የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለ ድርቅ የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለ ድርቅ 

በመካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ አገሮች የታየው የውሃ እጥረት ሕጻናትን ለአደጋ ማጋለጡ ተገለጸ

ዓለም አቀፍ የውሃ ሳምንት ምክንያት በማድረግ በቅርቡ ይፋ የወጣው የተባበሩት መንግሥታት ሕጻናት መርጃ ድርጅት ሪፖርት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሰሜን አፍሪካ አገሮች የታየው የውሃ እጥረት ሕጻናትን ላይ አደጋ መጣሉን በማስጠንቀቂያው አስታውቋል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚታይ የውሃ እጥረት ከ10 ሕጻናት መካከል በዘጠኙ ላይ የጤና መቃወስን እና የዕድገት እንቅፋቶችን በማስከተል ለከፍተኛ ውጥረት መዳረጉን አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዘንድሮ ከነሐሴ 17-21/2013 ዓ. ም. ድረስ ለአምስት ቀናት የሚቆየው ዓለም አቀፍ የውሃ ሳምንት፣ እያንዳንዱ ሰው ከተፈጥሮ ሃብት ጋር በተለይም ከውሃ ጋር ያለውን ግንኙነት ጠንቅቆ እንዲያውቅ ዕድል የሚሰጥ፣ እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንደሚቻል የውይይት መድረኮችን ያመቻቸ እና ዘላቂነት ያለውን እንክብካቤ ለማድረግ ሃሳቦችን የሚያቀርብ መሆኑ ታውቋል። የአየር ንብረት ለውጥ ለሰደድ እሳት ፣ ለመሬት መንቀጥቀጥ እና ለባሕር መናወጥ እና ለሌሎች በርካታ የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በሆነበት ባሁኑ ወቅት፣ ዘንድሮ ለሚከበርው ዓለም አቀፍ የውሃ ሳምንት መሪ ቃል እንዲሆን የተመረጠው ርዕሥ፣ “የአደጋው መቋቋሚያ አቅም በፍጥነት ይገንባ” የሚል መሆኑ ታውቋል። በዚህ መሪ ርዕሥ በመታገዝ፣ የኮቪድ-19 ወረሽኝን ጨምሮ ሌሎችንም አደጋዎች መቋቋም እንዲቻል ዘንድሮ የተከበረው ዓለም አቀፍ የውሃ ሳምንት መልዕክት አሳስቧል።

የመካከለኛው ምሥራቅ እና የሰሜን አፍሪካ አገሮች የውሃ እጥረት

በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሰሜን አፍሪካ አገሮች ውስጥ የሚታየው የውሃ እጥረት በሺህዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የዘለቀ መሆኑን ያስታወሰው የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ሪፖርት፣ የዚህ ቀውስ ተፅእኖ በአሁኑ ጊዜ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ በሕፃናት ህልውና ላይ አደጋ መደቀኑን አመልክቶ፣ የጤና መቃወስን እና የዕድገት እንቅፋቶችን በማስከተል ለከፍተኛ ውጥረት የዳረጋቸው መሆኑን አስታውቋል።

በውሃ እጥረት የተጎዱ ሕጻናት

ሪፖርቱ አክሎም በእነዚህ ሁለት አካባቢዎች የታየው የውሃ እጥረት፣ ረሃብን፣ የእርስ በእርስ አመጽን፣ ሕጻናትን ጨምሮ ድሃ ቤተሰቦችን እንዲፈናቀሉ በማድረግ ለስደት እና ከማኅበረሰቡ በማግለል ለከፍተኛ ችግር መዳረጉን አስታውቋል። በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት፣ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የሰሜን አፍሪካ አካባቢዎች ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት አቶ ቤርናርድ ባይንቬል፣ በእነዚህ አካባቢዎች የሚታየው የውሃ እጥረት፣ ሕጻናትን ጨምሮ በርካታ ቤተሰቦችን ለጤና መጓደል የዳረጋቸው መሆኑን አረጋግጠው፣ ከዚህም በላይ ለአመጽ እና ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ ያደረጋቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የውሃ እጥረትን የሚያስከትሉ ምክንያቶች

“በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ ውስጥ የውሃ እጥረት በልጆች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ” በሚል ርዕሥ ይፋ የሆነው በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ሪፖርት፣ የውሃ እጥረትን ካስከተሉት ምክንያቶች መካከል የከተሞች መስፋፋት፣ ደካማ የውሃ አያያዝ ፣ እና የአየር ንብረት ለውጥ መሆናቸውን አስታውቆ፣ እንደ ሶሪያ ፣ የመን እና ሱዳን ባሉት አገሮች ውስጥ ለውሃ እጥረት አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ተጨማሪ ምክንያቶች አንዱ ግጭት እንደሆነ የገለጸው ሪፖርቱ “ግጭቶች እና የክልል ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች፣ የጭነት መጓጓዣን ጨምሮ አስቸኳይ የውሃ አቅርቦት ጥያቄን እንደጨመረ እና ይህም የከርሰ ምድር ውሃ መሟጠጥን ያባባሰው መሆኑን አስረድቷል። 

  የውሃ እጥረትን ለመዋጋት የጋራ ጥረት ይደረግ

የውሃ እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣበት ባሁኑ ወቅት፣ በተባበሩት መንግሥታት ሕጻናት መርጃ ድርጅት በየአገራቱ ለሚገኙ ተባባሪ ድርጅቶች፣ ለመንግሥታት እና ሲቪል ማኅበረሰብ የሚያደርገውን እገዛ በማሳደግ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሰሜን አፍሪካ አገሮች የሚታየውን የውሃ ሀብቶች ተጋላጭነት ለመቅረፍ ጥረት እያደርገ መሆኑ ታውቋል። የሕጻናት መርጃ ድርጅቱ ጥረት እያንዳንዱ ሰው ንጹሕ የመጠጥ ውሃን እና የጤና አገልግሎቶችን የማግኘት መብትን ማስከበር፣ ግጭቶችን ማስወገድ፣ የውሃ እጥረት የሚያስከትላቸውን ችግሮች በማስረዳት፣ ወጣቶች ጨምሮ የማኅበረሰብ ተወካዮች ለውሃ ትኩረትን በመስጠት ጥበቃን እንዲያደርጉ በማሳሰብ ላይ መሆኑ ታውቋል።

የዓለም የውሃ ሳምንት

ዓለም አቀፍ የውሃ ሳምንት በስዊድን ስቶክሆልም እ. አ. አ 1991 ዓ. ም መጀመሩ ሲታወቅ፣ ተማሪዎችን፣ የፖለቲካ ባለ ሥልጣናትን፣ የንግድ ተቋማት ተወካዮችን እና የሳይንስ ተመራማሪዎች በማሰባሰብ በየዓመቱ ተግባራዊ የሚሆኑ ግንዛቤዎችን በማስጨበጥ ትክክለኛ ውሳኔዎች እና ፖሊሲዎች እንዲረቀቁ የሚያደርግ መሆኑ ይታወቃል።           

26 August 2021, 16:35