የቤይሩት ከተማ በጨለማ ተውጣ፤ የቤይሩት ከተማ በጨለማ ተውጣ፤ 

ካርዲናል ራይ፣ ሊባኖስ በከባድ የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንደምትገኝ አስታወቁ።

በሊባኖስ የምስራቅ ቤተክርስቲያን ሥርዓት አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ካርዲናል ቡትሮስ ራይ፣ አገራቸውን ከባድ የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ ቀውስ ያጋጥማት መሆኑን ገልጸው፣ ከችግር እንድትወጣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እርዳታን እንዲያደርግላት ጠይቀዋል።

የቫቲካን ዜና፤

ከጎርጎሮሳዊያኑ ጥቅምት ወር 2019 ዓ. ም. ጀምሮ ሊባኖስን ያጋጠማት የፖለቲካ እና ኤኮናሚ ቀውስ ተከትሎ በአገሪቱ አውራ ጎዳናዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች የታገዙ ጸረ መንግሥት ሰልፎች በስፋት ሲካሄዱ መቆየታቸው ይታወቃል። ሕዝባዊ ተቃውሞ በርትቶ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ሳድ ሐሪሪ ከስልጣናቸው ማስወገዳቸው ይታወሳል። ባሁኑ ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሊባኖሳዊያን የዕለት ጉርሳቸውን እስከ ማጣት መድረሳቸው ታውቋል።

በአገሪቱ የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶችን አስከትሏል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ቡትሮስ ራይ ለቫቲካን ኒውስ እንደገለጹት፣ የፖለቲካ ቀውሱ ዋና ምክንያቱ የሦስት ፖለቲካ ፓርቲዎች ጣልቃ ገብነት ነው ብለው እነርሱም የሄስቦላ ፓርቲ፣ የሺያ እስላማዊ ግንባር እና ተጣቂ ሚሊሻ ቡድን ጣልቃ ገብነት ነው ብለዋል።  በሊባኖስ የሚገኝ ሄስቦላ ፓርቲ መንግሥትን በመቃረን፣ በአገሪቱ ጦርነትን በማወጅ የአገሪቱን ጸጥታ ሲነሳ መቆየቱን ገልጸው፣ በሌሎች አገሮችም በሶርያ፣ በኢራቅ እና በየመን ውስጥ ጦርነቶችን ሲያግዝ መቆየቱን ብጹዕ ካርዲናል ቡትሮስ ራይ አስረድተዋል።

አገራቸው የምትገኝበትን ሁኔታ ሲናገሩ፣ በርካታ ቤተሰቦች የሚበሉትን አጥተው በረሃብ መቸገራቸውን ገልሰው፣ ይህን ችግር ለማቃለል ካቶሊካዊ ድርጅቶች ተባብረው ዕርዳታን በማቅረብ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በርካታ ቤተሰቦች ከሥራ ገበታቸው የመወገዳቸው ምክንያት ችግሩን እንዳባባሰው ብጹዕ ካርዲናል ቡትሮስ ራይ ገልጸዋል። በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት “FAO” በቅርቡ ባቀረበው ሪፖርቱ ሃምሳ ከመቶ ለሚሆን የሊባኖስ ሕዝብ፣ በጥገኝነት ለተቀመጡ 63 ከመቶ ለሚሆኑ የፍልስጤም ስደተኞች እና 75 ከመቶ ለሚሆኑ የሶርያ ስደተኞች የምግብ እርዳታን በማቅረብ ላይ መሆኑን አስታውቆ፣ ባሁኑ ጊዜ ድርጅቱን ከፍተኛ የምግብ እጥረት ያጋጠመው መሆኑን አስታውቋል።

በአጎራባች አገር ሶርያ የሚካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት በርካታ ሶርያዊያን ወደ ሊባኖስ እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ቡትሮስ ራይ፣ በሶርያ ውስጥ የእርስ በእርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ከጎርጎሮሳዊያኑ 2011 ዓ. ም. ጀምሮ ወደ ሊባኖስ የተሰውደዱት ሶርያዊያን ቁጥር አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ መሆናቸውን ገልጸዋል። ብጹዕ ካርዲናል ቡትሮስ ራይ፣ ሊባኖስ አሁን ባለችበት ሁኔታ በርካታ ስደተኞችን ማስተናገድ ይከብዳታል ብለው፣ ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ሊባኖስ ራሷንም ሆነ የሌሎች አገሮች ስደተኞችን መርዳት እንድትችል ማንኛውም ዓይነት ድጋፍ እንዲያደርግ በማለት ተማጽነዋል። 

16 July 2020, 18:54