ወይዘሮ ኤሊሴ ሊንድኬስት፣ ወይዘሮ ኤሊሴ ሊንድኬስት፣ 

ወይዘሮ ኤሊሴ ሊንድኬስት ዳግማዊት ማዜር ተሬዛ ናቸው ተባሉ።

 በስዊዲን ዋና ከተማ ስቶክሆልም የሚገኙ ሴተኛ አዳሪዎች ከገቡበት አስከፊ ሕይወት ወጥተው ትክክለኛ ማሕበራዊ ሕይወትን እንዲኖሩ የተቻላቸውን ሁሉ በማድረግ ላይ የሚገኙ ወይዘሮ ወይዘሮ ኤሊሴ ሊንድኬስት ዳግማዊ ማዘር ተሬዛ ናቸው ተባሉ። ወይዘሯ በሕጻንነት እድሜአቸው ለተለያዩ ስቃዮች የተጋለጡ፣ አልኮል መጠጦችን እና አደንዛዥ ዕጽ የሚጠቀሙ እንደነበር ታውቋል። ዛሬ ግን ከዚያ መከራ ሁሉ ወጥተው በስዊድን ዋና ከተማ በስቶክሆልም ዋና ዋና መንገዶች ላይ የሚገኙ ሴተኛ አዳሪዎችን ወደ ትክክለኛ ማሕበራዊ ሕይወት እንዲመለሱ በማድረግ የሚታወቁ እና ዳግማዊ ማዜር ተሬዛ የሚል ስም የተሰጣቸው መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቫቲካን የዜና አገልግሎት ባልደረባ ካርሎታ ስሜድዝ ከላከችልን ዘገባ ለመረዳት እንደተቻለው ወይዘሮ ኤሊሴ በሕጻንነት እድሜአቸው ብዙ መከራዎችን ማለፋቸውን ገልጻ አሁን በሕይወታቸው ሰላምን እና ደስታን አግኝተው ሕይወታቸውን በመምራት ላይ መሆናቸዋን ገልጻለች። ወይዘሮ ኤሊሴ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰላምታን ለማቅረብ ያለፈአው ግንቦት ወር ወደ ሮም መጥተው እንደነበር ታውቋል። ወደ ሮም የመጡበት ዋና ዓላማ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም ለሚያደርጉት ከፍተኛ ጥረት ምስጋናቸውን ለማቅረብ መሆኑን የቫቲካን የዜና አገልግሎት ባልደረባ ካርሎታ ስሜድዝ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወይዘሮ ኤሊሴን ባለፈው ግንቦት ወር በቫቲካን ባገኟቸው ጊዜ ባደረጉት ንግግር ወይዘሮዋ በስቶክሆልም ከተማ አውራ ጎዳናዎች የሚገኙት ሴትኛ አዳሪዎች ከወደቁበት አስከፊ ማሕበራዊ ሕይወት ለማውጣት የሚያደርጉትን ጥረት አድንቀው ማስጋናቸውንም አቅርበውላቸዋል። በከተማይቱ ለሚገኙ ሴትኛ አዳሪዎች እናት ሆነው በመቅረብ፣ ከወደቁበት ችግር ለማላቀቅ ላለፉት ሀያ ዓመታት የምክር አገልግሎት ሲያበረክቱ መቆየታቸው ታውቋል።

