የዓለም የህጻናት መብቶች ስብሰባ፡- ለሚሰቃዩ ልጆች ፈገግታ ማምጣት ይገባል
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ለአንደኛ ደረጃ ብቁ የሆኑ እና የደረሱ 64 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት ትምህርታቸውን መከታተል አልቻሉም። ከአምስት አመት በታች ከሆኑ ህጻናት ከሦስቱ አንዱ ለከፋ የምግብ ድህነት ይጋለጣል። እ.አ.አ በ 2022 ዓ.ም ብቻ 12 ሚሊዮን ሴት ልጆች በልጅነት እድሜያቸው ጋብቻ ፈጽመዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዝም ከማለት ይልቅ “መብታቸውን የተነፈጉትን፣ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሚኖሩ፣ ብዝበዛና እንግልት የሚደርስባቸውን እና ጦርነት የሚያስከትላቸውን አስከፊ መዘዝ የሚደርስባቸውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናትን ለመርዳት እና ለመጠበቅ እንደሚጥሩ አስታውቀዋል።
ለሚሰቃዩ ልጆች ፈገግታ ለማምጣት ሞክሩ
ማክሰኞ ጥር 20/2017 ዓ.ም የቅድስት መንበር የፕሬስ ጽ/ቤት በህፃናት መብቶች ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን የአለም አቀፍ ስብሰባ መርሃ ግብር አውጥቷል። የቅዱስ ኤጂዲዮ ድርጅት ፕሬዝዳንት ማርኮ ኢምፓሊያዞ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ይህንን ስብሰባ “የተስፋ ክስተት” ብለውታል። “በጣም ብዙ ልጆች በጦርነት፣ በዓመፅ፣ በፆታዊ ጥቃት እና የጉልበት ብዝበዛ እንደሚሞቱ” ተናግሯል፣ እናም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለእነዚህ በስቃይ ላይ ያሉ ሕፃናትን “ፈገግታ ማምጣት” ይፈልጋሉ።
አንድ ቀን ለልጆች መስጠት
ዓለም አቀፉ የሕፃናት መብት ስብሰባ በቫቲካን በጥር 26/2017 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን “ውደዷቸውና ጠብቋቸው” በሚል መሪ ቃል ይካሄዳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልእክታቸውን ሊያጋሩ እና ሊያካፍሉ የሚችሉ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ 10 ሕጻናት ጋር አቀባበል በማድረግ ዝግጅቱን ሊከፍቱ ተዘጋጅተዋል።
ሰባት ውይይቶች ይካሄዳሉ፣ እያንዳንዳቸው ልዩ ርዕስ ያላቸው በልጆች መብቶች ላይ ያተኮሩ፣ የትምህርት ተደራሽነት፣ የቤተሰብ መብቶች፣ ከጥቃት መከላከል እና የሀብቶች ተደራሽነትን ጨምሮ እነዚህን ያካተቱ ንግግሮችን እና ውይይቶች ይካሄዳሉ። ከመላው ዓለም እና የኑሮ ዘይቤዎች ተሟጋቾች ወደ ሮም ይመጣሉ። በዝርዝሩ ውስጥ የዮርዳኖስ ንግሥት ራኒያ አል አብዱላህ፣ ማኙስ ማክፋርላን-ባሮ፣ የሜሪ ምግቦች ዋና ሥራ አስፈፃሚ፣ ካሊአሽ ሳትራቲ፣ የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸላሚ እና የቀድሞ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት አል ጎሬ በዚህ ስብሰባ ላይ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።
አዲስ የችግር ዘመን
ይህ የአለም የህጻናት መብቶች ስብሰባ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናት በየቀኑ እና በየእለቱ እያደጉ ላሉ ተግዳሮቶች ምላሽ ይሰጣል። "ዓለማችን በልጆች ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች የተነሳ ወደ አዲስ የችግር ዘመን እየገባች ነው፥ የአየር ንብረት ለውጥ፣ እኩልነት፣ አለመመጣጠን እና ግጭቶች ሕይወታቸውን እያወኩ እና የወደፊት ሕይወታቸውን እየገደቡ ነው” ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት ጥናት ዘግቧል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጥር ወር ባደረጉት የጸሎት ዓላማ “ዛሬ የትምህርት አደጋ እያጋጠመን ነው” በማለት ይህን አስደንጋጭ መግለጫ ደግመዋል። ሁሉም ህጻናት እና ወጣቶች የመማር መብት ቢኖራቸውም ወደ 250 ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት “በጦርነት፣ በስደት እና በድህነት ምክንያት” ትምህርት ማግኘት አልቻሉም" ሲሉ ተከራክሯል።