በአፍጋኒስታን ውስጥ የሚካሄድ ግጭት ያስከተለው መፈናቀል በአፍጋኒስታን ውስጥ የሚካሄድ ግጭት ያስከተለው መፈናቀል 

በርካታ ሕጻናት ለውትድርና አገልግሎት የሚመለመሉ መሆናቸው ተነገረ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ለጸጥታው ምክር ቤት ባቀረቡት አዲስ ሪፖርት እ. አ. አ 2020 ዓ. ም ለውትድርና አገልግሎት የተመለመሉት ሕጻንት ቁጥር ከ8,500 በላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሰኞ ሰኔ 14/2013 ዓ. ም ለጸጥታው ምክር ቤት ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት በዓለማችን ዙሪያ በተከሰቱት አመጾች እና ጦርነቶች በውትድርና አገልግሎት የተመለመሉት ሕጻናት ቁጥር ከ8,500 በላይ መሆኑን ገልጸው ከእነዚህ መካከል የተገደሉት ወደ 2,700 የሚጠጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ከፍተኛ የመብት ጥሰት

ዓመታዊው የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት በሕጻናት ላይ የሚፈጸመውን የመብት ጥሰት ሲተነትን በሕጻናት ላይ ግድያ፣ የአካል ማጉደል፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ አፈና፣ አስገዳጅ ምልመላ እና የዕርዳታ አቅርቦት መከልከል የሚደርስባቸው መሆኑን አስታውቋል። የሪፖርቱ ግኝቶች በ19,379 ሕጻናት ላይ የመብት ጥሰት የተፈጸመባቸው መሆኑን አረጋግጧል። እ. አ. አ በ2020 ዓ. ም ውስጥ አብዛኛዎቹ የሕጻናት መብት ጥሰቶች የታዩባቸው አገራትም ሶማሊያ፣ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ፣ አፍጋኒስታን፣ ሶሪያ እና የመን መሆናቸውን ሪፖርቱ አስታውቋል።

ሪፖርቱ አክሎም በትምህርት ቤቶች እና በሆስፒታሎች ላይ በደረሰው ከፍተኛ ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው ሕጻናት ቁጥር ብዙ መሆኑን አስታውቆ ጥቃት ከተፈጸመባቸው ሕጻናት ቁጥር አንድ አራተኛው ሴት ሕጻናት መሆናቸውን አስታውቆ በእነዚህ ሴት ሕጻናት ላይ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ጾታዊ ጥቃቶች የደረሱባቸው መሆኑን አስታውቋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓመታዊ ሪፖርት ላይ ማብራሪያን የሰጡት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ልዩ ተወካይ እና የሕጻናትን የጦር መሣሪያ ትጥቅ እና ግጭቶች መርማሪ ወ/ሮ ቬርጂኒያ ጋምባ በዓለማችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱ ጦርነቶች እና አመጾች በ2020 የአውሮፓዊያኑ ዓመት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕጻናት፣ ወንዶች እና ሴቶች የሕጻንነት ጊዜያቸውን በከንቱ አባክኖባቸዋል ብለዋል። ይህም ለሕጻናቱ እና ለሚኖርሩበት ማኅበረሰብ ጉዳት፣ ለዘላቂ ሰላም ጥረት እንቅፋት ከመሆኑም በላይ የሰላም ዕድሎችን ያሚያጨልም መሆኑን አስረድተዋል።

የታዩ መልካም ዕድገቶች

ምንም እንኳን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስደንጋጭ አኃዛዊ መረጃዎችን ይፋ ቢያደርግም አመጾች በሚካሄድባቸው አገራት እነርሱም አፍጋኒስታን፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፑቢሊክ፣ ናይጄሪያ፣ ፊሊፒን፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶርያ ከሚገኙት የጦር አዛዦች ጋር በተደረገው ውይይት መልካም ለውጦች መታየታቸው ታውቋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በጦር መሪዎች መካከል በተደረገው ውይይት ከ12,643 ሕጻናት ከጦር ግንባር ተመልሰው ከወላጆቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ መደረጉ ታውቋል። ሪፖርቱ አክሎ የሕጻናትን መብት ለማስጠበቅ የሚደረግ ጥረት መልካም ውጤቶችን ቢያሳይም ረጅም ጊዜን የሚወስድ እና ዝቅተኛ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገ መሆኑን አስታውቋል።

ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እ. አ. አ በ2016 ዓ. ም የሕጻናትን ጉዳይ በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት የሕጻናትን ሰብዓዊ መብት ለማስከበር እና ባርነትን ለማስቀረት የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ያስፈልጋል ማለታቸ ይታወሳል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስችስ ሰኔ 6/2013 ዓ. ም በሕጻናት ላይ የሚደርስ የጉልበት ብዝበዛን የሚቃወም ዓለም አቀፍ ቀንን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክታቸው በሕጻናት ላይ የሚፈጸም የጉልበት ብዝበዛ ሕጻናት የልጅነት ጊዜያቸውን በደስታ እንዳያሳልፉ የሚደረጉ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ሕጻናት ስለ ወደፊት ሕይወታቸው እንዳያስቡ እና በራስ የመተማመን አቅም እንዳይኖራቸው ያደርጋል ብለዋል። የሕጻናት የወደ ፊት ሕይወት ተስፋ መጨለም የለበትም በማለት ባስተላለፉት የዘንድሮ መልዕክታቸው፣ በሕጻናት ማኅበራዊ አገልግሎት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ተቋማት ሕጻናት ከሚደርስባቸው ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች የሚወጡበትን መንገድ እንዲያመቻቹ በማለት መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።       

23 June 2021, 16:23