የብፁዕ ካርዲናል ጉጄሮቲ ጉብኝት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ለሶሪያ ያላቸውን ቅርበት ያሳያል መባሉ ተገለጸ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
የምስራቅ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናትን በበላይነት የሚቆጣጠረው ጽሕፈት ቤት ዋና አስተዳዳሪ ብፁዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ በዚህ ሳምንት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለተቸገሩት ምእመናን የቤተክርስቲያንን ቅርበት ለማሳየት በአደራ የተሰጣቸው ተልዕኮ አካል በሆነው የሶሪያ የስድስት ቀናት ጉብኝት ማድረግ እንደ ሚጀምሩ ይጠበቃል።
ጉብኝቱ ከጥር 16 እስከ ጥር 22/2017 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል። በቫቲካን የምስራቅ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናትን በበላይነት የሚቆጣጠረው ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ “የቅዱስ አባታችን ዓላማ፣ አሁን ባለው የሶሪያ ሁኔታ የአገሪቱ ካቶሊኮች የመላው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፍቅርና ድጋፍ ሊሰማቸው ይችላል፣ በተለይም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ስለ እነርሱ መጸለይ መቀጠላቸውን ለመግለጽ እድሉን የሚከፍት ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሆነም ከወዲሁ ተጠብቋል።
በመግለጫው መሠረት ብፁዕ ካርዲናል ጉጄሮቲ በቫቲካን የምስራቅ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናትን በበላይነት የሚቆጣጠረው ጽሕፈት ቤት ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ሚሼል ጃላክ እና ከካርዲናሉ የግል ፀሐፊ አባ አማኑኤል ሳባዳክ ጋር አብረው እንደሚጓዙ ገልጿል።
የካርዲናል የጉዞ መስመር
በሶርያ ከሚገኘው የቫቲካን ሐዋርያዊ አስተዳደር ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ ጋር በመገናኘት በተጨማሪም በእዚያው በሶሪያ ከሚገኙ ካህናት፣ ገዳማዊያን/ገዳማዊያት እና የካቶሊክ ምእመናን ጋር በእዚያው በሚገኘው ካቴድራል ይጸልያሉ፡- ከግሪክ-መልካይት (ከፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ አብሲ ጋር ይገናኛሉ። እናም በመለኮታዊ ቅዳሴ ውስጥ ይሳተፋሉ፣ ማሮናዊት ፣ ከለዳውያን ፣ አርሜኒያ እና ላቲን ስርዓት ተከታዮች ጋር እንደሚገናኙም ከወዲሁ ይጠበቃል)።
በደማስቆ እና በአሌፖ፣ ካርዲናል ጉጄሮቲ ከካቶሊክ ማህበረሰቦች መሪዎች፣ ቀሳውስት፣ የሃይማኖት አባላት እና ምእመናን እንዲሁም ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር ይገናኛሉ።
በሆምስ ከተማ በሚካሄደው የካቶሊክ ጳጳሳት ምልአተ ጉባኤ ላይም ይሳተፋል።
በጉብኝታቸው ወቅት ብፁዕ ካርዲናል ጉጄሮቲ ከኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ፓትርያርክ ጋር ይገናኛሉ፣ ብፁዕ አቡነ ሞር ኢግናቲየስ አፍሬም 2ኛ፣ የአንጾኪያ እና የመላው ምስራቅ የሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ፣ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ኤክስ፣ የግሪክ ኦርቶዶክስ የአንጾኪያ እና የመላው ምሥራቅ ፓትርያርክ፣ እና ሌሎች የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳት፣ የአርመን ሐዋርያዊ ቤተ ክርስቲያን ተዋረዶችን ጨምሮ እንደሚገናኙ ይጠበቃል።
በመግለጫው መሠረት ብፁዕ ካርዲናሉ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሰላምታ ለፓትርያርኮች እንደሚያስተላልፉ እና “አሁን ባለው ሁኔታ የክርስቲያን አንድነት የግድ አስፈላጊ ነው” እና “የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለሁሉ ትብብር ዝግጁ መሆኗን አጽንኦት ይሰጣሉ" ተብሎ ይጠቃል።