በየመን ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ   በየመን ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ  

በየመን ለስድስት ዓመታት የዘለቀው ጦርነት በሕፃናት ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከተለ

“ሴቭ ዘ ችልድረን” ወይም ሕጻናትን አድን የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት፣ በየመን ውስጥ ለስድስት ዓመታት የዘለቀው ጦርነት በሕፃናት ላይ ያደረሰውን ጉዳት ይፋ አደረገ። ግብረ ሰናይ ድርጅቱ እንዳስታወቀው ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውቅናን ባገኘው የአገሪቱ መንግሥት እና በሁቲ አማፅያን መካከል በተደረገ ጦርነት ከጠቅላላው የአገሪቱ ሕዝብ አንድ አራተኛ በሚሆኑት ሕጻናት ላይ ከፈተኛ አደጋ መድረሱን ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በየመን እ. አ. አ ከመጋቢት ወር 2015 ዓ. ም. ጀምሮ የተካሄደው አመጽ እና ጦርነት ለበርካታ ሽህዎች መሞት፣ ለንብረት እና ማህበራዊ መሠረተ ልማቶች መውደም ምክንያት ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከታዩት እና በጣም አስከፊ ከተባሉ ሰብአዊ ቀውሶች መካከል አንዱ መሆኑ ታውቋል። “ሴቭ ዘ ችልድረን” የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ትናንት ማክሰኞ መጋቢት 14/2013 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ 2,300 ሕጻናት መገደላቸውን አስታውቆ፣ ይህ ቁጥር አደጋው ከደረሰባቸው ጠቅላላ ሰዎች መካከል ሃያ አምስት ከመቶ መሆኑን አስታውቋል። ድርጅቱ በማከልም ዕድሜአቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆናቸው 1.8 ሚሊዮን ሕጻናት በተመጣጣኝ ምግብ እጥረት የሚሰቃዩ መሆኑን፣ ሁለት ሚሊዮን ሕጻናት ከትምህርት ገበታቸው መቅረታቸውን እና ከ 11 ሚሊዮን ሕጻናት በላይ አስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታን የሚፈልጉ መሆኑን አስታውቋል።

በየመን የጦርነቱ ተጥቂ ሕጻናት

በየመን ለስድስት ዓመታት የተካሄደው ጦርነት ለሕጻናት እጅግ አደገኛ እየሆነ መምጣቱን “ሴቭ ዘ ችልድረን”  የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት አስታውቆ፣ እ. አ. አ በ 2018 ዓ. ም. ከተሰበሰበው መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው በየመን ከአምስት የጦርነት ሰለባ ሕጻናት መካከል አንዱ በሕጻንነት የዕድሜ ክልል የሚገኝ፣ እ. አ. አ በ 2019/20 ዓ. ም. ደግሞ ከአራቱ መካከል አንዱ የአደጋው ተጠቂ መሆኑን ገልጿል። ድርጅቱ አክሎም በየመን ከሦስት ሰዎች መካከል ሁለቱ በሕይወት ለመቆየት የሚያስችል አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን አስታውቆ፣ ሕጻናት በተመጣጣኝ ምግብ እጥረት፣ በቀላሉ ሊወገዱ በሚችሉ በሽታዎች ምክንያት እና በቦምብ ፍንዳታ ደንግጠው የሚሞቱ መሆኑን ድርጅቱ ገልጾ፣ በአሁኑ ጊዜ አራት መቶ ሺህ ሕጻናት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት መሰቃየታቸው ታውቋል። በየመን ውስጥ የሚታየው ማኅበራዊ ቀውስ በረሃብ እና በእርዳታ መቋረጥ፣ ለረጅም ጊዜ በተቋረጠው የዕርዳታ መንገድ መዘጋት፣ በአገሪቱ ኤኮኖሚ መውደቅ፣ እንደ ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች በመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች ላይ የተደረጉ ጥቃቶች አደጋውን የከፋ ማድረጉ ታውቋል።

