በሰሜን አሜሪካ የኒው ዮርክ ከተማ፣ በሰሜን አሜሪካ የኒው ዮርክ ከተማ፣  

270 ሚሊዮን የዓለማችን ስደተኞች በዓመት 689 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገራቸው ይልካሉ ተባለ።

ዓለም አቀፍ የስደተኞች መርጃ ድርጅት በጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. ባወጣው ሪፖርት መሠረት ከዓለማችን 7.7 ቢሊዮን ሕዝብ መካከል 3.5 ከመቶ በስደት የሚኖር መሆኑን ገልጾ ከእነዚህ መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ከሕንድ፣ ሜክስኮ እና ቻይና መሆናቸውን አስታውቋል። ድርጅቱ በማከልም የስድተኞች መዳረሻ አገሮችንም ገልጾ፣ 51 ሚሊዮን ስደተኞችን በማስተናገድ የመጀመሪያ ቦታን የምትይዘው አገር ሰሜን አሜሪካ፣ 13 ሚሊዮን ስደተኞችን በማስተናገድ ጀርመን ሁለተኛ ደረጃን ስትይዝ፣ ሳውዲ አረቢያ ወደ 13 ሚሊዮን የሚጠጋ ስደተኛን በማስተናገድ ሦስተኛ አገር መሆኗን አስታውቋል። የድርጅቱ የዘንድሮ ሪፖርት ከሁለት ዓመት ጋር ሲወዳደር የስደተኛ ቁጥር በ0.1 መጨመሩን አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አብዛኛው ስደተኛ ከእስያ ነው፣

በዓለማችን ውስጥ ከተሰደዱት ሰዎች መካከል 40 ከመቶ በላይ የሚሆኑ ከእስያ አህጉር መሆኑ ሲታወቅ ይህም ቁጥሩን ወደ 112 ሚሊዮን እንደሚያደርስ ሪፖርቱ አስታውቋል። ከፍተኛ የሕዝብ መሰደድ የሚታይባት ሕንድ 17.5 ሚሊዮን ስደተኞች ያሏት ሲሆን ቀጥሎም ሜክስኮ 11.8 ሚሊዮን ስደተኛ ዜጋ ያላት ሲሆን በሦስተኛ ደረጃ ቻይና 10.7 ሚሊዮን ስደተኛ ዜጋ ያላት መሆኑ ታውቋል።

በርካታ ቁጥር ያለው ስደተኛ ወደ ሰሜን አሜሪካ እንደሚጓዝ ሪፖርቱ አስታውቆ ቢሆንም በማደግ ላይ ካሉ አገሮች የሚነሱ ስደተኞች መዳረሻቸውን ወደ ፈረንሳይ፣ ሩስያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ሳውድ አረቢያ የሚያቀኑ መሆናቸውን አስታውቋል። በአፍሪካ፣ እስያ እና አውሮፓ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ከትውልድ አካባቢያቸው ርቀው የማይሄዱ መሆናቸውን የገለጸው ሪፖርቱ ካላቲን አሜሪካ፣ ከካረቢያን አገሮች እና ከሰሜን አሜሪካ የሚሰደዱት ስደተኞች ከተወለዱበት አገር ወጥተው ወደ ሌሎች አገሮች የሚሄዱ መሆናቸውን አስታውቋል። የአፍሪካን የስደተኞች ሁኔታን የተመለከተው ዓመታዊ ሪፖርት እንዳስታወቀው ከአፍሪካ አገሮች ውስጥ ከፍተኛ የስደተኛ ቁጥርን በማስመዝገብ የታወቁት አገሮች ግብጽ፣ ሞሮኮ እና ደቡብ ሱዳን ሲሆኑ ደቡብ አፍሪካ በርካታ የአገር ውስጥ ስደተኛ የሚገኝባት አገር መሆኗ ታውቋል።

የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣

በየጊዜው በሚነሱ አመጾች እና ጦርነቶች ምክንያት በርካታ ተፈናቃይ ያሉባቸው አገሮች ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ፣ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ፣ ሚያንማር፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶርያ እና የመን መሆናቸው ታውቋል። ባለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ 2018 ዓ. ም. ብቻ በዓለም ዙሪያ የተመዘገበው የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ቁጥር 41.3 ሚሊዮን መድረሱን ዓለም አቀፍ የስደተኞች መርጃ ድርጅት አስታውቆ ይህም እስካሁን ከተነዘገበው ቁጥር በልጦ መገኘቱን አስታውቋል። ባለፉት ዘጠኝ ዓመታን በተነሱ አመጾች እና ጦርነቶች ምክንያት ሶርያ 6.1 ሚሊዮን የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ያለባት አገር ስትሆን ኮሎምቢያ 5.8 ሚሊዮን፣ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ 3.1 ሚሊዮን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በመያዝ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን መያዛቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት አስታውቋል። ከትውልድ አገራቸው ወጥተው ወጥተው ከሚሰደዱ 26 ሚሊዮን የዓለም ስደተኞች መካከል ሶርያ ከ6 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች እንዳላት፣ ቀጥሎም አፍጋኒስታን 2.5 ሚሊዮን የስደተኛ ቁጥር ያላት መሆኑን ሪፖርቱ አስታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
04 December 2019, 17:04