PAKISTAN-RELIGION-COURT PAKISTAN-RELIGION-COURT 

በፓክስታን ለተቃውሞ ከወጡት መካከል 150 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነገረ።

የአሲያ ቢቢን መፈታት በመቃወም ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡት የአክራሪ እስላማዊ ፓርቲ ደጋፊዎች ላለፉት ሦስት ቀናት በመላው የአገሪቱ ክፍሎች ባካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች መንገዶችን ዘግተዋል፣ በርካታ መኪኖችን በእሳት አጋይተዋል ተብሏል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የፓክስታን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ. ም. የክርስትና እምነት ተከታይ አሲያ ቢቢን ከእስር ነጻ ማሰናበቱን በመቃወም ለሰልፍ ከወጡት መካከል 150 ሰዎች በመንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች ተይዘው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል። የፓክስታን መንግሥት ነጻ ያሰናበታት የክርስትና እምነት ተከታይ አሲያ ቢቢ፣ የእስምናን ሕይማኖት አንቋሽሻለች፣ የነብዩ መሐመድን ስም አጥፍታለች በሚል ወንጀል ክስ ተመስርቶባት የሞት ፍርድ የተፈረደባት ሲሆን፣ ለስምንት ዓመታትም በእስር መቆየቷ ታውቋል። የአሲያ ቢቢን መፈታት በመቃወም ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡት የአክራሪ እስላማዊ ፓርቲ ደጋፊዎች ላለፉት ሦስት ቀናት በመላው የአገሪቱ ክፍሎች ባካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች መንገዶችን ዘግተዋል፣ በርካታ መኪኖችን በእሳት አጋይተዋል ተብሏል። ለአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአቃቤ ሕጉ ያቀረበውን ይግባኝ ተከትሎ መንግስት፣ አሲያ ቢቢ ከአገር እንዳትወጣ በማገዱ ምክንያት የተቃውሞ ሰልፉ መቀዝቀዙ ታውቋል።

የአሲያ ቢቢ ባለቤት አሺክ ማሽ፣ ለአሜርካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ለእንግሊዟ ጠቅላይ ሚንስትር ተረዛ ሜይ እና ለካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጃስቲን ትሩዶ የፖለቲካ ጥገኝነት ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው እንዲሰጣቸው ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል። አቶ አሺክ ማሽ ለእነዚህ ሦስት መንግሥታት መሪዎች በቪዲዮ ምስል በኩል ባቀረቡት አቤቱታ እርሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከሚደርስባቸው ጥቃት ለመከላከል የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉላቸው ተማጽነዋል።

የሞት ፍርድ ተፈርዶባት የነበረው ነገር ግን በአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ በነጻ የተለቀቀች አሲያ ቢቢ አሁን ያለችበት ስፍራ በውል እንደማይታወቅ፣ ጠበቃዋ የነበሩት ሳይፉል ማሉክም አገር ለቀው መውጣታቸው ታውቋል። ለሕይወታቸው ስጋት ስላደረባቸው የተወለዱበትን አገር ለቀው እንዲሰደዱ የተገደዱት የአሲያ ቢቢ ጠበቃ አውሮጳ ውስጥ እንደሚገኙና ባሉበት አገር ሆነው የአሲያ ቢቢን ጉዳይ መከታተል እንደሚፈልጉ መግለጻቸው ታውቋል።

የአውሮጳ ፓርላማ ትብብር፣

የአውሮጳ ፓርላማ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ አንቶኒዮ ታያኒ ለፓክስታን መንግሥት ባቀረቡት ጥያቄ አሲያ ቢቢን ነጻ እንዲያደርግ፣ በአሲያ ቢቢ እና መላ ቤተሰቦችዋ ላይ ከአክራሪ እስላማዊ ፓርቲ ደጋፊዎች ከሚሰነዘር ጥቃትና አደጋ እንዲከላከል አሳስበዋል። የአውሮጳ ፓርላማ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ አንቶኒዮ ታያኒ በማከልም በአገሪቱ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ፣ በአሲያ ቢቢ ላይ እንደ ጥፋት የተቆጠረባት ነገር ቢኖር የክርስትና እምነት ተከታይ መሆኗ ብቻ ነው ብለዋል።        

የአሲያ ቢቢ ከእስር መፈታት ለፓክስታን የክርስትና እምነት ተከታዮች ድል ነው ባይባልም የፓክስታንን መንግሥት ትልቅ ዋጋን ያስከፈለ፣ ፓክስታንን ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ ትኩረት የሳበ ምሳሌ እንደሆነ፣ በኢጣሊያ የፓክስታን ክስቲያቲያኖች ሕብረት መስራች የሆኑት ፕሮፌሰር ሞቢን ሻዲድ ያስረዱት ሲሆን በፓክስታን መንግሥት የተወሰደው እርምጃ በፓክስታን ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮች በሚገኙት የተለያዩ የእምነት ተቋማት መካከል ውይይት እንዲደረግ መንገድን የከፈተ አጋጣሚ እንደሆነ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ መናገራቸው ይታወሳል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን ተጫወት የሚለውን ምልክት ይጫኑ
05 November 2018, 08:47