ፈልግ

cq5dam.thumbnail.cropped.1500.844.jpeg

የአውስትራሊያ ነባር ተወላጆች መሪ በቫቲካን ለአንድ ሳምንት ጉብኝት ያደርጋሉ ተባለ!

በአውስትራሊያ በጣም የተከበሩ የአቦርጂናል (ከጥንት ጀምሮ ወይም ቅኝ ገዥዎች ከመምጣታቸው በፊት በአውስትራሊያ ምድር ላይ የነበሩ ወይም መኖር የጀመሩ ፣ ተወላጅ የሆኑ ፣ በደቡብ ምስራቅ እስያ የሚገኙ ተወላጅ ህዝቦች) መሪዎች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ኡንጉንመር ባውማን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና ሌሎች ከፍተኛ የቫቲካን መሪዎች ጋር ይገናኛሉ። በቫቲካን ሙዚየምም አዲስ የሥዕል ሥራን ያሳያሉ።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ዶ/ር ሚርያም ሮዝ ኡንጉንመር ባውማን የአውስትራሊያ አቦርጂናል የዕድሜ ባለጸጋ ፣ መምህርት እና አርቲስት ፥ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ጉብኝት በቫቲካን ይገኛሉ።

በቆይታቸውም ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና ከፍተኛ የቤተክርስትያን ባለስልጣናት ጋር በመገናኘት ስለ መንፈሳዊነት ፣ ስነ-ምህዳር እንዲሁም በቤተክርስቲያን እና በአውስትራሊያ ተወላጆች መካከል ስላለው እርቅ ጉዳይ ይወያያሉ።

አውስትራሊያ ውስጥ ካሉ የጎሳ መሪዎች መሃል በጣም የተከበሩ የአቦርጂናል መሪዎች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ኡንጉንመር ባውማን የቫቲካን ሙዚየምን ይጎበኛሉ ተብሎም ይጠበቃል። እዚያም ፥ ማክሰኞ ምሽት ላይ እንደ ብዙዎቹ የስነጥበብ ስራዎቿ ሁሉ ፣ ‘የአቦርጂናል የመስቀል ማረፊያ’ ተብሎ እንደሚታወቀው ታዋቂው ሥራቸው ፥ በአገሬው ተወላጆች ባህል እና በክርስቲያናዊ ይዘቶች ላይ የተመሰረተ አዲስ የሥዕል ሥራቸውን ያሳያሉት።

ተፈጥሮአዊ በሆነ ዓለም ውስጥ እግዚአብሔርን መገናኘት

ዶ/ር ባውማን አዲሱ ሥዕላቸውን ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳብራሩት በአውስትራሊያ ክልል በሰሜኑ ክፍል ያለውን ‘የበጋ ወቅት’ ያሳያል ብለዋል።

ተፈጥሮ የዝናቡን መጨረሻ ለማመልከት የሚሰጣቸውን ምልክቶች ፥ ለምሳሌ የ ‘ድራጎን ዝንቦች’ መምጣት እና ባራሙንዲ የሚባለው የዓሳ ዝርያ በወንዙ ውስጥ መታየት የሚጀምሩትን ለማሳየት ይሞክራል ይላሉ።

ለዶክተር ኡንጉንመር ባውማን ፥ በነዚህ የተፈጥሮ ክስተቶች እና በካቶሊክ እምነቷ መካከል ያለው ግንኙነት ግልጽ ነው ፤ ተፈጥሮ ከእግዚአብሔር ጋር የምትገናኝበት ቦታ ነው። ከቫቲካን ዜና ባልደረባ በፊት ሌላ ጋዜጠኛ የአውስትራሊያ ተወላጅ የሆኑ ማህበረሰባቸው እንዴት ወደ ክርስትና እንደመጡ ሲጠይቃቸው ‘መልሱ ቀላል ነው ብለዋል’ ፥ በማከልም “እግዚአብሔርን በተፈጥሮ ውስጥ አገኘነው” የሚል ነበር መልሳቸው።

እሳቸውም ይህን ጥያቄ ተጠይቀው ተመሳሳይ የሆነ መልስ ነው የመለሱት። ይህ በጣም ማዕከላዊ የሆነ መልስ ነው ፥ ለአዲሱ ሥዕላቸው መጠሪያ ስምም ሆኖ ሊያገለግል ይችላል።

 ከአገሬው ተወላጆች ጋር እርቅ

የዶ/ር ኡንጉንመር ባውማን ጉብኝት የአቦርጂናል ታሪክ እና ባህል ዓመታዊ ክብረ በዓል ከሆነው የአውስትራሊያ የእርቅ ሳምንት ጋር ለማገጣጠም እንደሆነም ተነግሯል።

