የተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ መንገዶች፤ የተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ መንገዶች፤ 

ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ለመልካም የቤተሰብ ግንኙነት ማዋል።

ክቡራት እና ክቡራን የ“ቤተሰባችን” ጽሑፍ አንባቢዎቻችን ሰላምን እና ፍቅርን እየተመኘን የከበረ ሰላምታችንን እናቀርብላችኋለን። በዛሬው ጽሑፍ “ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ለመልካም የቤተሰብ ግንኙነት ማዋል ያስፈልጋል በሚል ርዕሥ የተዘጋጀ አጭር ጽሑፍ እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

ማኅበራዊ መገናኛዎች ቤተስብን በማገናኘት እና መረጃን እንዲለዋወጡ በማገዝ፣ በማስተማር እና በማዝናናት ከፍተኛ አገልግሎትን ያበረክታሉ። የቤተሰብን፣ የማኅበረሰብን እና የአገርን ሰላም እና አንድነት በማስጠበቅ ረገድም የሚያበረክቱት ጥቅም ከፍተኛ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያ ወይም ማኅበራዊ መገናኛዎች የምንላቸው ፌስ ቡክን፣ ቲዊተርን ሽንስ ኢስታግራምን ጨምሮ ሌሎችም በማኅበራዊ መገናኛ ዘርፍ የጽሑፍ ፣ የምስል እና የድምጽ መልዕክቶችን በአጭር ጊዜ ወደ መላው ዓለም በማድረስ የሚሰጡት አገልግሎት ከፍተኛ ነው። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ ዘመን አቆጣጠር 2018 ዓ. ም. የቀረበው የግሎባል ዲጂታል ሪፖርት እንዳመለከተው በዓለማችን ውስጥ በግምት 3.196 ቢሊዮን የሚሆኑ የሶሻል ሚዲያ ወይም ማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች መኖራቸውን አረጋግጧል።  

ፌስ ቡክ፣ ቲዊተር፣ ኢስታግራም እና ሊንክድ ኢን የሚባሉ ማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በቅርብ ከሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች አልፎ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ሰዎች ጋርም በቀላሉ እንዲገናኙ ዕድል ፈጥሯል። ማኅበራዊ መገናኛዎች የሚሰጡን አገልግሎት በመጠቀም በሕዝቦች፣ በሐይማኖቶች እና በፖለቲካ ቡድኖች መካከል የጋራ ውይይትን በማካሄድ ወንድማማችነትን፣ ሰላምን፣ ብልጽግናን እና አንድነትን ላማሳደግ ተችሏል። ማኅበራዊ ውይይቶ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገትን በማሳየት በሕዝቦች መካከል የአመለካከት ለወጥን፣ መቻቻልን እና መግባባትን በማምጣት ላይ ይገኛሉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ቀንን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት አንድነቱን የጠበቀ ጠንካራ ማኅበሰብን ለመፍጠር ከሁሉ አስቀድሞ በሰዎች መካከል መተማመን እና ተመሳሳይ የጋራ ዓላማ ያለው ማኅበረሰብ ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል። የዚህ ማኅበረሰብ ግንኙነት ቀጣይነት እንዲኖረው፣ አንድነቱም ዘላቂ እንዲሆን ለማድረግ ከተፈለገ በመካከላቸው መደማመጥ እና ሃላፊነት ያለበት ግልጽ ቋንቋ መናገር፣ በእውነት ላይ የተመሠረተ የጋራ ውይይቶችን ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር በማያያዝ ማኅበራዊ መገናኛዎች በሕዝቦች መካከል ጠንካራ አንድነትን ለመፍጠር ከመቻላቸው በተለየ መልኩ በተለይ ወጣቱን ትውልድ በመጉዳት ላይ ያለውን የብቸኝነት ስሜት ሊያስከትል እንደሚችል አስረድተዋል። ይህን አስከፊ ማኅበራዊ ልዩነትን እና ክፍፍልን ለማስወገድ ክርስቲያን ማኅበረሰብ የተፈጥሮ ስጦታ የሆነውን ሰብዓዊ አንድነት፣ ሰላም እና ፍቅርን ለማሳደግ ማኅበራዊ መገናኛ መንገዶችን በሚገባ መጠቀም እንደሚገባቸው አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም እኛ ክርስቲያኖች ማኅበራዊ መገናኛዎችን በምንጠቀምበት ጊዜ ማስተዋል ያለብን የክርስቲያናዊ ማንነታችን መገለጫ የሆነውን አንድነት ለመመስከር ተጠርተናል ብለው፣ ክርስቲያናዊ እምነታችን የእግዚአብሔር ፍቅር የሚገኝበት በመሆኑ ይህን የፍቅር ጸጋን ተቀብለን በተግባር ልናውል ያስፈልጋል ብለዋል።   

