በአየር ንብረት ለውጡ ምክንያት የተከሰተው የውሃ እጥረት በአየር ንብረት ለውጡ ምክንያት የተከሰተው የውሃ እጥረት 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምድር ሙቀት መጨመር የሰውን ልጅ ለአደጋ ማጋለጡን አስታወቀ

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የምድራችን ሙቀት መጠን እየጨመረ መምጣቱን ከልዩ ልዩ መንግሥታት የተወጣጡ የተመራማሪ ቡድን አስታውቋል። በተከሰተው ከፍተኛ ሙቀት ሊጠቁ የሚችሉ የዓላማችን ሕዝቦች ቁጥር 420 ሚሊዮን የሚደረስ መሆኑን ቡድኑ የገለጸ ሲሆን፣ የግሪንአኮርድ ተመራማሪ ቡድኑ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ አንድሬያ ማሱሎ፣ ወደ ፊት ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ከወዲሁ ለመከላከል የመፍትሄ ሃሳቦችን ማግኘት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአየር ንብረት ለውጡ ምክንያት በዓለማችን ውስጥ የውሃ እጥረት፣ ስደት፣ ረሃብ፣ በሽታ፣ የእንስሳት እና የዕጽዋዕት ዝርያዎች ከምድር ገጽ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ሊጠፉ መቃረባቸውን የተመራማሪ ቡድኑ አስታውቋል። የምድራችን ሙቀት መጠን አሁን ከሚገኝበት 1.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ወደ ሁለት የሚያድግ ከሆነ በሰው ልጆች ሕይወት ላይ የማይቀለበስ ተጽዕኖን ሊያከትል እንደሚችል የፓሪስ ስምምነት ማስጠንቀቁ ይታወሳል። በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት 420 ሚሊዮን ሰዎች በከፍተኛ ሙቀት የሚጠቁ ሲሆን 80 ሚሊዮን የሚሆኑ ደግሞ በከፍተኛ የረሃብ አደጋ የሚጎዱ መሆናቸው ተገልጿል።

መወሰድ ያለበት ምርጫ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንዳስተወቀው፣ በመጨረሻዎቹ ዓመታት ውስጥ የታየው የአየር ንብረት ለውጥ የሰውን ልጅ ለከፍተኛ አደጋ የዳረገው መሆኑን ገልጾ አደጋው እ. አ. አ ከ2050 ዓ. ም በፊት እጅግ ጎልቶ የሚታይ መሆኑን አስታውቋል። በምድራችን ሙቀት መጨመር ይበልጥ የሚጎዱት የእስያ እና የአፍሪካ አህጉራት መሆናቸውን ሪፖርቱ አስታውቆ በሚቀጥሉት ሰላሳ ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሚወሰዱ የፖለቲካ ውሳኔዎች ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን አክሎ አስታውቋል። የምድራችን አየር አሁን ከሚገኝበት ወደ ተሻለ ደረጃ ቢሸጋገር በውስጡ የሚገኙ ፍጥረታት በአዲስ መልክ እንደገና መንሰራራት የሚችሉ ሲሆን የሰው ልጅ ግን ይህ ዕድል የሌለው መሆኑን ጥናቶች አመልክተዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በምድራችን ላይ በተከሰተው የሙቀት መጠን ጥናቱን ያካሄደው መርማሪ ቡድን ጠቅላላ ሪፖርቱን እ. አ. አ ከሚቀጥለው የካቲት ወር በፊት ይፋ የማያደርግ መሆኑን የግሪንአኮርድ ተመራማሪ ቡድኑ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ አንድሬያ ማሱሎ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል። ይፋ ለማድረግም በ195 አባል አገራት የጋራ ስምምነት መጽደቅ እንዳለበት ፕሬዚደንቱ አክለው አስታውቀዋል። የግሪንአኮርድ ተመራማሪ ቡድኑ አጉዳዩን አስከፊነት ከማሳሰብ ባሻገር ምንም ሊያደርግ የማይችል መሆኑን አስረድተው፣ የአደጋው አስከፊነት ከሰላሳ ዓመታት ወዲህ ሲነገር የቆየ ቢሆንም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት የተወሰዱ እርምጃዎች እምብዛም ለውጥ ያላስገኙ መሆናቸውን አስረድተው ጊዜ እየጨመረ በሄደ ቁጥር አደጋውን ለመግታት የሚያስችል አቅም ዝቅተኛ ይሆናል ብለዋል።

አዳዲስ ሃሳቦችን ማምጣት እና የቅሪተ አካል ምንጮችን መተው

የግሪንአኮርድ ተመራማሪ ቡድኑ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ አንድሬያ ማሱሎ በገለጻቸው በምድራችን ውስጥ በሰው ሕይወት ላይ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ለመከላከል አዳዲስ ሃሳቦችን ማፍለቅ እንደሚገባ አሳስበው፣ የቆዩ የዕድገት ሞዴሎችን ዛሬ ላይ ለመጠቀም መሞከር ጉዳትን እንጂ መልካም ውጤትን ማምጣት የማይቻል መሆኑን አስረድተዋል። ዛሬም ቢሆን የቅሪተ አካል ምንጮችን ለመጠቀም መሞከሩ ወደ አደጋ የሚመራ እንጂ ውጤት እንደሌለው ክቡር አቶ አንድሬያ ማሱሎ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልል አስረድተዋል።   

ሰፋፊ ከተሞችን ሊያጋጥም የሚችል አደጋ

በእስያ እና በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ትላልቅ ከተሞች ለከፍተኛ የአየር ሙቀት የሚጋለጡ ከሆነ ሌሎች አካባቢዎችም እንደዚሁ ለተመሳሳይ አደጋ የሚጋለጡ መሆናቸው ክቡር አቶ አንድሬያ ማሱሎ ገልጸው አደጋውን ከሚያስከትሉ ክስተቶች መካከል አንዱ የሕዝብ መጨመር ምሆኑን አስረድተው ሊወሰድ የሚገባ እርምጃ እነዚህ ሰፋፊ ከተሞች የሙቀት መጠናቸውን ለመቀነስ የሚያግዙ የሕንጻ እና የመንገድ አሰራር መንገዶችን መከተል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ከዚህም በተጨማሪ በከተሞች አካባቢ የዛፍ ችግኞችን በመትከል የምድር ሙቀት መጠን መቀነስ የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል።     

24 June 2021, 16:36