የየመን ጦርነት እና አመጽ ዋና ምክንያቱ የረጅም ጊዜ ፕሬዝዳንት የነበሩት አሊ አብደላህ ሳህላ እ. ኤ. አ በ 2011 ስልጣናቸውን ለምክትላቸው አብድራቡህ ማንሱር ሀዲ እንዲያስረክቡ ያስገደደውን የአረቡን አብዮት ተከትሎ፣ በሀገሪቱ መረጋጋትን ያመጣል ተብሎ የታሰበው የፖለቲካ ሽግግር ውድቅ በመደረጉ ነው ተብሏል። በሽግግሩ ደስተኛ ያልሆኑ እና በኢራን የሚደገፉ የሁቲ አማፅያን እ. ኤ. አ. በ 2014 ዓ. . መጨረሻ እና በ 2015 መጀመሪያ መካከል ቀስ በቀስ ዋና ከተማዋን ሰንዓን መቆጣጠራቸው ይታወሳል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሳዑዲ አረቢያ እና የሌሎች መንግሥታት ጥምረት፣ አማጽያንን ለማሸነፍ እና በየመን የኢራንን ተጽዕኖ ለማስቆም ያለመ ዘመቻ መጀመራቸው ይታወሳል።             

የተኩስ አቁም ጥያቄ

ባለፈው ሰኞ መጋቢት 13/2013 ዓ. ም. ሳዑዲ አረቢያ በየመን የሁቲ አማጽያን የስድስት ዓመቱን ጦርነት እንዲያቆሙ እና በዋና ከተማዋ ሳንዓ የሚገኝ ዋና አውሮፕላን ማረፊያ እንዲከፈት ለማስቻል የታቀዱ ሀሳቦች አካል የሆነውን የተኩስ አቁም ሃሳብ ማቅረቧ ታውቋል። በሳዑዲ አነሳሽነት የሳንዓ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለተለያዩ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ በረራዎች የሚከፈት ሲሆን፣ ሳዑዲ አረቢያ በሳዑዲ ወታደሮች ታግዶ ወደ ነበረው የሆዲዳ ወደብ መርከቦችን ለማስገባት ፈቃደኛ መሆኗን ተናግራለች። የወቅቱ ረቂቀ-ሀሳብ፣ ከወደቡ የሚገኘው ገቢ በሁቲ አማጺያን እና በየመን መንግሥት በጋራ ወደ ሚተዳደር የባንክ ሂሳብ ውስጥ የሚገባ መሆኑን የረቂቀ-ሃሳቡ ስምምነት ያስገነዝባል። ረቂቀ ሃሳቡ ሁሉም ወገኖች በተቻለ ፍጥነት የተኩስ አቁሙን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በተግባር መተርጎም እንዳለባቸው ገልጾ፣ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ዘላቂነት ያለው፣ ሰላምን እና ፖለቲካዊ መፍትሄን ለማምጣት እና ሰብአዊ አደጋን ማቆም የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ነው ተብሏል።

ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ማግኘት

የመን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ በሚያስፈልጋት በዚህ ወቅት፣ ከሚያስፈልጋት የገንዘብ ድጋፍ ግማሽ ያህሉ መገኘቱ ታውቋል። በእርግጥም በአመፅ የተጎዱ ሕፃናትን ለማከም የተገኘው የገንዘብ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር አርባ ከመቶ በላይ መቀነሱ ተመልክቷል። ከጤና ተቋማት መካከል ከግማሽ በላይ ተዘግተው ወይም በከፊል አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ እና የጤና ስርዓቱ በመውደቅ ላይ ያለ መሆኑን “ሴቭ ዘ ችልድረን” አስታውቋል። አስቸኳይ እርምጃ ካልተወሰደ፣ ቀድሞም ቢሆን እጅግ በከፋ ደረጃ ላይ የሚገኘው የየመን ሰብዓዊ ሁኔታ ሊባባስ እንደሚችል፣ የሲቪሎች ሞት እንደሚጨምር እና የመሠረታዊ አገልግሎቶች መውደቅ ህዝቡን በበለጠ ችግር ውስጥ ሊያስገባ እንደሚችል ድርጅቱ አስታውቋል።

ሕጻናትን አድን ድርጅት አቅመ ደካሞችን በመርዳት ላይ ይገኛል

በአሁኑ ወቅት “ሴቭ ዘ ችልድረን” በየዓመቱ በመላው የመን የሚገኙ አቅመ ደካሞችን በመድረስ የምግብ ዕርዳታን፣ የጤና ክብካቤን፣ የትምህርት ዕድልን እና አመፅን ለመከላከል እየሠራ መሆኑ ታውቋል። እስካሁን በሥራ ላይ ባሉት የድርጅቱ የመስክ ሰራተኞቹ ያላሰለሰ ጥረት ለ 4 ሚሊዮን ሕፃናት ድጋፍ መደረጉ ታውቋል።

24 March 2021, 14:35