ፈልግ

የእስያ አህጉራዊ የኖዶሳዊነት ስብሰባ - ባንኮ የእስያ አህጉራዊ የኖዶሳዊነት ስብሰባ - ባንኮ  (CATHOLIC SOCIAL COMMUNICATIONS OF THAILAND)

ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ተሳትፎአቸው የሲኖዶሱ ታላቅ ሃብት መሆናቸው ተገለጸ

በጥቅምት ወር 2016 ዓ. ም. ለሚሰበሰብ ቅዱስ ሲኖዶሱ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የሚቀርብ የተግባር ሰነድ የሚያዘጋጅ ምክር ቤት ተቋቁሟል። የምክር ቤቱ አባል የሆኑት እህት ፊሎሜና ሂሮታ፣ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ለሲኖዶሱ ታላቅ ሃብት መሆኑን ገለጸዋል። የምክር ቤቱ ዋና ተግባር በሲኖዶሳዊ ሂደት ወቅት ከሁሉም አህጉራት የቀረቡትን ሃሳቦች እና አስተያየቶች በማሰባሰብ በ2016 ዓ. ም. በቫቲካን ለሚካሄድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የተግባር ሰነድን ማቅርብ ነው። ሰነዱን ከሚያዘጋጁት የምክር ቤቱ አባላት አንዷ የሆኑት እህት ፊሎሜና ዝግጅቱን የሚረዱ ልዩ ልዩ መንገዶችን፣ እውነታዎችን እና ልምዶችን ለምክር ቤቱ በማካፈል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚደርጉ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለቅዱስ ሲኖዶሱ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የሚቀርብ የተግባር ሰነድ የሚያዘጋጅ ምክር ቤት፣ መጋቢት 6/2015 ዓ. ም. በይፋ መቋቋሙ ይታወሳል። በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ውሳኔ መሠረት የተጀመረውን የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት ሂደት የሚያጠና ጉባኤ ሁለት ደረጃዎች ሲኖሩት የመጀመሪያው ሂደቱ በተጀመረበት ወቅት በየሀገራቱ የተካሄደው የሲኖዶሳዊነት ሂደት ሥነ-ሥርዓት ሲሆን ሁለተኛው በሲኖዶሳዊ ሂደት ወቅት ከመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ የተሰበሰቡ ሃሳቦችን እና አስተያየቶችን በያዘ የተግባር ሰነድ ላይ በጥልቀት የሚያሰላስል የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ነው። 

ማዳመጥ የሲኖዶሳዊ ሂደቱ ዋና ማዕከል ነው

በዚህ የሲኖዶሳዊ ሂደት መጀመሪያ ላይ “ለአንዲት ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ኅብረት፣ ተሳትፎ እና ተልዕኮ” በሚል መሪ ቃል በሁሉም አገራት ውስጥ የሚገኙት ሀገረ ስብከቶች፣ ቁምስናዎች፣ መንፈሳዊ ማኅበራት፣ ማኅበረሰቦች እና ግለሰቦች ራሳቸውን የጠየቁበት፣ ቀጥሎም በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ፣ በእስያ፣ በኦሺኒያ እና መካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ካቶሊክ ቤት ክርስቲያናት በአህጉራዊ ምዕራፍ ላይም ውይይት ያካሄዱበት መሪ ቃል ነው። ማዳመጥ የሚለው ቃል ማንንም ወደ ጎን ሳይሉ በሁለቱም የሲኖዶሳዊነት ሂደት ስብሰባዎች ጉልቶ የውጣ ቃል ነው። እርስ በርስ በመደማመጥ የተገኙት ሃሳቦች እና አስተያየቶች ወደ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ቀርበው፣ የጥምቀት ጸጋን የተቀበሉት እና ሐዋርያዊ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በሙሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚያሳዩት መለወጥ ወደ ሲኖዶሳዊነት ጎዳና ያመራሉ።

መሪያችን መንፈስ ቅዱስ ነው

የቅዱስ ሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች የሚመሩት የተግባር ሰነድ አዘጋጅ ምክር ቤት አባላት ሰባት ሲሆኑ፣ ከእነዚህ መካከል አንዷ የቶኪዮ ከተማ ነዋሪ እህት ፊሎሜና ሂሮታ ናቸው። በትውልድ ጃፓናዊት እህት ፊሎሜና ከዚህ በፊት አገልግሎታቸውን በኒካራጓ፣ በሜክሲኮ እና በፊሊፒንስ ያበረከቱ ሲሆን፣ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሮም ውስጥ ከሚገኝ “ፓክስ ክሪስቲ” ከተሰኘ ካቶሊካዊ ዓለም አቀፍ የሰላም እንቅስቃሴ ጋር በመተባበር አገልግለዋል።

