የማሌዥያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የማሌዥያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት  

የማሌዥያ ፍርድ ቤት ሁሉም ሐይማኖቶች የ “አላህ” ስም መጥራት የሚችሉ መሆኑን አስታወቀ

የማሌዥያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከዚህ በፊት የ “አላህ” ስም በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ብቻ እንጂ በሌሎች እምነቶች ዘንድ እንዳይጠራ መንግሥት ያስቀመጠውን ሕግ በአብላጭ ድምጽ መሻሩ ተነገረ። ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ እገዳው ሕገ-መንግሥቱ ከሚፈቅደው የሃይማኖት ነፃነት መብት ጋር የሚጋጭ መሆኑን አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከአሥር ዓመታት በላይ ክርክር ሲካሄድበት ከቆየ በኋላ መጋቢት 8/2013 ዓ. ም በጸደቀው ሕግ መሠረት፣ ከእስልምና እምነት ሌላ የክርስትናን እምነትን ጨምሮ በሁሉም ሐይማኖቶች ዘንድ የ “አላህ”ን ስም መጥራት ሕገ-ወጥ አለመሆኑን የማሌዥያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታውቋል። በዚህም መሠረት የእስልምና እምነት ተከታይ ያልሆኑ ሌሎች እምነቶች “አላህ” የሚለውን የእግዚአብሔር ስም ለሐይማኖት ማስተማሪያነት፣ ለጸሎት፣ ለመጽሐፍት ሕትመት እና ለመንፈሳዊ አገልግሎቶች ማስፈጸሚያ መጠቀም የሚችሉ መሆኑን ታውቋል።

እ.አ.አ የ 1986 ዓ. ም የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መመሪያ

“አላህ” የሚል ስም ከእስልምና እምነት በስተቀር በሌሎች እምነቶች ዘንድ እንዳይጠራ የታገደው፣ ጂል አይርላንድ ሎሬንስ ቢል የተባሉ ማሌዥያዊት ክርስቲያን ምዕመን የያዟቸው፣ የ “አላህ” ስም የተጻፈባቸው ስምንት ትምህርታዊ ካሴቶች እ.አ.አ በ2008 ዓ. ም በኳላ ላምፑር አየር ማረፊያ ላይ ሲያዝባቸው መሆኑ ታውቋል።  እ.አ.አ የ 1986 ዓ. ም. የማሌዥያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሕዝብ ፀጥታ ሲባል ክርስቲያን ምዕመናን “ኣላህ” የሚለውን ስም እንዳይጠቀሙ የሚከለክል መመሪያ ማስተላለፉ ይታወሳል። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ አክራሪ ሙስሊም የሃይማኖት አባቶች “አላህ” የሚለውን ስም መጠቀም የሙስሊሞች ብቸኛ መብት በመሆኑ ክርስቲያኖች እንዲጠቀሙት መፍቀድ ግራ የሚያጋባ እና ብጥብጥ ሊያስከትል የሚችል ነው በማለት ተከራክረዋል።

ሎሬንስ ቢል የተባሉ ማሌዥያዊት ክርስቲያን ምዕመን ግን በኳላ ላምፑር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው ባቀረቡት የመከራከሪያ ሃሳባቸው ተከትለው ‘“ኣላህ” የሚለውን ስም ለመንፈሳዊ ትምህርቶች መጠቀም መብቴ ነው’ በማለት የድጋፍ ፊርማ ሲያሰባስቡ ቆይተዋል። በዚህ መሠረት ከዚህ በፊት የተወረሰባቸው እና የ “አላህ” ስም የተጻፈባቸው ስምንት ትምህርታዊ ካሴቶቻቸውን እ.አ.አ በ2014 ዓ. ም ሊያስመልሱ መቻላቸው ታውቋል።

እገዳው "ህገ-ወጥ እና ህገ-መንግስታዊ ያልሆነ ነው"

የማሌዥያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መጋቢት 1/2013 ዓ. ም ባሳለፈው ውሳኔ ባለመብቷ በምትከተለው እምነቷ ምንም ዓይነት ልዩነት እንዳይደረግባት ትዕዛዝ ማስተላለፉ ታውቋል። በተላለፈው ውሳኔ መሠረት ከ “ኣላህ” ስም በተጨማሪ  የአረብኛ ቋንቋ መሠረት ያላቸው ሦስት ቃላት እነርሱም “ካአባ” (በመካ የሚገኝ የንግደት ሥፍራ)፣ “ባሂቱላህ” (የእግዚአብሔር ቤት) እና “ሳላት” (ጸሎት) የሚሉ ቃላት በክርስቲያን ሐይማኖት ዘንድ መጠቀም እንደሚቻል ዳኛ ኖር ቢይ መፍረዳቸው ታውቋል።

ሌሎች ጉዳዮችም አሉ

በማሌዥያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መካከል “ኣላህ” በሚለው ስም ላይ ልዩነት ሲታይ ይህ የመጀመሪያ አለመሆኑ ሲታወቅ እንደዚሁም “ዘ ሄራልድ” የተሰኘ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሳምንታዊ ጋዜጣ በዕትሙ መንግሥት በአገሩ ቋንቋ የተጻፈውን “ኣላህ” የሚለውን ስም  የክርስቲያኖች እግዚአብሔር በሚል ስም እንዲተካ ማዘዙ አስታውሷል። እ.ኤ.አ. በ 2009 የዝቅተኛው ፍርድ ቤት የመንግሥት ውሳኔን በመሻር “ኣላህ” የሚለውን ስም በክርስቲያናዊ ጸሎት እንዲጠቀሙት ሲፈቅድ ከአክራሪ ሙስሊም ቡድኖች በኩል ጠንካራ ተቃውሞን መቀስቀሱ ይታወሳል።  

“ኣላህ” የሚል ስም ወደ ማሌዥያ የመጣው ከአረቡ ዓለም ሲሆን በማሌዥያ ብሔራዊ ቋንቋ ደግሞ እግዚአብሔር የሚል ትርጉም በመስጠት ለዘመናት ሲጠቀሙት መቆየታቸው ይታወቃል። በማሌዥያ ውስጥ በተለይም በቦርኔዎ ክፍለ ሀገር የሚገኙ የሳባህብ እና ሳራዋክ ግዛቶች የሚገኙ ሦስት አራተኛ ክርስቲያን ማኅበረሰብም ለዘመናት ያህል መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓቶችን በሚያካሂዱበት ወቅት እግዚአብሔር የሚለውን ትርጉም በመስጠት ሲገለገሉበት መቆየታቸው ይታወሳል። ከማሌዥያው 32 ሚሊዮን ህዝብ መካከል 60 ከመቶ ሙስሊም ሲሆኑ ክርስቲያን 13 ከመቶ በመያዝ በቁጥር ሶስተኛው የሃይማኖት ቡድን መሆኑ ይታወቃል።     

20 March 2021, 17:22