛው ላቲን አሜሪካ አገር ኒካራጓ ላይ የሕክምና ዕርዳታን በማድረግ መሆኑ ይታወሳል።  በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ውስጥም እንቅስቃሴውን በማሳደግ በዩጎዝላቪያ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት፣ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ኤች አይ ቪ እና ወባን በመዋጋት፣ በጣሊያን ላምፔዱዛ ግዛት ስደተኞችን በመቀበል፣ በጦርነትና በግጭቶች ወቅት በኢራቅ በመገኘት፣ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ በደረሰባት ኢትዮጵያ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት በሥፍራው መገኘቱ ይታወሳል። በአፍጋኒስታን እና በስሪላንካ እንዲሁም በሶርያ እና በየመን የሕክምና አገልግሎቶችን ማድረጉ ይታወሳል። እ. አ. አ. በ 1999 የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸላሚ እንደነበር ሲታወስ፣ በተለያዩ አህጉራት ለሚያደርጋቸው ፈር ቀዳጅ ሰብዓዊ ሥራዎች እውቅናን ማግኘቱ ይታወሳል።

22 December 2021, 13:44