ፈልግ

በሮም፣ ቅዱስ አጎስጢኖስ ባዚሊካ ውስጥ የሚገኝ የቅድስት ሞኒካ መካነ መቃብር በሮም፣ ቅዱስ አጎስጢኖስ ባዚሊካ ውስጥ የሚገኝ የቅድስት ሞኒካ መካነ መቃብር  

ካርዲናል ሰመራሮ፣ እግዚአብሔር የልጆቹን ስቃይ ተመልክቶ ሕመማቸውን የሚጋራ መሆኑን ገለጹ

የቅዱስ አጎስጢኖስ ገዳማውያን ማኅበር አባል እና ጳጳስ የነበሩ የእግዚአብሔር አገልጋይ አቡነ ጁሴፔ ቤርቶሎሜዎ ዕረፍት ሁለት መቶኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ፣ በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮችን የሚከታተል ጳጳሳዊ ምክር ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ፣ ሮም ውስጥ በሚገኝ የቅዱስ አጎስጢኖስ ባዚሊካ ውስጥ እሁድ መጋቢት 17/2015 ዓ. ም. የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መርተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስና ጉዳዮችን የሚከታተል ጳጳሳዊ ምክር ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከት፥ “እግዚአብሔር የልጆቹን ስቃይ ተመልክቶ ሕመማችንን እና ለቅሶአችንን የሚጋራ አምላክ ነው” በማለት ተናግረዋል። በሕይወት ዘመናቸው እንደ ቅዱስ ይቆጠሩ የነበሩት አቡነ ጁሴፔ ቤርቶሎሜዎ፣ የችግረኞችን ስቃይ የሚጋሩ፣ ግዞተኛ እና እስረኛ ለነበሩ ለቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ ሰባተኛ ዘወትር ታማኝ እና ወዳጅ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ርኅሩህነት

በላቲን ሥርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠር መሠረት የዐቢይ ጾም አምስተኛው እሑድ በተነበበው ዮሐ. 11:1-45 ላይ በማስተነተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ብጹዕ ካርዲናል ሰመራሮ፥ ስለ “እንባ” በተናገሩት ላይ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ጥልቅ ሐዘን እና እንባ መጻፉን እና ኢየሱስ ወዳጁ የሆነውን አልዓዛርን ከሞት ማስተነሳቱን አስታውሰዋል። “እነዚያ የእግዚአብሔር ልጅ እንባዎች፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት ሰው መሆኑን የሚያስረዱ ናቸው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ሰመራሮ፣ የአልዓዛር ታሪክ በእርግጥም የኢየሱስ ክርስቶስን ስሜታዊ ባለጠግነትን እንደሚያጎላ ገልጸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ልቡ የሚያዝን፣ የሚያለቅስ እና ሐሴትንም የሚያደርግ፣ ከሁሉ በላይ ለተቸገሩ የሚራራ መሆኑን አስረድተዋል።

እግዚአብሔር ጩኸታችንን ሁል ጊዜ ይሰማል

በጥንታዊው የግሪክ-ሮማውያን ልማድ ማልቀስ ከወንድ ልጅ የማይጠበቅ ምልክት እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ሰመራሮ፣ በክርስትና ባሕል ማልቀስ ሰብዓዊነትን ብቻ ሳይሆን መለኮታዊነትንም እንደሚገልጽ አንደሆነ አስረድተዋል። ቅዱስ አጎስጢኖስም በልጅነት ጓደኛው እና ከዚያም በእናቱ ሞኒካ ሞት ምክንያት ማልቀሱን ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ሰመራሮ፣ እግዚአብሔር በእውነት የሰውን ለቅሶ ዘወትር እንደሚሰማ እና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ሆኖ እርሱ ራሱ ማልቀሱንም አስረድተዋል።

ለሕመማችንን ዋጋን መስጠት

በዮሐንስ ወንጌል ላይ እንደተጠቀሰው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በአልዓዛር መቃብር ፊት ቆሞ ካፈሰሰው እንባ ቢያንስ ሁለት ነገሮችን እንማራለን ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ሰመራሮ፣ የመጀመሪያው፣ እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ሕመማችንን እና ስቃያችንን በቁም ነገር ወስዶ እንደሚጋራ እና አብሮን እንደሚያለቅስ፣ ሁለተኛው፣ ሽንፈታችን፣ ጥፋታችን እና ሕመማችን እንደማይጠገን ብንቆጥርም፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሌሎች ምርጫዎችን እንደሚያቀርብልን እና የተለየ ዕይታን የሚመርጥ መሆኑን፣ ይህም ብዙውን ጊዜ የማይገባን እና የማንረዳው መሆኑን በመግለጽ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ጋር በመሆን ጣልቃ እንደሚገባ አረጋግጠዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስን በሥራው መተባበር

“ኢየሱስ ክርስቶስ በሥራው እንድንተባበር ይፈልጋል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ሰመራሮ፣ በዮሐንስ ወንጌል ላይ እንደተጠቀሰው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አልዓዛርን ከመቃብር ውስጥ ከጠራው በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ሥራውን እንዲያጠናቅቁ መጠየቁን አስታውሰው፣ አልዓዛር የተገነዘበትን ጨርቅ እንዲፈቱለት እና እንዲሄድ እንዲያደርጉ ማዘዙን አስታውሰዋል።

“ይህ ዛሬ ለምእመናን በሙሉ የቀረበ ግብዣ ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ሰመራሮ፣ አንዳንድ ጊዜ በእርግጥ የእግዚአብሔር ዕርዳታ ስንጠይቅ ሁሉንም ነገር እርሱ ማድረግ እንዳለበት እናስባለን” ብለው፣ ቢያንስ ጉዟችንን ወደፊት መቀጠል እንድንችል፣ በመንገዳችን የሚያጋጥሙን እንቅፋቶችን እኛ እራሳችን ማስወገድ አለብን” ብለዋል። “ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የታሰሩበትን ገመድ በፍጥነት መፍታት አለብን” ያሉት ካርዲናል ሰመራሮ፣ ይህም የምሕረት መንገድ እንደሆነ ገልጸው፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱ ንቁ ተባባሪዎች እንድንሆን ይጠይቀናል” በማለት ስብከታቸውን ደምድመዋል።

27 March 2023, 14:43