ፈልግ

በአሜሪካ ውስጥ የቱልሳ ከተማ አፍሮ አሜሪካዊያን ነዋሪዎች በአሜሪካ ውስጥ የቱልሳ ከተማ አፍሮ አሜሪካዊያን ነዋሪዎች  

ጆ ባይደን በቱልሳ ከተማ በአፍሮ አሜሪካዊያን ላይ ጭፍጨፋ መፈጸሙን አረጋገጡ

ከመቶ ዓመታት በፊት ግንቦት 23 ቀን በአሜሪካ ውስጥ ቱልሳ በተባለች ከተማ የነጭ የበላይነት የሚያራምዱት በ300 አፍሮ አሜሪካውያን ላይ ጭፍጨፋ ማካሄዳቸው ይታወሳል። የአሜሪካዉ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ወደ ሥፍራው በመጓዝ ከከተማው ነዋሪዎች ጋር ሆነው ዕለቱን ማስተወሳቸው ታውቋል። አንድ የአሜሪካን ፕሬዚደንት ዕለቱን ለማስታወስ ወደ ሥፍራው ሲሄድ ጆ ባይደን የመጀመሪያ መሆናቸው ተዘግቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከመቶ ዓመታት በፊት በ300 አፍሮ አሜሪካዊያን ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ከዘረኝነት ጋር የተቆራኘ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ በጣም ከሚያሳዝኑ ታሪኮች መካከል አንዱ እንደሆነ ተነግሯል። በኦክላሆማ ግዛት ቱልሳ ከተማ የተፈጸመው “አመጽ ሳይሆን በአፍሮ አሜሪካዊያን ላይ የተፈጸመ ግልጽ ጭፍጨፋ እና የነጭ የበላይነት በሀገሪቱ ላይ እጅግ የከፋ አደጋን የተፈጸመበት ድርጊት ነው” በማለት የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ገልጸውታል።

የጆ ባይደን ቃላት

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በከተማው ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ በመቶ ዓመታት ውስጥ በሥፍራው ተገኝተው በአፍሮ አሜሪካዊያን ላይ ጭፍጨፋ መፈጸሙን በማረጋገጥ እርሳቸው የመጀመሪያ መሪ መሆናቸውን ገልጸው፣ ጥቃቱ ለደረሰባቸው ሰዎች ክብር በማለት የአንድ ደቂቃ የሕሊና ጸሎት እንዲቀርብ አድርገዋል። ጆ ባይደን ቀጥለውም በወቅቱ ከጥቃቱ ከተረፉ ጥቂት አባላት ጋር ተገናኝተዋል። ጭፍጨፋው በአገሪቱ ታሪክ እጅግ የከፋ አደጋ የተፈጸመበት መሆኑን አስረድተው “በአሜሪካዊያን ውስጥ የሚታይ ጥላቻ ተደበቀ እንጂ በጭራሽ አልተሸነፈም” ብለዋል።

ቱልሳ እ. አ. አ 1921 ዓ. ም.

እ. አ. አ ግንቦት 31/1921 ዓ. ም. በግሪንዉድ ቱልሳ ከተማ ውስጥ በ300 አፍሮ አሜሪካዊያን ማኅበረሰብ ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ የንጹሃን ሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ ከማድረጉ በተጨማሪ ሌሎችንም መጠለያ አልባ ያደርገ መሆኑን የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን አስታውሰው፣ ከአንድ መቶ ዓመታት በኋላም በሕዝቡ መካከል ፍርሃት እንዲነግሥ እና ከፍተኛ ሐዘንን እያስከተለ መሆኑን ገልጸዋል። ከአካባቢው ሕዝቦች የቀረበው የፍትህ ጥያቄ ሙሉ ምላሽ ባያገኝም፣ እ. አ. አ ግንቦት 31 በየዓመቱ የቱልሳ እልቂት የሚታሰብበት ቀን መሆኑን ገልጸዋል።

የመታሰቢያነቱ አስፈላጊነት

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በኦክላሆማ ግዛት ቱልሳ ከተማ ተገኝተው ያደረጉት ንግግር እጅግ ጠቃሚ እና የጭፍጨፋው አስከፊነት ተረስቶ እንዳይቀር የሚያደርግ መሆኑን በሮም ከተማ የሉምሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ፍራንቸስኮ ቦኒኒ አስረድተዋል። ይህን የመሰለ አስከፊ ተግባር መረሳት አመጾችን በማርገቡ በፖለቲካው ረገድ ጠቃሚ ቢሆንም ከዓመታት በኋላ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ መርሳት ጥሩ ቢሆንም እውነተኛውን ታሪክ በመናገር ለጋራ ዕድገት መሥራትን መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።  

ዘረኝነትን ለማጥፋት የሚወሰዱ እርምጃዎች

ክቡር አቶ ፍራንቸስኮ ቦኒኒ በገለጻቸው ጆ ባይደን በአፍሮ አሜሪካዊያን ላይ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ማመናቸው ዴሞክራሲን እና ዜጎችን ማዕከል ያደረገ ጉዞ ያረጋግጣል ብለዋል። በዲሞክራቲክ አገሮች ውስጥ ማህበራዊ መብቶች መሠረታዊ መሆናቸው መታወስ ያለበት ገጽታ ነው ያሉት ክቡር አቶ ፍራንቸስኮ ቦኒኒ፣ ፕሬዚደንቱ ድርጊቱ እንደተፈጸመ ከማረጋገጣቸው በተጨማሪ በጥቁሮች እና በነጮች መካከል የሚታዩ ኤኮኖሚያዊ ልዩነቶች እና ዘረኝነት ለማጥበብ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዳቸውን አስታውሰዋል። አቶ ፍራንቸስኮ ቦኒኒ ገለጻቸውን ሲያጠቃልሉ እንደተናገሩት ከፕሬዚደንት ጆ ባይደን መፈክሮች አንዱ “አሜሪካ ከተሳሳተችበ መንገድ ተመልሳለች” የሚል መሆኑን አስታውሰው፣ በትክክል የዴሞክራሲ እሴቶች አስፈላጊነትን ለማጉላት መፈለጋችውን ገልጸዋል።  

03 June 2021, 16:29