ፈልግ

በሥራው ዓለም የሚወሰድ የደኅንነት ጥንቃቄ በሥራው ዓለም የሚወሰድ የደኅንነት ጥንቃቄ  

ቫቲካን እና የጣሊያን መንግሥት የሠራተኞችን ክብር የሚያስጠብቅ የጋራ ስብሰባ አካሄዱ

በቫቲካን ከተማ አስተዳደር ጠቅላይ ጽ/ቤት አስተባባሪነት በሠራተኞች ጉዳይ ላይ የተወያየ ስብሰባ ማክሰኞ ግንቦት 29/2015 ዓ. ም. ተካሂዷል። የጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ ዋና ጸሐፊ እህት ራፋኤላ ፔትሪኒ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ጉዳዩን በማስመልከት ከዚህ በፊት ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ያደረጉት አስተዋጽዖ በመመልከት ጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ስብሰባውን የተካፈሉት የሮም ከተማ ረዳት አቃቤ ሕግ አቶ ጆቫኒ ኮንዞ፥ በሥራ ገበታ ላይ ለብዝበዛ የሚዳረጉ በርካታ ተጋላጭ ሰዎች መኖራቸውን ተናግረው፥ ክስተቱን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት እያንዳንዱ የሠራተኛ ሕግ በተግባር ሊውል ይገባል ብለዋል። ጣሊያን ውስጥ በየዓመቱ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች በሥራ ገበታቸው ጉዳት እንደሚደርስባቸው ሲታወቅ፥ በክስተቱ ላይ ግምገማ እና ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል ስልጠና መቀነስ እንደማይገባ የስብሰባው ተካፋዮች ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና የሥራ ክብር

የሥራ ደኅንነት ጉዳይ ዘላቂ የሥራ ሞዴልን ለመከተል ለሚፈልግ ማንኛውም ድርጅት አስፈላጊ እንደሆነ እና አንዳንድ ምሁራንም አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ብለው በመጥራት ዓለም አቀፋዊ ይዘት መያዙን፥ ርዕሠ ጉዳዩን በግልፅ የሚመለከቱ፥ “አዳዲስ ነገሮች” ከሚለው የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዎ 13ኛ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን አንስቶ እስከ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ድረስ ያሉትን ዋና ዋና ሰነዶች ዋቢ በማድረግ የገመገሙት፥ የቫቲካን አስተዳደር ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ጸሐፊ እህት ራፋኤላ ፔትሪኒ ናቸው። እህት ራፋኤላ ከእነዚህ ሠነዶች በተጨማሪ “የሥራ ልምምድ” የሚለውን የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በመጥቀስ፥ሥራ ጠቃሚ እና መልካም ብቻ ሳይሆን አስደሳች፣ ክብርን የሚገልጽ እና የሚጨምር እንደሆነም አስረድተዋል። የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛም በሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፥ “በሥራው ዓለም የመጀመሪያው ሃብት ሰው ነው” ማለታቸው እህት ራፋኤላ አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የቀደምት ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ አስተምህሮን ሙሉ በሙሉ በመጋራት እና ወደ ፊት በማራመድ፥ ሥራ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የሰዎች ሕይወት ትርጉም ዋና አካል እንደሆነ ማረጋገጣቸውን እህት ራፋኤላ ገልጸው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ታኅሳስ 10/2015 ዓ. ም. የጣሊያን ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን አባላትን በቫቲካን ተቀብለው ያደረጉትን ንግግር ዋቢ በማድረግ፥ ሥራ ኅብረተሰብን በመገንባት እና ዜግነትን ይፋ በማድረግ፣ ማኅበረሰቡ የራሱ ትክክለኛ ገጽታ እንዲኖረው እንደሚያደርግ፣ ዴሞክራሲን ከዕለት ወደ ዕለት ማሳደግ የሚቻለው በሰዎች፣ በምጣኔ ሃብታዊ እና በፖለቲካዊ ውጥኖች መካከል ባለው ግንኙነት እንደሆነ፣ የሥራ ማኅበራት ሰዎች የሥራ ስሜት እንዲኖራቸው ማስተማር እንደሚገባ፣ በሠራተኞች መካከል ወንድማማችነትን መገንባት ትርፍን ከማካበት የበለጠ አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት መስጠታቸውን እና ለጋራ ጥቅም የሚውል ኢኮኖሚ ለሰላም ዋስትናን እንደሚሰጥ መናገራቸውን እህት ራፋኤላ አስታውሰዋል።

