በእንግሊዝ ግላስጎው የተካሄደ የአየር ንብረት ለውጥ ሰላማዊ ሰልፍ በእንግሊዝ ግላስጎው የተካሄደ የአየር ንብረት ለውጥ ሰላማዊ ሰልፍ 

የዓለም ባንክ፣ ለአየር ንብረት በዓመት 25 ቢሊዮን ዶላር ለመመደብ ዕቅድ እንዳለው ገለጸ

በእንግሊዝ ግላስጎው ከተማ የአየር ንብረት ለውጥን በማስመልከት ከጥቅምት 21 - ኅዳር 3/2014 ዓ. ም. በመካሄድ ላይ በሚገኝ 26ኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ላይ የዓለም ባንክ ሪፖርት ማቅረቡ ታውቋል። የገንዘብ ተቋሙ በሪፖርቱ እንደገለጸው እ. አ. አ እስከ 2025 ዓ. ም. ድረስ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚፈሰውን መዋዕለ ንዋይ ለማሳደግ ዕቅድ እንዳለው ገልጿል። ይህ በእንዲህ እንዳለ “ሕጻናትን አድን” የተሰኘ የዕርዳታ ድርጅት በበኩሉ፣ በትውልድ መካከል ወደፊት ሁሉን በሚጠቅም የጋራ አገልግሎት ላይ ትብብር እንዲደረግ በማለት ጥሪ አቅርቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በእንግሊዝ ግላስጎው ከተማ፣ የአየር ንብረት ለውጥን በማስመልከት ከጥቅምት 21 - ኅዳር 3/2014 ዓ. ም. 26ኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ በመካሄድ ላይ መሆኑ ታውቋል። በጉባኤው ላይ ሪፖርት ካቀረቡት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የዓለም ባንክ፣ ለአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በዓመት 25 ቢሊዮን ዶላር ለማውጣት ዕቅድ እንዳለው በድርጊት መርሃ ግብሩ አስታውቋል። መርሃ ግብሩ የግብርና እና የምግብ ዘርፍን የሚያካትት መሆኑን አክሎ አስታውቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአየር ንብረት ተሟጋቿ ግሬታ ቱምበርግ የተመራ የአካባቢ ተቆርቋሪ ወጣቶች ሰልፍ፣ በአየር ንብረት ላይ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጉባኤ ውጤታማ እንደማይሆን ያለውን እምነት ገልጿል። የአየር ንብረት ተሟጋቿ ግሬታ ቱምበርግ በንግግሯ፣ የጋራ መኖሪያ ምድራችን በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ እንደወደቀች ገልጻ፣ በዚህ ሳቢያ በማደግ ላይ የሚገኙ ድሃ አገሮች የበለጠ ጉዳት የሚደርስባቸው መሆኑን ገልጻ፣ ሃብታም አገሮች ለድሃ አገሮች የሚያደርጉት ዕርዳታ በቂ አለመሆኑን አስረድታለች። በዚህ ጉዳይ ላይ የአየር ንብረት ጉባኤ የአሜሪካው ተወካይ ክቡር አቶ ጆን ኬሪ እ. አ. አ እስከ 2022 ዓ. ም. ማብቂያ ድረስ የአንድ መቶ ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ እንዲለቀቅ በማለት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። ሰልፈኞቹ አክለውም በኤኮኖሚ የበለጸጉ አገሮች ታዳጊ አገራትን ለማገዝ የገቡት ቃል ባዶ እንዳሆን እና በተጨማሪም የምድራችን ሙቀት መጠን ከ 1.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች ለማድረግ የወሰዱትን እርምጃ በፍጥነት ተግባራዊ እንዲያደርጉት ጠይቀዋል።    

የአየር ንብረት ለውጥ የትውልዶች የጋራ ጉዳይ ነው

ለጋራ መኖሪያ ምድራችን የሚደረግ እንክብካቤ ሁሉን ትውልዶች የሚመለከት፣ በተለይም የወጣቶችን አስተዋፅኦ የሚጠይቅ መሆን እንዳለበት “ሕጻናትን አድን” የዕርዳታ ድርጅት አስታውቋል። “የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በሚካሄድበት ግላስጎው ከተማ በርካታ ህጻናት እና ወጣቶች ተገኝተው ድምፃቸውን ማሰማታቸው ምንም አያስደንቅም” በማለት ‘በሕጻናት አድን’ ድርጅት የሕጻናት ድህነት እና የአየር ንብረት ለውጥ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ወ/ሮ ዮላንዴ ራይት ተናግሯል። ዋና ሥራ አስኪያጇ አክለውም፣ የአየር ንብረት ጉባኤው ምንም እንኳን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁሉን የሚያካትት እንደሚሆን ቃል ቢገባም ፣ እንደ ወጣት የአየር ንብረት ተሟጋቾች ገለፃ መሠረት እውነታው ፍጹም ተቃራኒ መሆኑን ገልጸዋል።

በአካባቢ ጥበቃም ቢሆን ዓለም አቀፋዊ አለመመጣጠን አለ

በአየር ንብረት ቀውስ፣ የህጻናትን እና የወጣቶችን ድምጽ አለማዳመጥ፣ እንዲሁም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ላይም የሚታየው ያልተመጣጠነ የክትባት ስርጭት በዓለም ዙሪያ ወረርሽኙ በተለያየ ፍጥነት እንዲሰራጭ ማድረጉን ወ/ሮ ዮላንዴ ራይት ገልጸዋል። ዋና ሥራ አስኪያጇ በማከልም፣ በግላስጎው የሚገኙ በርካታ ወጣት የአየር ንብረት ተሟጋቾች ለ “ሕጻናት አድን” የዕርዳታ ድርጅት ባሰሙት ድምጽ፣ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት የመጡ ህጻናት የበታችነት እና የመድልዎ ሰለባ በመሆን ከድርድሩ እንደተገለሉ መናገራቸውን ወ/ሮ ዮላንዴ ራይት አስታውቀዋል። ወ/ሮ ራይት ንግግራቸውን ሲኣያጠቃልሉ፣ በአሁኑ ጊዜ የካርቦን ጋዝ ልቀት ተጠያቂ የሆኑት አገራት የምድራችንን ሙቀት መጠን ከ 1.5 ዲግሪ ሴቲግሬድ በታች ለመገደብ ሥር ነቀል እርምጃን ወስደው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

08 November 2021, 14:23