አስደንጋጭ የሕጻንነት ሕይወት፣

በስዊድን አገር በምትገኝ ትንሽ መንደር የተወለዱት ወይዘሮ ኤሊሴ ከአምስት አመት ዕድሜ ጀምሮ የመከራ ሕይወትን የኖሩ ሲሆን በየቀኑ ጾታዊ ጥቃት ይደርስባቸው እንደነበር ታውቋል። ከአካባቢው ሕዝብ ይደርስ  የነበረው ማስፈራሪያ ብዙ እንደነበር የገለጹት ወይዘሮ ኤሊሴ ከፍራቻ የተነሳ ከጎረቤቶቻቸው በኩል ወደ ቤት መጥተው ምግብ እንዲበሉ ሲጋበዙ የማይመጡ መሆኑን ገልጸው የፍርሃታቸው ዋና ምክንያት በሰዎች ላይ እምነትን በማጣት መሆኑ አስረድተዋል። ከወላጅ እናታቸው ጭምር ፍቅር የተነፈጋቸው ወይዘሮ ኤሊሴ በትምሕርት ቤትም ቢሆን ከልጆች ተነጥለው እንዲቀመጡ፣ ተማሪዎች በዕረፍት ጊዜአቸው ለጨዋታ ሲወጡ እርሳቸው ግን ከክፍል እንዳይወጡ መደረጋቸውን አስታውሰዋል። ወይዘሮ ኤሊሴ እንደገለጹት ከአባታቸው ይታይ የነበረው ጥቂት የፍቅር ስሜት ባይኖር ኖሮ እሳክሁን በሕይወት መቆየት ባልቻልኩ ነበር ብለዋል። ዕድሜአቸው 10 ዓመት በሆናቸው ጊዜም ቢሆን ሕይወታቸው ከባድ እንደነበር ያስታወሱት ወይዘሮ ኤሊሴ፣ አባታቸው ካረፉ በኋላ ቤት ለማስተዳደር የመጡት የእንጀራ አባታቸው ሰካራም እና ግፍን እንደሚፈጸሙባቸው ያስታወሱት ወይዘሮ ኤሊሴ በአንድ ወቅት ሕይወታቸውን ለማጥፋት መነሳታቸውንም አስታውሰዋል።

እጅግ ቆንጆ ነሽ?

ዕድሜአቸው 14 ዓመት በሞላቸው ጊዜ ከቤት ወጥተው መጥፋታቸውን ያስታወሱት ወይዘሮ ኤሊሴ ወደ አንድ ቤተ ሰብ ዘንድ ተጠግተው መኖር እንደጀመሩ አስታውሰው ይህ ቢሆንም የያዛቸው ፍርሃት እንዳልለቀቃቸው ገልጸዋል። በሕይወታቸው መካከል ይደረሳቸው የነበረው ስቃይ ዛሬ በሌሎች ልጃገረዶችም እንደሚደርስ የተገነዘቡት ከዚህ ዕድሜ ጀምሮ እንደነበር ወይዘሮ ኤሊሴ ተናግረዋል። በእንግድነት ላስጠጓቸው ቤተሰብ የቤት ውስጥ ሠራተኛ ሆነው መስራታቸውን ያስታወሱት ወይዘሮ ኤሊሴ ያ ቤተሰብም በሴተኛ አዳሪነትን ስራ ላይ እንዲሰማሩ ማስገደዱን ገልጸዋል ከደንበኞቻቸው በኩል በተፈጸመው የጭካኔ ተግባር የተነሳ ስራውን ማቆማቸውን በማስታወስው ገልጸዋል።

ዛሬ አንድ ልጃገረድ ለቀጣሪዋ ይህን ሥራ መልቀቅ እፈልጋለው ብትል የሞት ቅጣት እንደሚጠብቃት ያስታወሱት ወይዘሮ ኤሊሴ አሠሪዎቻቸውም ተቆጥተው ከቤት ማባረራቸውንም አስታውሰዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን፣

ራስን በሚጎዱ የሕይወት አቅጣጫዎች ብቻ ተሰማርተው እንደነበር ያስታወሱት ወይዘሮ ኤሊሴ ከእለታት አንድ ቀን በሰላም እና በፍቅር የተሞላውን መልክ መመልከታቸውን ገልጸው እ. አ. አ. 1994 ዓ. ም. በአንድ እርዳታ መስጫ ማዕከል ውስጥ ጥገኛ ሆኜ ኖሬአለሁ ብለዋል። በዚህ ማዕከል ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች በሙሉ እንደሚጠሏቸው የገለጹት ወይዘሮ ኤሊሴ ዘወትር ይናደዱ እንደነበር ገልጸዋል። ተጠግተው ከሚኖሩበት ማዕከል የሚኖሩ ሰዎች የሚያሳዩት የፈገግታ እና የደስታ ስሜት ፈጽሞ እንግዳ ነገር የሆነባቸው ወይዘሮ ኤሊሴ ምን ዓይነት መድሃኒት እንደሚወስዱ መጠየቃቸውን አስታውሰዋል። ምንም ዓይነት መድሃኒት እንደማይወስዱ የተነገራቸው ወይዘሮ ኤሊሴ አብሮ አቸው የነበሩ ሰዎች በማዕከሉ በሚገኘው ጸሎት ቤት በመገኘት የሚጸልዩ መሆናቸውን ገልጸዋል። በወቅቱ ስለ እግዚአብሔር ምንም ዓይነት እውቀት እንዳልነበራቸው ተናግረው ቤተክርስቲያን ሲባል የሞት ሥፍራ ይመስላቸው እንደነበር ገልጸዋል። ከዕለታት አንድ ቀን በማዕከሉ ውስጥ በውሃ ሳይሆን በብርሃን እና በውስጣዊ ሰላም መታጠባቸውን የገለጹት ወይዘሮ ኤሊሴ ለመዳኔ ምክንያት የሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ብለው ከዚያን ጊዜ ወዲህ እንደገና መወለዳቸውን ያስታወሱት ወይዘሮ ኤሊሴ ከ 25 ዓመታት ወዲህ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠኝ አዲስ ሕይወት እየኖርኩ የፍቅሩንም ሃያልነት ለማወቅ ችያለሁ ብለዋል።

ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሕረት ድነት የለም፣

በማዕከሉ ውስጥ የነበሩ መንፈሳዊ አባት በእምነት ጎዳና ላይ ሌላ ተጨማሪ እርምጃን እንድወስድ ጠይቀውኛል ያሉት ወይዘሮ ኤሊሴ ይህም ምሕረትን እንዳደርግ የሚል ነበር ብለዋል። ሌሎች ሰዎች በፈጸሙብኝ በደል ምን ምሕረት እንዳደርግ ይጠበቅብኛል በማለት የቁጣ ስሜት ቢይዘኝም ለበደሉኝ በሙሉ ምሕረትን የማላደርግ ከሆነ ምህረት እንደማይደረግልኝ ተነግሮኛል ብለዋል። ከረጅም ጊዜ ውስጣዊ ትግል በኋላ ከዚህ በፊት የበደሉኝን በሙሉ ለእናቴንም ጭምር ምሕረት አድርጌላታለሁ ብለዋል።

የሴተኛ አዳሪዎች ታዳጊ፣

ከ20 ዓመታት ወዲህ በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም አውራ ጎዳናዎች በምሽት እየተዘዋወሩ በሴትኛ አዳሪነት ሥራ ላይ የተሰማሩትን ልጃገረዶች በመጎብኘት፣ ይህ አገልግሎት በሕይወት ዘመኔ እንዳበረክት የተጠራሁበት ነው በማለት ገልጸዋል።

የወይዘሮ ኤሊሴ አገልግሎት በስቶኮልም ከተማ ውስጥ በሴትኛ አዳሪነት ለተሰማሩት በቁጥር በርካታ ልጃገረዶች የእናትነትን መንፈስ በማሳየት፣ በቅርብ ሆነው በማዳመጥ፣ የሚበሉትን እና የሚጠጡትን ማቅረብ፣ በቀዝቃዛ ወራትም ከብርድ መከላከያ የሚሆን ልብሶችን በማቅረብ ማገዝ መሆኑ ታውቋል። በሴተኛ አዳሪነት ሥራ ላይ የተሰማሩትን ልጃገረዶች ከአስከፊ እና አስቸጋሪ የሕይወት መንገድ መመለስ ስችል ያ የላቀ ደስታን የሚያስገኝ ሽልማት ነው ብለው ለእነዚህ ልጃገረዶች የሚያስፈልገው እንዲጽናኑ ማበረታታት፣ ብቻቸውን እንዳልሆኑ ማስረዳት እና ከሰዎች ዘንድ ፍቅር እንደማይ ጎድልባቸው መንገርን ነው ብለዋል።

ወይዘሮ ኤሊሴ እ. አ. አ. በጥቅምት 18/2016 ዓ. ም. በአውሮጳ ታስቦ በዋለው ጸረ ሰዎች ዝውውር ቀን በፓላመንት ፊት ቀርበው ንግግር እንዲያደርጉ መጋበዛቸው ታውቋል። በዕለቱ ባቀረቡት ንግግራቸው እንደገለጹት ችግሩን ለማቃለል የአውሮጳ አገሮች መንግሥታዊ ተቋማት ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸው የአውሮጳ ሕብረት አባል አገሮች ይህን በሰብዓዊ ፍጡር ላይ የሚደርሰውን ጥቃት የሚያስቆም ቆራጥ ውሳኔን አውጥተው ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ማሳሰባቸው ይታወሳል። ዕድሜዬ 90 እስከሚሆን ድረስ ይህ ችግር ተወግዶ እንደሆነ ለማረጋገጥ ወደ አውሮጳ ሕብረት ጉባኤ እመለሳለሁ ማለታቸውም ይታወሳል።                  

08 July 2019, 16:54