ሕገ-ወጥ ቅጥር ጣሊያን ውስጥ አሳሳቢ ችግር ሆኗል

የሮም ከተማ ረዳት አቃቤ ሕግ አቶ ጆቫኒ ኮንዞ ለስብሰባው ተሳታፊዎች ባደረጉት ንግግር፥ በሥራ ዘርፍ ላይ የሚደርስ የሞት አደጋን ማሸነፍ እንደሚቻል አስገንዝበው፥ አደጋውን ማስቀረት የሚቻልበት ዋናው መንገድ ጥብቅ የመከላከያ ደንቦችን መከተል እና የደኅንነት ሕጎችን በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል።ቫቲካን ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2021 ዓ. ም. በሥራ ላይ እያሉ የሞት አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር 1,221 እንደ ነበር መግለጹን የተናገሩት አቃቤ ሕጉ አቶ ጆቫኒ ኮንዞ፥ በሕገወጥ ቅጥር ላይ የሚደረጉ ጥናቶች እና የሚጣልባቸው ቅጣቶች ጥቂት በመሆናቸው የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸዋል። “ሕገ-ወጥ ቅጥር እና የሰዎች ዝውውር ክስተቶች በቅርብ የተቆራኙ ናቸው” ያሉት አቃቤ ሕጉ አቶ ጆቫኒ ኮንዞ፣   እዚህን ወንጀሎች ለመቆጣጠር ሕጎችን በሙሉ ተከትሎ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። "ዋናው ፈተና ሰዎች ያላቸውን አቅም እንዲጠቀሙ ማድረግ ነው” ያሉት አቶ ጆቫኒ ኮንዞ፣ በዚህ ረገድ ለኅብረተሰቡ ጠቃሚ ምላሽ መስጠት እንደሚቻል አስረድተዋል።

በሥራ ላይ እያሉ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 1090 ነው (እ.አ.አ 2022)

ለሮም ከተማ አቃቤ ሕግ ቢሮ ሪፖርታቸውን ያቀረቡት ኢንስፔክተሮች ባርባራ እና ቪቪያና ቶዲኒ፥ በሥራ ቦታ ላይ ያለውን የደኅንነት ጥበቃ በማስመልከት ባደረጉት ገለጻ፥ ኅብረተሰቡ ገና ወደ እውነተኛ የሥራ ክብር ላይ አለመድረሱን ጠቁመው፥ “የቴክኖሎጂ አቅርቦት፣ የማዕቀቦች መበራከት፣ ደንቦቹን በሚጥሱ ኩባንያዎች ላይ ኤኮኖሚያዊ እርምጃዎችን መውሰድ፣ በተቆጣጣሪ አካላት ላይ የተቀመጡት የመከላከል ቁርጠኝነት፥ በዓመት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርን ከአንድ ሺህ ዝቅ ለማድረግ ገና በቂ ሥራ አይደለም” ብለዋል። ኢንስፔክተሮቹ አክለውም፥ “ይህን ችግር ለማሸነፍ የሚሞክር ወሳኑ ሰው እንደሆነ እና የተጣለበትን ሃላፊነት ተቀብሎ በኅሊናው ላይ እርምጃ መውሰድ ያለበትም ሰው ነው” በማለት አስረድተዋል።

ቫቲካን ፥ ለስልጠና ቅድሚያን መስጠት ያስፈልጋል

ለስብሰባው ተሳታፊዎች ሃሳባቸውን ያጋሩት፥ የቫቲካን የሥራ ደኅንነት አገልግሎት ባልደረባ አቶ ቶማሶ ማሮኔ እና የቫቲካን የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍል ኃላፊ አቶ ፓውሎ ደ አንጄሊስ በበኩላቸው፥ ዛሬ ላይ በቂ ስልጠናን ከመስጠት ይልቅ ዲፕሎማ መስጠት ብቻ እንደሚንጸባረ ገልጸው፥ ሥነ-ምግባር ያስፈልጋል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከዚህ አንፃር እ.አ.አ ከጥር 1/2008 ዓ. ም. ጀምሮ ሥራ ላይ በዋለው ሕግ ቁ. 54 መሠረት፣ በቫቲካን ግዛት ውስጥ በሕጉ ማዕቀፍ መሠረት 3850 ስልጠናዎች መሰጠታቸውን እና በዚህ ዓመት ብቻ ወደ 500 የሚጠጉ ሰዎች ስልጠና መውሰዳቸውን አስረድተው፥ ዛሬ በአማካይ በየሦስት ተኩል ቀናት ውስጥ አንድ የሥራ ላይ አደጋን እንደሚመዘግብ ገልጸው፥ አገልግሎቱ ከመቋቋሙ አስቀድሞ በየሁለት ቀኑ አንድ የሥራ ላይ አደጋ የሚመዘገብ እንደ ነበር ገልጸው፥ "በሥራ ገበታ ላይ ለሰው ልጅ አስፈላጊውን ክብር መስጠት ከግምት ውስጥ መግባት አለበት" በማለት አጥብቀው ተናግረዋል።

07 June 2023, 15:21