ለማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ ሰላም ጸሎት፣   ለማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ ሰላም ጸሎት፣  

በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ የጸሎትና የሐዘን ቀን ታወጀ።

የመካከለኛው አፍሪቃ ርፓብሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በጎ ፈቃድ ላላቸው በሙሉ ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ በመሣሪያ ታጣቂዎች ጥቃት ሕይወታቸውን ያጡትን በሙሉ በጸሎታቸው እንዲያስታውሱ አደራ ብለው፣ ሕዳር 23 ቀን 2011 ዓ. ም. በአገሪቱ በሙሉ በአመጽ ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡት የመታስቢያ ቀን ሆኖ እንዲታወጅ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በአገሪቱ የሚከሰቱ አመጾችና ኢፍትሃዊነት እንዲያከትም አሳስበዋል። በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ የሚገኙ ሚሲዮናዊ አባ አውረሊዮ ጋዜራ ከቫቲካን ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸዋል። በያዝነው የአውሮጳዊያን 2018 ዓ. ም. በታጣቂ ሃይሎች የተገደሉ የካቶሊካ ቤተክርስቲያን ካህናት ቁጥር ቢያንስ አምስት እንደሚደርስ ጠቅሰው የሃገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት በመልዕክታቸው አማካይነት፣ ክርስቲያኖችና የሌሎች እምነቶች ተከታዮች በሙሉ በጋራ ሆነው እርቅን ለማውረድ ጥረት እንዲያደርጉ መማጸናቸውን ገልጸዋል።

ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን የጥቃቱ ኢላማ ሆናለች፣

በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፓብሊክ፣ የቦሳንጎዋ ሃገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ኔስቶር ደዚሬ በሃገሪቱ እየደረሰ ያለውን መከራ አስመልክተው ፊደስ ለተባለ የዜና ማሰራጫ ማዕከል እንደገለጹት፣ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በሃገሪቱ ሰላምን፣ በሕዝቦች መካከልም አንድነትንና ወንድማማችነትን ለማሳደግ ከምታደርገው ጥረት፣ በጦርነቱ ለተጎዱት ሕዝቦች የምታቀርበው የእርዳታ አገልግሎት በግልጽ የሚታይ ሆኖ እያለ ነገር ግን የጥቃቱ ኢላማ መሆንዋን ገልጸው ካህናት መገደላቸውን፣ ቤተክርስቲያኖች መቃጠላቸውን፣ ቅዱሳት ምስሎች መዘረፋቸውንና መውደማቸውን ገልጸዋል። እነዚህ ጥቃቶች በሙሉ፣ በሃገሪቱ የእምነት ቀውስ እንዲመጣ ለማድረግ በተነሱ ጸረ ሰላም ሃይሎች የሚሰነዘሩ ጥቃቶች እንደሆኑ መወሰድ አለባቸው ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ወታደሮች ሃላፊነት፣

ብጹዕ አቡነ ኔስቶር ደዚሬ ፊደስ ለተባለው የዜና ማሰራጫ ማዕከል እንደገለጹት ከሁሉም የከፋው የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ወታደሮች፣ በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙትን ተፈናቃዮች እንዲያጠቁ፣ የተጠለሉበትንም ቤተክርስቲያን እንዲያቃጥሉ ለእስላማዊ ሚሊሻዎች ነጻነት መስጠታቸውን አስረድተዋል። ከዚህ በፊት ሊቀ ጳጳስ ደዎዶኔ እንደገለጹት መሣሪያ ታጣቂዎቹ በተፈናቃዩ ሕዝብ ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ማስፈራራትም የታከለበት እንደሆነ ገልጸው የአገሪቱ መንግሥትም ይሁን ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ግድያና ስቃይ የሚደርስበትን ሕዝብ ከአደጋ የመጠበቅና የመከላከል ብቃት ያንሳል ማለታቸው ይታወሳል። በብዙ የአገሪቱ ክፍሎች የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እጅግ አነስተኛ በመሆኑ በርካታ ሕጻናት ለረሃብና ለበሽታ መዳረጋቸው ታውቋል።

ከመካከለኛው አፍሪቃ ሪፓብሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የወጣው ዜና እንዳመለከተው፣ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት በመጀመሪያ አንቀጹ እንደሚገልጸው ሰብዓዊ ፍጡር ቅዱስ፣ ክብሩም የማይጣስ መሆኑን አስታውሰው፣ ነገር ግን በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች ሕገ መንግሥቱን እንደሚቃረኑ ገልጸዋል። በመሆኑ የመካከለኛው አፍሪቃ ርፓብሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በጎ ፈቃድ ላላቸው በሙሉ ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ በመሣሪያ ታጣቂዎች ጥቃት ሕይወታቸውን ያጡትን በሙሉ በጸሎታቸው እንዲያስታውሱ አደራ ብለው፣ ሕዳር 23 ቀን 2011 ዓ. ም. በአገሪቱ በሙሉ በአመጽ ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡት የመታስቢያ ቀን ሆኖ እንዲታወጅ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

04 December 2018, 16:59