ስደተኞች  በሊቢያ ወደብ ላይ ስደተኞች በሊቢያ ወደብ ላይ  

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስደተኞች ድጋፍ እና የጉዞ ዋስታና እንዲሰጣቸው ጠየቀ።

ከፍተኛ ሃላፊነት እንዲኖር ያስፈልጋል ያለው፣ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት፣ የአካባቢው አገሮች የተቀናጀ የሃላፊነት ድርሻ መኖር እንደሚያስፈልግ፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚገታበትን ደንብ በጋራ ሆነው እንዲያወጡ እና ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ፣ በባሕር ላይ ይሁን በየብስ አደጋ ለሚያጋጥማቸው ስደተኞች አስቸኳይ እርዳታን ማቅረብ፣ ስደተኞች የሚገቡባቸውን ወደቦች ወስነው በቂ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጎርጎሮሳዊው 2018 ዓ. ም. ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፣ የሜዲተራንያንን ባሕር ለማቋረጥ ሲሞክሩ የሚሞቱ የፍልሰተኞች ቁጥር መቀነሱን ቢያስታውቅም ፍልሰተኞች ከሚጓዙበት ከሌሎች የጉዞ መስመሮች ጋር ሲመዛዘን የሟች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን አስታውቋል። የሜዲተራንያንን ባሕር ከሚያቋርጡት ፍልሰተኞች መካከል በቀን በአማካይ ስድስቱ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ከፍተኛ ኮሚሽን አስታውቆ፣ የጉዞ መስመሩም ከሌሎች ይልቅ እጅግ አደገኛ መሆኑን ገልጿል።

በጎርጎሮሳዊው 2018 ዓ. ም. ከ2000 በላይ ፍልሰተኞች ሞተዋል፣

በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ከፍተኛ ኮሚሽን እንደገለጸው ባለፈው የጎርጎሮሳዊው 2018 ዓ. ም. የሜዲተራንያንን ባሕር ሲያቋርጡ የሞቱት የፍልሰተኞች ቁጥር 2275 እንደሚሆን ሲገመት፣ የአውሮጳ አገሮች ድንበሮችን ለማቁረጥ ሲሞክሩ የሞቱት ቁጥር 136 መሆናቸውን ገልጿል። ድረጅቱ በተጨማሪም ባለፈው የጎርጎሮሳዊው ዓመት ወደ አውሮጳ መድረስ የቻሉት፣ የጥገኝነት ጠያቂዎችና ፍልሰተኞች ጠቅላላ ቁጥር 139,300 እንደሆነ ገልጾ፣ ከእነዚህም መካከል 116,647 በባሕር፣ የተቀሩት 22,653 ደግሞ በየብስ የተጓዙ መሆናቸውን አስታውቋል። ይህ አሃዝም ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የመዲተራንያን ባሕር ማቋረጥ ከቻሉት የፍልሰተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑን ገልጾ፣ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር የተመዘገበው በጎርጎርሳዊው 2015 ዓ. ም. 1.015,877 ሲሆን ሕይወታቸውን ያጡትም 3,771 መሆናቸውን ገልጿል።

የሰውን ሕይወት ማዳን ግዴታ ነው፣

በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፊሊፖ ግራንዲ እንደገለጹት በአደጋ ላይ የሚገኝ የሰውን ሕይወት ከሞት አደጋ ማትረፍ ምርጫ ወይም የፖለቲካ ድርድር የሚደረግበት ሳይሆን ግዴታ ነው ብለዋል። የስደተኞች መርጃ ድርጅት ከፍተኛ ኮሚሺን ኮሚሽነር አቶ ፊሊፖ ግራንዲ በማከልም፣ በረጅም ጊዜ ዕቅድ ተግባራዊ የሚሆን እና ለእያንዳንዱ የሰው ልጅ ሕይወት ክብር ቅድሚያን የሚሰጥ የክልላዊ መንግሥታት ትብብር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የሊቢያ በጣም አደገኛ የጉዞ መስመር፣

በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት በዓመታዊ ሪፖርቱ እንደገለጸው፣ ፍልሰተኞች የሚጠቀሙበት እጅግ አደገኛው የጉዞ መስመር በሊቢያ በኩል ያለው እንደሆነ ገልጾ፣ ባለፈው የጎርጎሮስዊው 2018 ዓ. ም. ወደ አውሮጳ ለመድረስ የሜዲተራንያንን ባሕር ጉዞ ከሚጀምሩት 14 ፍልሰተኞች መካከል 1ዱ በባሕር ላይ ሕይወቱን እንደሚያጣ አስረድቶ፣ በሊቢያ የሰደተኞች ማቆያ ጣቢያ ውስጥ የሚታየው የፍልሰተኞችም አያያዝ እጅግ አሰቃቂ እንደሆነ ገልጿል።

የፍልሰተኞች አስደንጋጭ ጉዞ፣

በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት በዓመታዊ ሪፖርቱ ይፋ እንዳደረገው ፍልሰተኞች እና ተፈናቃዮች በጉዞአቸው ወቅት አሰቃቂ ግርፋት፣ ወሲባዊ ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው ገልጿል።  

