ፈልግ

የቅድስት መንበር ፍርድ ቤት ችሎት የቅድስት መንበር ፍርድ ቤት ችሎት   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ካርዲናል ቤቹ፣ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን በደብዳቤ አላግባባሁም” በማለት ራሳቸውን ተከላከሉ

ለንዶን ከተማ ውስጥ ይገኛል ከተባለው የቅድስት መንበር ሕንጻ ጋር በተገናኘ፣ ሐምሌ 20/2012 ዓ. ም. ክስ ተመስርቶባቸው የፍርድ ሂደቱን በመከታተል ላይ የሚገኙት ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ቤቹ፣ በእርሳቸው እና በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መካከል የተደረገ የደብዳቤ ልውውጥ ጥያቄን በማስመልከት ድንገተኛ መግለጫን የካቲት 30/2015 ዓ. ም. ሰጥተዋል። ካርዲናል ቤቹ ከዚህ በፊት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር የተለዋወጡትን እና በፍርድ ቤት መዝገብ ውስጥ ያልገባ ሌላ ደብዳቤ ወደ ችሎቱ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ቤቹ በቅድስት መንበር ከነበራቸው የገንዘብ አያያዝ ጋር በተያያዘ የካቲት 30/2015 ዓ. ም. በዋለው 52ኛ ችሎት ሁለት ድንገተኛ መግለጫዎችን ሰጥተዋል። ትናንት ዓርብ መጋቢት 8/2015 ዓ. ም. የዋለው ችሎት በዋናነት የቅድስት መንበር ምክትል ጸሐፊ አቡነ ኤድጋር ፔኛን ምስክርነት አዳምጧል። አቡነ ፔኛ ፓራ በቫቲካን አዳራሽ ውስጥ የምስክርነት ቃላቸውን በሰጡበት ወቅት ካርዲናል አንጄሎ ቤቹም እንደገና ተገኝተው ወሳኝ ጉዳዮች ጎልተው ባለመውጣታቸው የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸዋል።

ከር. ሊ. ጳ. ጋር የነበራቸው የመልዕክት ልውውጥ

ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ቤቹ በዕለቱ ባቀረቡት ሁለተኛ መግለጫቸው፣ ባለፈው የካቲት 30/2015 ዓ. ም. የዋለው ችሎቱ በፍትህ አራማጁ በአቶ አሌሳንድሮ ዲዲ የተዘጋጀውን፣ በካርዲናሉ እና በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መካከል የነበረውን የመልዕክት ልውውጥ ተመልክቶ እንደነበር ይታወሳል። ብጹዕ ካርዲናል ቤቹ ለሁለቱም ሂደቶች "አሉታዊ መግለጫ" ያሏቸውን አንዳንድ ቀደምት መግለጫዎች እንዲሻሩ ቅዱስነታቸውን ጠይቀዋል። “ቅዱስ አባታችንን ሆነ ማንንም መልዕክት በመጻፍ አላግባባሁም” በማለት ያብራሩት ብጹዕ ካርዲናል ቤቹ፣  የመልዕክት ልውውጡ በምስጢር እንዲቆይ የተደረገበት ምክንያትም፣ “ሰብአዊ ተግባር እየተባለ የሚጠራው እና በማሊ ውስጥ ታግተው የነበሩ ኮሎምቢያዊ ት መነኩሴን ነፃ ለማውጣት የተደረገውን ጥረት የያዘ መልዕክት በመሆኑ ነው” ብለዋል።

ለአቡነ ፔኛ የቀረበ መስቀለኛ ጥያቄ

አራት ሰዓት ያህል በቆየው ችሎቱ ላይ ለአቡነ ፔኛ ፓራ መስቀለኛ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል። ለአቡነ ፔኛ ፓራ የቀረበው ጥያቄም በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ጥያቄ መሠረት፣ በለንደን ከተማ ውስጥ የሚገኝ ሕንጻ ግዢ በወር አንድ ሚሊዮን ዩሮ ስለሚከፈል የብድር ገንዘብ የተመለከተ እንደነበር እና አቡነ ፔኛ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ዝርዝር ምላሽ መስጠታቸው ታውቋል። ሁለት ከፍተኛ አበዳሪ ድርጅቶች ለሕንጻው ግዥ በብድር ገንዘብ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናቸውን የገለጹት አቡነ ፔኛ፣ የመጀመሪያው አበዳሪ ወዲያው ገንዘብ ሲያቀርብ ሁለተኛው አበዳሪ ከጥቂት ወራት በኋላ ገንዘብ መስጠት መጀመሩን ገልጸው፣ ይህም በጽሕፈት ቤታቸው የውስጥ ውሳኔ መሠረት የተፈጸመ መሆኑን አስረድተዋል።

የቅድስት መንበር ምክትል ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ኤድጋር ፔኛ በመጨረሻም፣ ከቫቲካን ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ከሆኑት ከአቶ ጁሴፔ ፒኛቶኔ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። በቼቺሊያ ማሮኛ ስም ለሚገኝ ሎግሲንክ የተባለ ድርጅት የ575 ሺህ ዩሮ ተከታታይ ክፍያዎችን መፍቀዳቸውን አረጋግጠው፣ የእነዚህ ክፍያዎች ዜና ወደ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና የሂደቱ ዋና ምስክር ወደ ሆኑት አቡነ አልቤርቶ ፔርላስካ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደደረስ እና ትዕዛዙም የባንክ ሂሳብን ከማዘዋወር ጋር የመጣ እንደነበር ገልጸዋል። 

ከቅድስት መንበር የገንዘብ አያያዝ ጋር የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ በአግባብ አልተጠቀሙም፣ በደልን አድርሰዋል በሚል ክስ የተመሠረተባቸው ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ቤቹ፣ ክሱን “መሠረተ ቢስ ነው" በማለት ችሎት ፊት በቀረቡባቸው በርካታ ቀናት ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።

18 March 2023, 16:28