አባ ሮቤርቶ ፓሶሊኒ፥ “እኛ በኢየሱስ ክርስቶስ ተደግፈን ለመቆየት ተጠርተናል” ሲሉ አስገነዘቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ፍራንችስካዊው የካፑቺን ወንድሞች ማኅበር አባል የሆኑት አባ ሮቤርቶ ፓሶሊኒ ዓርብ መጋቢት 12/2017 ዓ. ም. ጠዋት የዐብይ ጾም ወቅትን በማስመልከት ባሰሙት ስብከት፥ “በዚህ የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት የፆም ወቅት የሕይወታችን ዋስትና በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ተደግፈን ሕይወታችንን ለመቀጠል ተጠርተናል ብለው፥ በእርሱ ከተደገፍን ለሕይወታችን አስተማማኝ የሆነ መጠጊያ እናገኛለን ብለዋል።
አባ ሮቤርቶ ከዚህም ጋር አያይዘው፥ ይህ እምነታችን የሚያጽናናን ቢሆንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በቅርበት ለመተሳሰር ቅዱስ ወንጌሉን ተቀብለን መለወጥ እንዳለብን እና መንፈስ ቅዱስ ሰውነታችንን እና ድንበራችን እንደገና እንዲገልጽልን መፍቀድ አለብን ብለዋል።
ይህን ለማድረግ ራሳችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ማድረግ አለብን ብለው፣ ወደ ዘላለማዊው ቤታችን የምናደርገው ጉዞአችን ምን ዓይነት ሊሆን እንደሚገባ ከሕይወቱ መማር አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት የጉዞአችን ብርሃን ነው።
አባ ሮቤርቶ ፓሶሊኒ ለዓብይ ጾም ሰሞን ባዘጋጁት የመጀመሪያ ስብከታቸው እንደገለጹት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ ከተጠመቀ በኋላ በምድረ በዳ ፈተና ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ አገልግሎቱን መጀመሩን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ “የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት በሕይወት ውስጥ የታየ አንድ ክስተት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱን ምዕመን ጉዞ የሚያበራ ምልክት ነው” ብለው፥ “ይህም እኛ ልናደርገው የተጠራንባቸውን አንዳንድ የሕልውና እንቅስቃሴዎችን የሚያሳይ ምልክት ነው” ብለዋል።
ከእነዚህ የሕልውና ምልክቶች መካከል የመጀመሪያው፥ ከራሳችን ወጥተን ለሌሎች ቦታ መስጠት መቻል እንደሆነ በማስረዳት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ ራሱን ለሌሎች ድነት አሳልፎ የሰጠው በሰው ልጅ ሁኔታ ውስጥ በመሆን የእያንዳንዱን ሰው ደካማነት እና ታሪክ በሙላት በመካፈል እንደሆነ አስረድተዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ልዩ ልዩ ከፍተኛ ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤቶች ስብከት አቅራቢ ፍራንችስካዊው ካኅን አባ ሮቤርቶ ፓሶሊኒ በመቀጠልም ሁለተኛው የሕልውና እንቅስቃሴ መለወጥ እንደሆነ በመግለጽ ይህም ቀጣይነት ያለው ውስጣዊ ማረጋገጫን የሚያካትት እና “በእውነት ወንጌልን ተቀብለናል ወይ?” ብለን ራሳችንን የምንጠይቅበት እንደሆነ በማስረዳት፣ መለወጥ፣ “የሥነ ምግባር ለውጥ ብቻ ሳይሆን ጥልቅ የአመለካከት፣ ጠቃሚውን የመለየት እና ሌሎችን የመውደድ ለውጥ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።
አባ ሮቤርቶ ፓሶሊኒ በስብከታቸው መጨረሻ፥ “እኛ ከእውነታው ሳንሸሽ በውስጡ እንድንቆይ ተጠርተናል ብለው፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ በምድራዊ ሕይወቱ ከዓለም ውጥረቶች፣ ፈተናዎች እና ቅራኔዎች ለማምለጥ አልሞከረም” ሲሉ አስታውሰዋል።
አባ ሮቤርቶ ፓሶሊኒ ስብከታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ “እኛም በጊዜያችን ከውስብስብ እና ከባድ ከሆኑ ችግሮች ሳናመልጥ ወይም መሸሸጊያን ሳንፈልግ ጸንተን እንድንኖር ተጠርተናል” ብለዋል። በእግዚአብሔር ዕርዳታ ጉዞአችንን መቀጥል የምንችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው” ብለው፥ እግዚአብሔር ብቻችንን ሳይተወን ሁልጊዜ ከእኛ ጋር መሆኑን ልንገነዘብ የምንችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።