ፈልግ

በፖላንድ የተዘጋጀውን የብዙሃን መገናኛ ጉባኤ የተካፈሉ የቫቲካን ሚዲያ ልኡካን በፖላንድ የተዘጋጀውን የብዙሃን መገናኛ ጉባኤ የተካፈሉ የቫቲካን ሚዲያ ልኡካን 

ሕዝቦችን የሚያቀራርቡ እና የሚያገናኙ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሊኖሩ ይገባል ተባለ

በፖላንድ፥ ሉብሊን ከተማ በሚገኝ የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ "ዘመናዊ ሚዲያዎች እና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች ሚና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ" በሚል ርዕሥ የተዘጋጀውን ጉባኤ የቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ርዕሠ አንቀጽ ዋና አዘጋጅ አቶ አንድሬያ ቶርኔሊ እና የቫቲካን ሬዲዮ ኃላፊ አቶ ማሲሚሊያኖ ሜኒኬቲ ተካፍለዋል። ከቫቲካን መገናኛዎች ተጋብዘው ጉባኤውን የተካፈሉት ልኡካኑ "የውይይት ባሕልን በመገንባት፣ ታሪኮችን እና ምሥክርነቶችን መሠረት በማድረግ እውነትን መናገር ይገባል” በማለት ጉባኤውን ለተካፈሉ በርካታ ተማሪዎች ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሕዝቦችን የሚከፋፍሉ ሳይሆን የሚያቀራረብ፣ በመካከላቸውም ድልድዮችን የሚገነቡ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሊኖሩ እንደሚገባ፥ በፖላንድ ሉብሊን ከተማ ውስጥ በሚገኘው የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀውን ጉባኤ የተካፈሉት የቫቲካን ብዙኃን መገናኛ ዋና አዘጋጅ አቶ አንድሬያ ቶርኔሊ እና የቫቲካን ሬዲዮ ኃላፊ አቶ ማሲሚሊያኖ ሜኒኬቲ አስረድተዋል።  

ሚዲያዎች የውይይት ባሕልን ማሳደግ አለባቸው

"ዘመናዊ ሚዲያዎች እና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ" በሚል ርዕሥ የተዘጋጀውን ጉባኤ

የተካፈሉት የቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ተወካዮች የጉባኤውን ርዕሥ መሠረት በማድረግ ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት፥ የመገናኛ ብዙኃን በሕዝቦች መካከል እንቅፋትን የሚፈጥሩ ሳይሆን የእርስ በርስ ውይይት ባሕልን የሚደግፉ መሆን እንዳለባቸው አስምረውበታል። የብዙሃን መገናኛዎች በእውነት እና በሕይወት ምስክርነት ላይ የተመሠረተ መረጃን የማሰራጨት አስፈላጊነት ተናግረው፣ "ከአንድ ሰው ጋር ግንኙነት መፍጠር ስንጀምር ወይም የሕይወት ልምዱን ስንመለከተው ምንም እንኳን በመርሆዎቹ ባንስማማም ከፍተኛ ክብር ይሰማናል" ብለው፣ “በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ተማርከናል ለሚሉት ሰዎች የሕይወት ምስክርነት ምስጋና ይግባውና ቅዱስ ወንጌልም በዚህ መልኩ ከምንም በላይ ሊስፋፋ ችሏል” በማለት አቶ አንድሬያ ቶርኔሊ አስታውሰዋል። ለቫቲካን የመገናኛ ብዙሃን ተልዕኮ እና የተለያዩ ተግባራት አፅንዖትን የሰጡት አቶ አንድሬያ ቶርኔሊ፣ “እያንዳንዱ መልዕክት፣ አሳዛኝ ክስተቶችም ቢሆኑ እንኳን ተስፋን የሚሰጡ መሆን ይገባል ብለው፣ በዕለት ተዕለት ሥራችን እንደ ጦርነት ያሉ አስደንጋጭ እውነታዎች እንኳ ቢሆን ዘወትር የተስፋ ፍንጮች እንዲሆኑ ለማድረግ መሞከር ያስፈልጋል" በማለት ተናግረዋል።

ከዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር መሆን ያስፈልጋል

የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት እንቅስቃሴ ጉልህ ገጽታ የቤተ ክርስቲያኒቱን ማኅበራዊ አስተምህሮ መሠረት በማድረግ በዓለም ዙሪያ ያሉ ክስተቶችን መዘገብ እና ማሳወቅ መሆኑን የገለጹት የቫቲካን ሬዲዮ ኃላፊ አቶ ማሲሚሊያኖ ሜኒኬቲ በበኩላቸው፣ "ይህ ማለት ለምሳሌ በዩክሬን ውስጥ ቦምብ ቢፈነዳ ያስከተለውን ጥፋት በእርግጠኝነት ከማሳወቅ በተጨማሪ በተመሳሳይ መንገድ ከጥፋቱ ጀርባ ማን እንደሚገኝ እና ለሌሎች ሰዎች ጥቅም፣ ለሰላም እና ለወንድማማችነት ማን እንደቆመ እና ይህም መፍትሄዎችን ማግኘት የሚችሉ የዲፕሎማሲ ጥረቶችን የሚያካትት መሆኑን አስረድተዋል። በዘመናዊ የብዙሃን መገናኛ ቴክኖሎጂዎች ውስጥ የመቆየት አስፈላጊነትንም የተናገሩት ልኡካኑ፣ ከዘመናዊ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ጋር በጥሩ ሁኔታ በመግባባት የሃሳብ ልውውጥን በማድረግ ሌሎችን ማዳመጥ እና የክርስትና እምነት ውበትን መመስከር እንደሚያስፈልግ እና እውነትን ወደ ጦርነት መለወጥ እንደማይገባ ሁለቱ የቫቲካን ልኡካን ተናግረዋል።

ከትላልቅ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ነው

በጉባኤው ወቅት በፖላንድ የሉብሊን ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ሚሮስዋ ካሊኖቭስኪ፣የቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ዋና አዘጋጅ አቶ አንድሬያ ቶርኔሊን እና የቫቲካን ሬዲዮ ኃላፊ አቶ ማሲሚሊያኖ ሜኒኬቲን፣ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ትላልቅ የካቶሊክ ዩኒቨርስቲዎች መካከል አንዱ የሆነውን እንዲጎበኙ ጋብዘው ዩኒቨርሲቲው ሳይንሳዊ ጥናቶችን የሚያካሂዱ ወጣቶችን በነገረ መለኮት፣ በፍልስፍና፣ በማኅበራዊ ሳይንስ፣ በሕግ፣ በሂሳብ እና እንዲሁም በተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎችን እንደሚያስመርቅ ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር ካሊኖቭስኪ ለጉባኤው ተካፋዮች ባሰሙት ንግግር የቀድሞው ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን በማስታወስ፣ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ለዓለም ክፍት በመሆን እና እውነትን የሚያስተላልፉ የመገናኛ ዘዴዎችን በማስተዋወቅ የተጫወቱትን ሚና ጠቅሰዋል። በዩኒቨርሲቲያቸው ውስጥ “የጋዜጠኝነት ትምህርት እና ማኅበራዊ መገናኛዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው” ብለው፥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሁሉም የፖላንድ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ንቁ መሆናቸውን አስረድተዋል። በጉባኤው ላይ በርካታ ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በዋናነት የጋዜጠኝነት ትምህርት የሚከታተሉ እና እንዲሁም በሉብሊን ከተማ ከሚገኝ የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ፋውንዴሽን የነጻ ትምህርት ዕድልን ያገኙ ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

03 June 2023, 16:37