በኮንጎ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና የጎርፍ አደጋ ውስጥ ቤተክርስቲያን ተልዕኮዋን በመፈጸም ላይ መሆኗን አስታወቀች።
በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ደቡባዊው ኪቩ ክፍለ ግዛት የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በአርባ ሰዎች ላይ የሞት አደጋን እና አሥራ አምስት ሺህ መኖሪያ ቤቶችን ያወደመ መሆኑ ሲነገር ኡቪራ ከሚባል ከተማ ጋር ግንኙነት እንዲቋረጥ ማድረጉ ተሰምቷል። ብጹዕ አቡነ ሙኘንጎ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት በካባቢው የኮሌራ ወረርሽኝም መከሰቱን አስረድተው፣ ከኮሮና ወረርሽኝ በተጨማሪ አዲስ የኢቮላ ወረርሽኝም መከሰቱን ክቡር አባ ዲ ቪንቼሶ ከቡቴምቦ ገልጸዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በአካባቢው በጣለው ሀይለኛ ዝናብ ምክንያት የኡቪራ ከተማ ሙሉ በሙሉ ሰው ሊደርስባት የማይችል አካባቢ ሆናለች፣ ድልድዮች ፈርሰዋል፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ የላትም ፣ በመሆኑም የኮሌራ በሽታ ሊዛመት ነው፣ የአካባቢው ሕዝብ በምግብ እጥረት በረሃብ የሚሰቃይ መሆኑን በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ የኡቪራ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሰባስቲያን ሙኘንጎ ሙሎምባ ምስክርነታቸውን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል። በምስራቃዊው ደቡብ ኪቩ፣ ከብሩንዲ ጋር በሚዋሰኑ አካባቢዎች የጣለው ከባድ ዝናብ በሦስት ወንዞች የውሃ መጠን እንዲቸምር ከማድረጉ በላይ መኖሪያ ቤቶችን በማውደም የኡቪራ ከተማን ያጥለቀለቃት መሆኑ ታውቋል።
በኡቪራ ቀውስ አስወጋጅ ኮሚቴ ተቋቁሟል።
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ 400 የሚጠጉ ሰዎች በተመዘገበችባት ኮንጎ፣ የኡቪራ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሰባስቲያን ሙኘንጎ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የእርዳታ እጁን እንዲዘረጋ ተማጽነዋል። በአካባቢው ተሰማርቶ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ሚሽን እንዳስታወቀው ሃይለኛ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ምክንያት የአርባ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን፣ አሥራ አምስት ሺህ ቤቶች መውደማቸውን እና ወደ ሰማንያ ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ እና የደረሱበት የማይታወቅ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን አስታውቋል። አካባቢው ከዚህ ቀደም በጸጥታ ማነስ አምጽ የሚነሳበት በመሆኑ የተባበሩ መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል ተሰማርቶ የሚገኝበት ሥፍራ መሆኑ ታውቋል።
አዲስ የኢቮላ ወረርሽኝ መከሰት፣
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ ይውል ዘንድ 363 ሚሊዮን ዶላር መመደቡ ታውቋል። በአገሪቱ አዲስ የኢቦላ ወረርሽኝ በመከሰቱ አስቸኳይ የገንዘብ ዕርዳታ በመፈለግ ላይ መገኘቷ ታውቋል። ከትኩሳት ጋር ደም የሚያስቀምት ተላላፊ በሽታ ከዓለማችን ሙሉ በሙሉ መወገዱን ይፋ ለማድረግ የዓለም ጤና ድርጅት በሚዘጋጅበት ወቅት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር በ2018 ዓ. ም. በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎችን መግደሉ ይታወሳል። በሰሜን ኪቩ ግዛት ቤኒ በተባለ አካባቢ በሚያዚያ ወር መጀመሪያ ላይ አዲስ የኢቦላ ወረርሽኝ መታየቱን ከጎርጎሮሳውያኑ 1979 ዓ. ም. ጀምሮ የወንጌል አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ የሚገኙ ኮምቦናዊው ሚሲዮናዊ ክቡር አባ ጋስፓሬ ዲ ቪንቸንሶ አስታውቀዋል። ክቡር አባ ዲ ቪንቼንሶ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት በአካባቢው በተከሰተው የኢቦላ ወረሽኝ ቢያንስ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ሰዎች መሞታቸውን አስታውሰው፣ አሁን ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሲታከልበት በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን አባ ዲ ቪንቼንሶ አስታውቀዋል።
ከአገሪቱ ዋና ከተማ ኪንሻሳ ጋር ከአምስት ሳምንታት በላይ የስልክ ሆነ የመንገድ ግንኙነት ተቋርጦ መቆየቱን አባ ዲ ቪንቼንሶ ገልጸው እርሳቸው በሚኖሩበት ሰሜን ኪቩ ግዛት ዋና ከተማ ጎማ ጋር የሚያገናኝ የመኪና መንገድ መከፈቱን አስታውቀው ቤተክርስቲያናት እና ትምህርት ቤቶች ዝግ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተለያዩ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩት ሰራተኞች ደምወዝ ስለተቋረጠባቸው ራሳቸውን ለመመገብ በእርሻ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ መሆናቸውን አባ ዲ ቪንቼንሶ አስረድተው ሰዎች እርሻቸውን ለማረስ ረጅም መንገድ የሚጓዙ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ሌላው አካባቢ በሀገረ ስብከታቸውም ምዕመናን የሚሳተፉበት የመስዋዕት ቅዳሴ ጸሎት ስነ ስርዓት መቋረጡን የገለጹት አባ ቪንቼንዞ፣ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በሬዲዮ የሚተላለፍ መሆኑን እና ቤተሰብ በጋራ የሚያቀርቧቸው ጸሎቶች ለእያንዳንዱ ቤተስብ በጽሑፍ ተዘጋጅቶ የታደለላቸው መሆኑን አስረድተዋል። በተለያዩ ዕለታዊ ተግባራት፣ በማስተናር አገልግሎት፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የነበሩ የማኅበራቸው አባላት በኮሮና ቫይረስ ወረሽኝ ምክንያት በቤት እንዲቀመጡ መገደዳቸውን ገልጸዋል።
በሰሜናዊው ኪቩ ይጥል የነበረው ኃይለኛ ዝናብ እና የሰዎች ጥቃት መቀነሱን አባ ቪንቼንሶ ገልጸው ቤኒ በተባለ አካባቢ የጸጥታ ችግር መኖሩን ገልጸው፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት የመንግሥት ተቃዋሚ መሣሪያ ታጣቂ ቡድን በምሽት ከተማ ውስጥ በመግባት ጥቃት የሚፈጽሙ፣ አለፎ አልፎ የግድያ ወንጀል የሚፈጽም መሆኑን አስረድተው በሕዝቡ መካከል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዲስፋፋ የሚያደርጉ አለመረጋጋት፣ ፍርሃት፣ አመጽ እና የግድያ ወንጀሎች መኖራቸውን አስታውቀዋል።
ክቡር አባ ዲ ቪንቼንሶ የአካባቢያቸው ሕዝብ ወደ ቀድሞ ሕይወት እንደሚመለስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝም እንደሚገታ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ክቡር አባ ዲ ቪንቼሶ በመጨረሻም የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሀገሪቱ ውስጥ የተፈጠሩ ቀውሶችን ለማቃለል በርትቶ የሚሰራ መሆኑን ገልጸው፣ የኪንሳሻ ሊቀ ጳጳስ፣ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ የኮሮና ወረርሽኝ አስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታን አሰባሳቢ ብሔራዊ ጽሕፈት ቤት እንዲያስተባብሩ እና እንዲመሩ በመንግሥት የተመረጡ መሆኑን አስታውቀዋል።