ተማሪዎች በአፍሪካ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በአፍሪካ ትምህርት ቤት 

በአፍሪካ ውስጥ ትምህርት መብት እንጂ እንደ ዕድል መቆጠር የለበትም ተባለ

በደቡብ አፍሪካዊቷ ስዌቶ ከተማ እ. አ. አ በ1976 ዓ. ም በወጣቶች ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ በየዓመቱ ሰኔ 9 ቀን ሲታውስ መቆየቱ ይታወቃል። ትናንት ሰኔ 9/2013 ዓ. ም ታስቦ የዋለውን ዕለት ምክንያት በማድረግ የአፍሪካ ጉዳዮች አጥኚ የሆኑት ወ/ሮ ሐና ፖዚ፣ በአህጉሪቱ ውስጥ ካለፈው ዘመን ይልቅ ዛሬ በርካታ ጠቃሚ እርምጃዎች የተወስዱ ቢሆንም መሠራት ያለባቸው ብዙ ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ትናንት ሰኔ 9/2013 ዓ. ም “የአፍሪካ ሕጻናት ቀን” ታስቦ መዋሉ ታውቋል። በደቡብ አፍሪካ በነበረው የአፓርታይድ ሥርዓት፣  በአገሪቱ ለጥቁር ተማሪዎች የሚሰጠውን ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ በመቃወም በስዌቶ ከተማ እ. አ. አ በ1976 ዓ. ም አደባባይ በወጡት ወጣቶች ላይ ጭፍጨፋ መካሄዱ ይታወሳል። የወጣቶቹ ጥያቄ በተጨማሪም ትምህርቱ በቋንቋችን ይሰጥ የሚል መሆኑ ይታወሳል። አገዛዙ እነዚህን ጥያቄዎች ያነሱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንድ እና ሴት ተማሪዎች እንዲጨፈጨፉ ትዕዛዝ ማስተላለፉ ይታወሳል። ለሁለት ሳምንታት የተካሄደው ጭፍጨፋ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን  ለመቁሰል አደጋ እና ቢያንስ መቶ የሚሆኑትን ለሞት የዳረጋቸው ይታወሳል። ይህን አስከፊ ክስተት ለማስታወስ የፍሪካ አንድነት ድረጅት በኋላም የተባበሩት መንግሥታ ድርጅት እ. አ. አ ከ1991 ዓ. ም ጀምሮ ሰኔ 9 ቀን “የአፍሪካ ሕጻናት ቀን” ታስቦ እንዲውል በማለት መወሰናቸው ይታወሳል። በዚህ መሠረት “የአፍሪካ ሕጻናት ቀን” ዘንድሮ ለ31ኛ ጊዜ ታስቦ መዋሉ ታውቋል።

የመማር መብት ተከብሮ አያውቅም ነበር

በደቡብ አፍሪካ ውስጥ እ. አ. አ በ1976 ዓ. ም ወጣቶች እንዲከበርላቸው የጠየቁት የመማር መብት ጥያቄ ዛሬም በበርካታ የአፍሪካ አገሮች ዘንድ ምላሽ አለማግኘቱን፣ የአፍሪካ ጉዳዮች አጥኚ ወ/ሮ ሐና ፖዚ፣ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል። ወ/ሮ ሐና ፖዚ በቃለ ምልልሳቸው እንደገለጹት በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ካለፈው ዘመን ይልቅ ዛሬ በርካታ ጠቃሚ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸው፣ ከእነዚህም መካከል በአገሪቱ ለሚነገሩ 11 ኦፊሴላዊ ቋንቋዎች ዕውቅና የተሰጣቸው መሆኑን ወ/ሮ ሐና ገልጸው፣ በአህጉሪቱ ውስጥ የመማር መብት ዋና ጉዳይ እንጂ እንደ ዕድል መቆጠር የለበትም ብለዋል።   

