ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከሕጻናት ጋር በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ሕንጻ ውስጥ፤ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከሕጻናት ጋር በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ሕንጻ ውስጥ፤ 

“ቤተሰባችን”፣ ሕጻናት እንክብካቤ እና ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው የአገር ተስፋዎች ናቸው።

ክቡራት እና ክቡራን የ“ቤተሰባችን” ዝግጅት አንባቢዎቻችን በዚህ ጽሑፍ “ልጆች እንክብካቤ እና ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው የአገር ተስፋዎች ናቸው” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀ አጭር ጽሑፍ እናቀርብላችኋለን፥

ልጆች ከቤተሰብ ይሁን ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ አስፈላጊውን እንክብካቤ፣ ጥበቃን እና ክብር የማግኘት መብት አላቸው። መብታቸውም ቅዱሳት መጻሕፍት፣ ዓለም አቀፍ ሕጎችን እና የየአገራቱን ሕገ መንግሥት መሠረት ያደረገ ነው። ስለ ሕጻናት መብት ማወቅ ያስፈለገበት ምክንያት እንደ ማንኛውም ሰው የማይካድ እና የማይለውጥ ሰብዓዊ ክብር ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በመሆናቸው ነው። ይሁን እንጂ ልጆች በልጅነት ዕድሜአቸው መብታቸውን የማስከበር የአካልም ሆነ የአዕምሮ ብቃት ስለሌላቸው የማኅበረሰብ ክፍል ስለ ሕጻናት ወይም ልጆች መብት ሃላፊነትን መውሰድ ይኖርበታል። ሕጻናት ወደዚህ ምድር ፈልገው ወይም መርጠው የመጡ አይደሉም። ቢሆንም ከወላጆቻቸው እና ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ የሚደረግላቸው ፍትሃዊ ሕይወትን የመኖር መብት እና በነጻነት ማደግ አብሯቸው የሚወለድ መብት በመሆኑ ተግባራዊነቱን መከታተል ያስፈልጋል። ለሕጻናት ነጻነትን መስጠት ማለት፣ እንክብካቤ እና ጥበቃ ያለበት ሙሉ አስተዳደግ እንዲኖራቸው ማድረግ ማለት ነው። ይህም ማለት ደግሞ ቸልተኝነትን በማስወገድ፣ ሕጻናትን ከአካል እና ስነ ልቦና ጉዳት እና ከብዝበዛ ነፃ ማድረግን ያካትታል። ፍትሃዊ ሕይወት እንዲኖራቸው ማድረግ፣ መሠረታዊ እንክብካቤዎችን ማድረግ ሲሆን ይህም በቂ እና ተመጣጣኝ ምግብ እንዲያገኙ፣ ልብስ እና መጠለያን እንዲመቻችላቸው፣ በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ ሊደርስባቸው ከሚችል ጥቃት እና ጭቆና ነጻ እንዲሆኑ ማድረግን ያካትታል።

ዓለም አቀፍ ሕግን የተከተለ እና ቅድስት መንበርን ጨምሮ በርካታ የዓለማችን መንግሥታት በፊርማቸው ያጸደቁት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት መብት ድንጋጌ፣ ሕጻናት ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆላቸው፣ በነጻነት፣ በእኩልነት እና ከሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በአንድነት፣ በሰላም ማደግ እንዳለባቸው ያስገነዝባል። ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ፣ ሕጻናት ልዩ እንክብካቤ እና ጥበቃ የሚያሻው መሆኑን ይገልጻል። ከዚህም በተጨማሪ ሁሉም የዓለማችን መንግሥታት ቀዳሚ የሕጻናት ምርጫ እና ፍላጎት ምን እንደሆነ ተገንዝበው፣ ከሚደርስባቸው ጾታዊ ጥቃቶች፣ የጉልበት ብዝበዛዎች እና ሌሎች ጉዳቶች እንዳይደርስባቸው በመከላከል፣ መልካም የአካል እና የስነ ልቦና እድገት እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል በማለት ያሳስባል።