በጃፓን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የተዘጋጀውን ስብሰባ መካፈላቸውን የገለጹት እህት ፊሎሜና፣ ከሲኖዶሳዊነት ሂደት የተለየ ቢመስልም በተመሳሳይ መንገድ መካሄዱን ገልጸው፣ ስብሰባውን የተሳተፉት “ታሊታ ኩም” የተሰኘ ዓለም አቀፍ የገዳማውያት አለቆች ኅብረት የእስያ አህጉር ተወካይ ሆነው እንደነበር ገልጸዋል። ከ “ታሊታ ኩም” ዓለም አቀፍ የገዳማውያት አለቆች ኅብረት ተልዕኮ መካከል አንዱ፣ በዓለም ዙሪያ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ የነበሩ ሴቶችን መልሶ ማቋቋም እንደሆነ የገለጹት እህት ፊሎሜና፣ በዚህ እና ሴቶችን በሚመለከቱ ሌሎች አገልግሎቶች ተሰማርተው ማገልገላቸውን አስረተዋል። ከሌሎች የገዳማውያት ማኅበራት ጋር ተባብረው መሥራታቸውን የገለጹት እህት ፊሎሜና፣ የአብዛኞቹ የገዳማውያት ማኅበርት መሥራቾች ዋና ዓላማ ሴቶችን ነፃ ማውጣት እንደነበር ገልጸዋል።

የቅዱስ ሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽ/ቤት ሰብሳቢ ከሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሆሌሪች በኩል በቀረበላቸው ጥያቄ መሠረት የምክር ቤቱ አባል ለመሆን ፈቃደኛ የሆኑት እህት ፊሎሜና፣ በሲኖዶሳዊ ሄደቱ የሴቶች ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፣ በሲኖዶሳዊ ጉዞ ወቅት በምንኩስና ሕይወት ውስጥ የሌሉ በርካታ ሴቶች እና ወንዶች እንዳሉ እና በዚህ ጉዞ መካከል የጳጳሳት ተልዕኮ እና ሥልጣን የእግዚአብሔርን ሕዝብ መወከል እንደሆነ አስረድተዋል። በቅርቡ በተቋቋመው ምክር ቤታቸው አማካይነት ለቅዱስ ሲኖዶሱ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የሚቀርብ የተግባር ሰነድ ማዘጋጀት መጀመራቸውን ያስታወቁት እህት ፊሎሜና፣ በሲኖዶሳዊነት ሂደት ከብጹዓን ጳጳሳት ጀምሮ እስከ ምዕመናን ድረስ ባሉ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ተሳትፎ ላይ ውይይት ማድረግ መጀመራቸውን ገልጸው፣ “የሲኖዶስ አንዱ ባህሪ የምዕመናን ልምድ ጎልቶ የሚታይበት፣ ሁላችንም የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች በመሆናችን መንፈስ ቅዱስን የምንለማመድበት መሆን አለበት” ብለዋል። በማከልም “ከእግዚአብሔር የሚገኝ የአንድነት ልምድ ሊኖር ይገባል፣ ለአንድነት ልምድም በእውነት መዘጋጀት አለብን” ብለዋል።

በሲኖዶሳዊ ሂደት ወቅት ቤተ ክርስቲያን በርካታ ከበድ ያሉ ጥያቄዎችን መቀበሏን የገለጹት እህት ፊሎሜና፣ በሲኖዶሳዊ ጉዞ ወቅት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር መወያየት እንደሚገባ፣ እስከ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ያልተወያዩባቸው ርዕሠ ጉዳዮች እንኳ ቢሆኑ ሳይደነግጡ በድፍረት መጋፈጥ እንደሚገባ ተናግረው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በ2015 እና 2016 ዓ. ም. ሁለት የብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባዎች እንዲካሄዱ የወሰኑበት ለዚህ ሊሆን እንደሚችል ገልጸው፣ ለቅዱስ ሲኖዶሱ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የሚቀርብ የተግባር ሰነድን የሚያዘጋጁ የምክር ቤቱ አባላት ከሚያዚያ ወር አጋማሽ ጀምሮ ወደ ሮም እንደሚመጡ አስረድተዋል። 

29 March 2023, 17:07