ኮቪድ-29 ያስከተለው ቀውስ

“የአፍሪካ ሕጻናት ቀን” የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተዛመተ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ ታስቦ መዋሉን ያስታወቁት ወ/ሮ ሐና፣ ወረርሽኙ በአህጉሪቱ ከፍተኛ ዋጋን ማስከፈሉን ገልጸው ይህም በጤናው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በትምህርት እና በኤኮኖሚ ዘርፍም መሆኑን አስረድተዋል። ወ/ሮ ሐና አክለውም የሕክምና አገልግሎት ማነስ የታየው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የበሽታ ዓይነቶች መታየቱን አስረድተዋል። በዚህም ምክንያት በወባ፣ ሳንባ ምች እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚሞቱት ሕጻናት ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። ኡጋንዳን እንደ ምሳሌ የጠቀሱት ወ/ሮ ሐና ፖዚ፣ በኡጋንዳ ውስጥ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን እና ለተማሪዎች የሚታደል ምግብ መቁረጡን አስታውሰው፣ ለአንንድ ተማሪ በትምህርት ቤት የሚታደል ምግብ መቋረጥ ለከፍተኛ ችግር የሚያጋልጥ መሆኑን አስረድተዋል።

የግዳጅ ጋብቻዎች መጨመር

በአፍሪካ ውስጥ በአንዳንድ አገሮች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የግዳጅ ጋብቻ ቁጥር መጨመሩን የገለጹት ወ/ሮ ሐና ፖዚ፣ ይህም ማኅበራዊ ችግሮችን ማስከተሉን ገልጸው በመጨረሻዎቹ ዓመታት የግዳጅ ጋብቻ ቁጥር መጨመሩን ተናግረዋል። በማላዊ ውስጥ ይህን ችግር በማስወገድ ሴቶች ትምህርታቸውን እንዲገፉበት የሚያበረታታ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል። በአፍሪካ ውስጥ ሴት ልጅን ማስተማር አንድ መንደርን፣ አንድ ማኅበረሰብን ወይም አንድ አገርን እንደ ማስተማር የሚቆጠር መሆኑን አስረድተዋል።

ትምህርት እና የሕጻናት የጉልበት ብዝበዛ

በቅርብ ሳምንታት ውስጥ የትምህርት መብትን አስመልክተው የተደረጉት ወቅታዊ ውይይቶች፣ በሕፃናት ላይ ቁጥሩ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የጉልበት ብዝበዛ መፈጸሙን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። እንደ ውይይቱ ገለጻ መሠረት ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ውስጥ በሕጻናት ላይ የሚፈጸም የጉልበት ብዝበዛ መጨመሩን ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት እና ዩኒሴፍ ይፋ ባደረጉት የ2020 ዓመታዊ ሪፖርት አስታውቀዋል። ሪፖርቱ እንዳመለከተው በዓለማችን ከጉልበታቸው በላይ በሆኑ የሥራ መስክ ተሰማርተው የሚገኙ ሕጻናት ቁጥር ወደ 160 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን እና ይህም ካለፉት ዓመታት ጋር ሲወዳደር 5% መጨመሩን አስታውቋል። ከሰሃራ በታች ባሉት አገራት ውስጥ በሕጻናት ላይ የሚፈጸም የጉልበት ብዝበዛ መጨመሩን ሪፖርቱ አስታውቋል።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጥሪ

በሕጻናት ላይ የሚደርስ የጉልበት ብዝበዛን በመቃወም ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሑድ ሰኔ 6/2013 ዓ. ም. ባስተላለፉት ጥሪ በሕጻናት ላይ የሚፈጸም የጉልበት ብዝበዛን በዝምታ መመልከት የልብንም ብለው፣ ሕጻናት በልጅነት ዕድሜአቸው የመጨወት፣ የመማር እና መልካምን የመመኘት መብታቸውን ማጣት የለባቸውም ብለዋል። እንደ ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ዓመታዊ ሪፖርት መሠረት ባሁኑ ጊዜ ከአቅማቸው በላይ በሆኑ የሥራ ዘርፎች ጉልበታቸውን እየተበዘበዙ የሚገኙት ሕጻናት ቁጥር ከ150 ሚሊዮን በላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ ይህ ቁጥር የስፔን፣ የፈረንሳይ እና የጣሊያን ነዋሪዎች ድምር ያህላል ብለው፣ “ይህንን የዘመናችንን ባርነት ለማስወገድ ሁላችንም ጥረታችንን በጋራ እናድስ” ብለዋል።  

17 June 2021, 16:28