ፈልግ

የቫቲካን ቅጥር ግቢ ጠባቂ የሆኑ የስዊዝ የክቡር ዘበኛ የጥበቃ አባል የቫቲካን ቅጥር ግቢ ጠባቂ የሆኑ የስዊዝ የክቡር ዘበኛ የጥበቃ አባል  (AFP or licensors)

ወደ ቫቲካን ቅጥር ግቢ በግዳጅ የገባው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ዋለ!

አንድ የ40 አመት ወጣት መኪናውን በከፍተኛ ፍጥነት እያሽከረከረ ወደ ቫቲካን ከተማ ቅጥር ግቢ በመግባት የስዊዝ የጥበቃ አባላት እና የቫቲካን ጀንዳርሜሪ በመባል የሚታወቁት የቫቲካን የጥበቃ አባላት ሁለት የፍተሻ ኬላዎችን አስገድዶ ከገባ በኋላ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ሐሙስ እለት ግንቦት 10/2015 ዓ..ም ማምሻው ላይ በቫቲካን ከተማ ዋና መግቢያ አከባቢ መኪና በማሽከርከር ላይ የነበረ አንድ ሰው መኪናውን በፍጥነት በማሽከርከር ወደ ቫቲካን ቅጥር ግቢ አስገድዶ በመግባቱ የተነሳ ነበር በቁጥጥር ሥር የዋለው።

ክስተቱ የተፈጠረው በኢትዮጲያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 3 ሰዓት ገደማ ላይ የነበረ ሲሆን የቅድስት ሃና መግቢያ በመባል በሚታወቀው ወደ ቫቲካን ቅጥር ግቢ ከሚያስገቡ በሮች መካከል አንዱ እና ዋነኛ በሆነው በር በኩል ነበር አስገድዶ መኪናውን በፍጥነት በማሽከርከር የገባው።

የቅድስት መንበር የዜና ማሰራጫ ክፍል እንዳስታወቀው ሰውዬው ወደ ቫቲካን እንዳይገባ በስዊዝ የጥበቃ አባላት ወደ ቅጥር ግቢው እንዳይገባ ከተደረገ በኋላ በከፍተኛ ፍጥነት በመመለስ የስዊዝ የጥበቃ አባላት እና ጀንዳርሜሪ በመባል የሚታወቁትን የቫቲካን የድህንነት ጠባቂ ፖሊሶች ሁለቱን የፍተሻ ኬላዎች አስገድዶ እንዳለፈ ተገልጿል።

ጋዜጣዊ መግለጫው እንደገለጸው ከሆነ መኪናውን ለማስቆም በመሞከር የበር ጥበቃ ላይ የነበረው የፖሊስ ተቆጣጣሪው ወደ ተሽከርካሪው የፊት ጎማ አቅጣጫ ጥይት ተኩሷል።

ተሽከርካሪው ቢመታም መንገዱን መቀጠል ችሏል። ፖሊሶችም በመቀጠል የአደጋ ጊዜ ማንቂያ ሳይረን ደውለው የቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ የኋላ በር የቫቲካን የበስተጀርባ በሮች እና የቅድስት ማርታ አደባባይ መግቢያ በር፣ የጳጳሱ መኖሪያ ወደ ሚገኝበት የመዳረሻ በሮች በፍጥነት እንደ ዘጉ ተዘግቧል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ መኪናው ወደ ቅዱስ ደማሰስ ግቢ ደረሰ፡- “ሹፌሩ ራሱን ችሎ ከመኪናው ውስጥ ወጣ፣ ከእዚያም በኋላ በቫቲካን ፖሊስ ጓድ በቁጥጥር ስል ዋለ” ሲል የቫቲካን ፕሬስ ብሮ ባወጣው መግለጫ አክሎ ገልጿል።

ዕድሜው 40 ዓመት ገደማ የሆነው ሰው በቫቲካን ከተማ የጤና እና ንፅህና ዳይሬክቶሬት ዶክተሮች ወዲያውኑ የጤና ምርመራ የተደረገለት ሲሆን “በከባድ የስነ-ልቦና ቀውስ ሁኔታ” ውስጥ መገኘቱ ተዘግቧል።

በአሁኑ ጊዜ በቫቲካን የፍትህ አካላት ፊት ቀርቦ ጉዳዩ እስኪታይ ድረስ በቫቲካን ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው እስር ቤት ውስጥ ሆኖ ጉዳዩን በመከታተል ልይ ይገኛል።

 

19 May 2023, 13:38