ስፔን እና ግሪክ ፍልሰተኞች የሚያርፉባቸው የመጀመሪያ አገሮች ናቸው፣

ካለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ 2018 ዓ. ም. ወዲህ ፍልሰተኞቹ በቅድሚያ የሚያርፉባቸው ወይም የፖለቲካ ጥገኝነት የሚጠይቁባቸው አገሮች መቀየራቸውን የገለጸው የስደተኞች መርጃ ድርጅት ሪፖርት እንዳስታወቀው፣ ኢጣሊያ ወደ ግዛቷ የሚገቡ የፍልሰተኞች ቁጥር 80 ከመቶ እንደቀነሰ ማስታወቋን ገልጾ፣ በጎርጎሮስዊው 2017 ዓ. ም. 119,400 የነበረው የፍልሰተኞች ቁጥር ባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ 2018 ዓ. ም. ወደ 23,440 ዝቅ ማለቱን አስታውቋል። ነገር ግን ወደ ስፔን ግዛት የሚገባ የፍልሰተኛ ቁጥር 131 ከመቶ መድረሱንና ይህም እንደ ጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ. ም. 28,300 የነበረው ባለፈው የጎርጎሮሳዊው 2018 ዓ. ም. ወደ 65,400 መድረሱን ሪፖርቱ ገልጿል። ወደ ግሪክ የሚገባው የፍልሰተኛ ቁጥር እድገት ማሳየቱን ያስታወቀው የድርጅቱ ሪፖርት፣ በጎርጎሮስዊው 2017 ዓ. ም. 35,400 የነበረው የፍልሰተኞች ቁጥር ባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ 2018 ዓ. ም. ወደ 50,500 ከፍ ማለቱን ገልጿል።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፍልሰተኛ ቁጥር፣ ሞሮኮ እና ጊኒያ ናቸው፣

ፍልሰተኞቹ የሚነሱባቸው አገሮችን የዘረዘረው፣ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ከፍተኛ ኮሚሽን፣ ወደ ስፔን ከሚደርሱ ፍልሰተኞች መካከል 13,000 ከሞሮኮ፣ 13,000 ከጊኒያ፣ 10,300 ከማሊ፣ 5,800 ከአልጀሪያ፣ 5,300 ከአይቮሪ ኮስት ሲሆኑ ወደ ግሪክ ከሚደርሱት መካከል 9,000 ከአፍጋኒስታን፣ 7,900 ከሶርያ፣ 5,900 ከኢራቅ፣ 1,800 ከኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ፣ 1,600 ከፍልስጤም፣ ወደ ኢጣሊያ የሚደርሱትም 5,200 ከቱኒዚያ፣ 3,300 ከኤርትራ፣ 1,700 ከኢራቅ፣ 1,600 ከሱዳን፣ 1,600 ካፓክስታን መሆናቸውን ገልጿል።

የፍልሰታቸው ዋና ምክንያት አልተቀረፈም፣

ሰዎች አገራቸውን ለቅቀው ወደ አውሮጳ የሚሰደዱባቸው ምክንያቶች በጎርጎሮርሳዊው 2019 ዓ. ም. ቢሆን እንዳልተቀረፉ የገለጸው፣ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ሪፖርት፣ የሰደታቸው ቀዳሚ ምክንያቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ አመጽ እና ድህነት መሆናቸውን ገልጾ ፍልሰተኞቹ የሚገቡባቸው አገሮች መንግሥታት የፍልሰተኞች የጥገኝነት ጥያቄ መብታቸውን እንዲያከብሩ፣ ሰብዓዊ እርዳታን እንዲያቀርቡ፣ ለሕይወታቸው ከለላን እንዲያደርጉ፣ ጠባቂ ለሌላቸው ሕጻናት እንዲንከባከቧቸው፣ ወሲባዊ ጥቃት ለተፈጸመባቸው የሕክምና እርዳታን እንዲያደርጉ፣ ህጋዊ ኣና ዋስትና ያለውን የጉዞ ሥርዓት በመዘርጋት ከሞት አደጋ የሚተርፉበትን መንገድ እንዲያመቻቹ ጠይቋል።

ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚያስቆም የጋራ ሕግ ይርቀቅ፣

ከፍተኛ ሃላፊነት እንዲኖር ያስፈልጋል ያለው፣ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት፣ የአካባቢው አገሮች የተቀናጀ የሃላፊነት ድርሻ መኖር እንደሚያስፈልግ፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚገታበትን ደንብ በጋራ ሆነው እንዲያወጡ እና ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ፣ በባሕር ላይ ይሁን በየብስ አደጋ ለሚያጋጥማቸው ፍልሰተኞች አስቸኳይ እርዳታን ማቅረብ፣ ስደተኞች የሚገቡባቸውን ወደቦች ወስነው በቂ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።                        

31 January 2019, 16:10