ምናባዊ ማኅበረሰብ ዕለታዊ ግንኙነቱን ወይም መልዕክቶቹን በጽሑፍ፣ በምስል እና በድምጽ አማካይነት ብቻ የሚለዋወጡ ናቸው። “ማኅበራዊ ግንኙነት ክርቲያናዊ ይዘት ሊኖረው የሚችለው ሰዎች በአካል፣ ዓይን ለዓይን በመተያየት ሰብዓዊ ግንኙነታቸውን ሲያሳድጉ ብቻ ነው” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያስረዳሉ። ቤተሰብ ማኅበራዊ መገናኛን የሚጠቀመው ተለያይቶ መቅረት እንዳይፈጠር እና እርስ በእርስ ለመጠያየቅ ከሆነ፣ ከዚያም በተጨማሪ ጊዜን እና አጋጣሚ ሲገኝ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ቀርበው ፊት ለፊ በመገናኘት መነጋገር፣ መወያየት እና መጫወት የሚችሉ ከሆነ ማኅበራዊ መገናኛን በትክክል መጠቀም መቻላቸውን ያረጋግጣል ብለዋል። በተመሳሳይ መልኩ የክርስቲያን ማኅበረሰብ የቤተክርስቲያንን አገልግሎቶች በማኅበራዊ መገናኛዎች በኩል የሚያከናውን ከሆነ እና ከዚህም በተጨማሪ ምስጢራትን እና የጸሎት ሥነ ሥርዓቶችን በአካል ተገናኝተው በጋራ መካፈል ከቻለ፣ ማኅበራዊ መገናኛን በአግባቡ መጠቀም ችሏል በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያስረዳሉ።          

በማኅበራዊ መገናኛ የሚተላለፍ መረጃ ለጋራ ጥቅም የሚውል መሆነው አለበት። ኅብረተሰብም በሐቅ፣ በነጻነት በፍትህና በአንድነት ላይ የተመሠረተ መረጃን የማግኘት መብት አለው። የኅብረተሰብ አባላት በዚህ ዘርፍ የፍትህንና የፍቅርን ጥያቄዎች መመለስ ይጠበቅባቸዋል። በማኅበራዊ መገናኛ አማካይነት ጤናማ ሕዝባዊ አስተሳሰብ በመፍጠር እና በማስረጽ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከት አለባቸው። ኅብረት የእውነተኛ እና የተክክለኛ መረጃ ልውውጥ፣ እንዲሁም እውቀትን እና ለሌሎች ያለውን አክብሮት የሚያዳብሩ ሃሳቦች በነጻ የሚንሸራሸሩበት የማኅበራዊ መገናኛ ውጤት ነው። (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2494-2495)

ማኅበራዊ ኑሮን ከሚያውኩ፣ ለማሕበራዊ ጸጥታ አስጊ ከሚባሉ ማሕበራዊ ቀውሶች መካከል አንዱ የሰላም መደፍረስ ነው። ማኅበራዊ መገናኛዎች በቤተሰብ እና በማኅበረሰብ መካከል ሰላምን በመፍጠር፣ መረጋጋትን በማምጣት ከፍተኛ ሚናን ሊጫወቱ ይችላሉ። ቤተሰቦች ንቁ የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች በመሆን በቤት ውስጥ ሆነ በጎርቤት መካከል የሰላም መልዕክቶችን በማስተላለፍ ጠቃሚ አገልግሎቶችን ማበርከት ይችላሉ። በማኅበራዊ መገናኛዎች በኩል የሚነገሩ፣ ጥላቻን እና አመጽን እያስፋፋ የሚገኝ ማኅበራዊ ጠንቅ የሐሰት ዜና ስርጭት ነው። ቤተሰብ ማኅበረሰብን የሚጠቅሙ ርዕሠ ጉዳዮችን በመምረጥ፣ መልካም ግንኙነቶች እንዲያድጉ በማድረግ የሰላም አስተማሪ ሊሆን ይችላል።       

ዮሐንስ መኰንን ነኝ፤

12 July 2020, 13:27