በሮም ቆይታቸውም የቅድስት መንበር የግዛቶች ግንኙነት ፀሐፊ ከሆኑት ሊቀ ጳጳስ ፖል ጋላገር ጋር ተገናኝተው በአገሬው ተወላጆች ጉዳይ ላይ ይወያያሉ ተብሎም ይጠበቃል። በስብሰባው ላይም በቫቲካን የሚገኙ ነባር ተወላጆች ያሏቸው የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እንደሚገኙ ታውቋል።

ዶ/ር ኡንጉንመር ባውማን በአገሬው ተወላጆች እና ተወላጅ ባልሆኑ ህዝቦች መካከል ድልድይ መገንባት 'ከእርቅ' አንፃር መረዳት እንዳለበት አጥብቀው ይናገራሉ። “ጉዳዩ እኛ ስለ እናንተ ለማወቅ እና እናንተም ስለ እኛ እንድታውቁ ስለማድረግ ነው” ይላሉ።

ሃምሳ ዓመታት የሆናቸው የሀገር በቀል የአምልኮ ሥርዓቶች

ዕሮብ እለት ፥ በቫቲካን ሙዚየም ውስጥ ‘አምላክን በተፈጥሮ ውስጥ ነው ያገኘነው’ የሚለውን የሥዕል ስራቸውን ይፋ ባደረጉ ማግስት ፥ ዶ/ር ኡንጉንመር ባውማን የመጀመሪያው የአቦርጂናል ሥርዓተ አምልኮ ከሃምሳ ዓመታት በፊት ከተከበረ በኋላ ፥ የሚደረግ ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ ይገኛሉ።

በዚያን ጊዜ ፥ እ.አ.አ. በ1973 ማለት ነው ፥ የአገሬው ነባር ተወላጆች ቋንቋዎችን እና ባህልን ያካተተ የመጀመሪያ ቅዳሴ ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው የአቦርጂናል ሰዎች በአውስትራሊያዋ ከተማ በሜልቦርን ተሰብስበው ነበር።

ዶ/ር ኡንጉንመር ባውማን ስለ በዓሉ አስፈላጊነት ተጠይቀው “ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁሉም የሰው ልጅ ብሎ እዛ ነበር” ይላሉ። “በቅዱስ ቁርባን ጊዜ እራሱን ሲያቀርብ ፥ ማንም ምንም ይሁን ፥ ለሁሉም ሰው ነው” ብለዋል።

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር የሚደረግ ቆይታ

ዕሮብ ዕለት ዶ/ር ኡንጉንመር ባውማን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋርም ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሚናገሩትን ገና አልወሰኑም ፥ ነገር ግን የአውስትራሊያ ነባር ተወላጅ ማህበረሰቦች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመግለፅ እንደ አንድ አጀንዳ እንደሚይዙ ተናግረዋል።

የዶክተር ኡንጉንመር ባውማን ቤተሰብ አባል ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪ ጋር ሲገናኝ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። እ.አ.አ. በ1986 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጆን ፖል ዳግማዊ ወደ አውስትራሊያ በሄዱበት ወቅት ከእህታቸው ጋር ተገናኝተው እንደነበር እና ትንሹን ልጇንም ባርከው እንደነበር አስታውሰዋል። ይሄም ሊያም የተባለው ልጅ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ እራሱን ያጠፋ ሲሆን ፥ ይህም አሁንም በአውስትራሊያ ነባር ተወላጅ ማህበረሰቦች ውስጥ ስለሚያጋትሟቸው በርካታ ትግሎች እና የእኩልነት ችግሮችን ያስታውሳል ብለዋል።

ከቫቲካን ባለስልጣናት ጋር የሚደረግ ውይይት

ዶ/ር ኡንጉንመር ባውማን ፥ ከቫቲካን ዋና መሪዎች ጋር ከሚያደርጉት ውስጥ ፥ ከጳጳሱ ጋር የሚያደርጉት ስብሰባ የመጀመሪያው ይሆናል። በእለቱም ከቫቲካን የትምህርት እና የባህል ዲካስትሪ ፀሐፊ ጳጳስ ፖል ቲጌ ጋር ከሚደረግ ህዝባዊ ውይይት ላይ ይሳተፋሉ።

የቤተክርስቲያኒቷ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ዉስጥ አንዱ ቅርንጫፍ ከሆነው ከካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ ተወካዮች ጋር እንዲሁም የዓለም አቀፍ የበላይ አለቆች ህብረት የሆነው ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ገዳማዊያን የሴቶች ህብረት መሪዎች ጋርም እንደሚገናኙ ይጠበቃል።

ከእነዚህም ጋር የአገሬው ነባር ተወላጅ ስለ አጠቃላይ የስነ-ምህዳር አመለካከት የሆነው እና ‘ዳዲሪ’ ተብሎ በሚታወቀው ጽንሰ-ሀሳብ ዙሪያ እንደሚነጋገሩ ታውቋል።

 

31 May 2023, 18:51