የሕጻናትን አስተዳደግ በተመለከተ፣ ሐይማኖታዊ አስተምህሮ ለሕጻናት የሚሰጡት ሥፍራ ከፍተኛ ነው። የክርስትና አስተምህሮን የተመለከትን እንደሆነ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ቅዱስ ሉቃስ እንደጻፈው በምዕ. 18፡17 “በእውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕጻን በየዋህነት ያልተቀበላት ሰው ከቶ አይገባባትም” በማለት ሕጻናት በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ወይም በክርስትና ሕይወት ውስጥ ማዕከላዊ ሥፍራን ይዘው እንደሚገኙ ያስገነዝባል። ይህ ማለት ደግሞ ቤተክርስቲያን በምድር ላይ ስለ እግዚአብሔርን መንግሥት በምትመሰክርበት ጊዜ ሕጻናትን ወደ ቤቷ በደስታ በመቀበል እና በመንከባከብ፣ ማዕከላዊ ቦታ እንዲኖራቸው ለማድረግ የተጠራች መሆኗንም ያስገነዝባል። አሁንም በቅዱስ ወንጌል ውስጥ፣ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴ. 19፡14 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ “መንግሥተ ሰማይ እንደነዚህ ላሉት ስለሆነች ሕጻናትን ተዉአቸው፥ ወደ እኔ ይምጡ” በማለት ማሳሰቡን በምንመለከትበት ጊዜ፣ ለህፃናትንና ወጣቶች የሚደረግ እንክብካቤ እና ጥበቃ የቤተክርስቲያን የጋራ ግዴታ መሆኑን ያስታውሰናል።

ወላጆችም ሆነ ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሕጻናትን መልካም የሥነ ምግባር እና የአካል አስተዳደግ በመከታተል ረገድ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታሉ፤ ሃላፊነትም አለባቸው። በተለይም ወላጆች በልጆቻቸው መልካም አስተዳደግ ላይ ያላቸውን ሃላፊነት በማስመልከት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ የሚከተለውን መልዕክት ይናገራል፥ “የባለትዳሮች የፍቅር ዓላማ ልጆችን በማፍራት ብቻ ሳይወሰን ሥነ ምግባራዊ ትምህርት እና መንፈሳዊ አስተዳደጋቸውንም በሚመለከት ጉዳይ ያላቸው ሚና በጣም ወሳኝ በመሆኑ ይህን በተመለከተ እነርሱን መተካት እጅጉን ኣዳጋች ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር ያላቸው መብት እና ግዴታ ፍጹም እና የማይገረሰስ ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን የእግዚአብሔር ልጆች እንደሆኑ አድርገው ማየት እና በሰብዓዊነታቸውም ሊያከብሯቸው ይገባል። ወላጆች በሰማይ ላለው አባት ፈቃድ ራሳቸውን ታዛዥ በማድረግ ልጆቻቸው የእግዚአብሔር ሕግ እንዲፈጽሙ ያስተምሯቸዋል” በማለት ያስገነዝባል። (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ፣ ቁ. 2221)

በዓለማችን ውስጥ በሚከሰቱ በርካታ ማኅበራዊ ችግሮች ምክንያት ብዙ ሕጻናት ከወላጆቻቸው ፍቅር እና እንክብካቤ ተለይተው ብቻቸውን በየመንደሩ እና በከተሞች አውራ ጎዳናዎች ሲንከራተቱ እናያቸዋለን። ይህን የመሰለ ሕይወት ለሕጻናት ቀርቶ ለጎልማሶችም እጅግ ከባድ መሆኑን መገመት ይቻላል። ያለ ተንከባካቢ በቀሩት ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ። በተለይም የሕጻናት መብት በተግባር በማይከበርባቸው አገሮች ውስጥ በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እያደጉ መምጣታቸውን የተለያዩ መረጃዎች በተጨባች ማስረጃ ሲያመላክቱ ቆይተዋል። በሕጻናት ላይ በሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች ሆነ ሌሎች ጉዳቶች ላይ በጥልቀት በመወያየት፣ ለችግሩ ፈጣን መፍትሄ ካልተገኘለት ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሊመጣ ይችላል። በሕጻናት ላይ የሚደርስ የመብት ረገጣ ጎልቶ በሚታይባቸው አገሮች፣ መርሃ ግብሮችን አዘጋጅቶ በማኅበረሰቡ መካከል ግንዛቤን መፍጠር እና የአመለካከት ለውጥ ማምጣት አስፈላጊ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ የሐይማኖት ተቋማት እና መንግሥታዊ ድርጅቶች ሕዝባቸውን በግብረ ገብ፣ በመንፈሳዊ እና ባሕላዊ እሴቶች በማነጽ መልካም ማኅበረሰብን ለመፍጠር የበኩላቸውን ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል።  

ዮሐንስ መኰንን ነኝ፤

18 July 2020, 21:28