Camerun manifestazioni a Bamenda Camerun manifestazioni a Bamenda 

በካሜሩን የሐይማኖት መሪዎች ለሰላም የሚበጅ ውይይት አካሄዱ።

በነሐሴ 23 ቀን 2010 ዓ. ም. ተጀምሮ ትናንት በተጠናቀቀው የሃይማኖት መሪዎች ስብሰባ፣ በሃገሪቱ የተፈጠረውን ችግር አስወግዶ ሰላምን ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በካሜሩን እየተስፋፋ የመጣውን የመገንጠል ጥያቄን ተከትሎ የተነሳውን አመጽ ለማስቆም በማለት በሁለት የእምነት መሪዎች መካከል ወይይት መጀመሩ ታውቋል። የመገንጠልን ጥያቄ ከሚያቀርብ የእንግሊዘኛ ተናጋሪ ክፍለ ሀገር ነጻ አውጭ እንቅስቃሴ መሪዎችና ከመንግሥት ጋር በሚደረገ ውይይት የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን በመወከል የተገኙት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ክርስቲያን ዊጋን ቱሚ መሆናቸው ታውቋል።

ነሐሴ 23 ቀን 2010 ዓ. ም. የተጀመረው የሁለት ቀናት ስብሰባ የተካሄደው በካሜሩን የደቡብ ምዕራብ፣ በቡያ ክፍለ ሃገር መሆኑ ታውቋል። የስብሰባው ዋና ዓላማ፣ የመገንጠልን ጥያቄ በሚያቀርብ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ ክፍለ ሀገር ነጻ አውጭ እንቅስቃሴ እና በመንግሥት መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ከቅርብ ወራት ወዲህ በሀገሪቱ የተፈጠረውን ቀውስ ለማርገብ የተጀመረውን ውይይት ለማጠናከር ነው ተብሏል።

የምዕራብ አፍሪቃ አገር የሆነችው ካሜሩን፣ ከረጅም ዓመታት ወዲህ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ ክፍለ ሃገርና  የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ክፍለሃገር በመባል ለሁለት የተከፈለች አገር መሆኗ ይታወቃል።  በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የኖረው ክፍለ ሀገር ከጠቅላላው የሀገሪቱ ክፍል 20 ከመቶ የያዘ ሲሆን በመንግሥት አስተዳደርና በሃብት ክፍፍል ፍትሃዊነት ይጎላል በማለት ብሶት ሲያሰማ እንደቆየ ታውቋል። በዚህም ምክንያት በ2008 ዓ. ም. የተቀሰቀሰው የመጀመሪያው አመጽ በብዙ ቁጥር ለሚገመቱ ሰላማዊ ዜጎች ሞትና ለሌሎች በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች መታሰራቸው ምክንያት ሆኗል የብሏል። የአመጹም ዋና ምክንያት በሃገሪቱ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች በሙሉ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ዳኞችን በመሰየም የፕሬዚደንት ፖል ቢያ መንግሥት በሕዝቡ መካከል አድልዎን በመፍጠሩ የተነሳና በክፍለ ሃገሩ የሚገኙ የሕግ ጠበቆች በሙሉ የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ ተማሪዎችንና መምሕራንን በማስተባበር በቀሰቀሱት አመጽ እንደነበር ታውቋል።

ከዚህ በፊት ከታዩት ቀውሶች በላይ ነው፣

ካሜሩን ነጻነቷን ከተቀዳጀችበት ከ1953 ዓ. ም. ወዲህ በሁለቱ ግዛቶች መካከል በሚገኘው ድንበር አካባቢ ሲካሄዱ የቆዩት ሰላማዊ ሰልፎች ጊዜ በጨመረ ቁጥር ወደ ከፋ አመጽ በመሸጋገር ካሜሩንን እጅግ እየጎዳት መምጣቱ ታውቋል። ባለፉት ወራት ውስጥ በተካሄዱት አመጾች ብዙ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው፣ ቢያንስ 16 የመንግሥ ወታደሮችና የፖሊስ አዛዦች መገደላቸው ታውቋል። ከቦኮ ሃራም እስላማዊ ታጣቂ ቡድን የሚቃጣውን ጥቃት ለመከላከል በማለት በሰሜናዊዉ የሃገሪቱ ግንባር መንግሥት ልዩ ሃይል ማሰማራቱም ታውቋል። በአመጹ ምክንያት 7,500 የሚሆኑ ነዋሪዎች መኖሪያቸውን ለቅቀው ወደ አጎራባች አገር ወደ ሆነችው ናይጀሪያ እንዲሰደዱ የተገደዱ ሲሆን ሌሎች 40,000 የሚሆኑ አካባቢያቸውን ለቅቀው ለመውጣት በዝግጅት ላይ መሆናቸው ታውቋል።

የመንግሥት ወከባ ቀጥሏል፣

በካሜሩን የሚነሳውን የነፃነት ጥያቄን ለማፈን በሚደረግ ጥረት መንግሥት ሃይል ይጠቀማል፣ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ተኩስ በመክፈት ፖሊስ የሃይል እርምጃን ይወስዳል ተብሏል። እስከ 2008 ዓ. ም. ማብቂያ ብቻ በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ እንደታሰረና በአካባቢው በብርቱ የታጠቁ የደህንነት ኃይሎች መሰማራታቸው ታውቋል። ፕሬዚደንት ፖል ቢያ በሃገራቸው የተነሳውን አመጽ ለማስቆም በማለት ከቅርብ ወራት ጀምሮ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ቢነገርም መፍትሄ አልተገኘም ተብሏል። በመንግሥትና በደል ደርሶብኛል በሚለው የእንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ መካከል ችግሩ የተጀመረው ካሜሩን ነጻነቷን ከተቀዳጀችበት ከ1953 ዓ. ም. ጀምሮ እንደሆነና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሃገሪቱ ዋና ከተማን ያውንዴን በማድረግ በማዕከላዊ መንግሥት እንዲተዳደር መደረጉ ሲታወስ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነው 20 በመቶ የሃገሪቱ ክፍል ከመንግሥት በኩል አድልዎ እየደረሰብኝ ነው በማለት ቅሬታን ሲያሰማ ቆይቷል ተብሏል።

የሃይማኖት መሪዎች ስብሰባ፣

በነሐሴ 23 ቀን 2010 ዓ. ም. ተጀምሮ ትናንት በተጠናቀቀው የሃይማኖት መሪዎች ስብሰባ፣ በሃገሪቱ የተፈጠረውን ችግር አስወግዶ ሰላምን ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ ታውቋል። ይህን የሃይማኖት መሪዎች ስብሰባን የተካፈሉት በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በኩል የዷላ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ክርስቲያን ዊጋን ቱሚ፣ የካሜሩን ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መጋቢ ባቢላ ጆርጅ ፎካንግ፣ የባሜንዳ ማዕከላዊ መስጊድ ኢማም የሆኑት ቱኩር ማሕመድ አዳሙ እና የቡያ ክፍለ ሀገር ማዕከላዊ መስጊድ ኢማም አልሃጂ ሙሐመድ አቡበከር መሆናቸው ታውቋል።       

31 August 2018, 17:13