ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጉጄሮቲ፣ በሶርያ እና በቱርክ ውስጥ ጉብኝት በማድረግ ላይ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጉጄሮቲ፣ በሶርያ እና በቱርክ ውስጥ ጉብኝት በማድረግ ላይ  

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጉጄሮቲ፣ የሶርያ እና የቱርክ ጉብኝታቸውን አጠናቀዋል

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ሃላፊ፣ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፣ በሶርያ እና በቱርክ ሲያደርጉ የቆዩትን ጉብኝት ፈጽመው ተመልሰዋል። በቅርቡ በመሬት መንቀጥቀጥ የተጎዱ ሁለቱን አገራት፥ ሶርያን እና ቱርክን የጎበኙት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በአካባቢው ባለስልጣናት በኩል እንክብካቤ የሚደረግላቸውን ቤተሰቦች አጽናንተው፣ የሚላክላቸው ዕርዳታ አስተማማኝ እና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለተጎጂዎች እንዲደርስ የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፣ በሶርያ እና በቱርክ የመሬት መንቀጥቀጥ ባስከተለው አደጋ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀዋል። በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢዎች ጥር 29/2015 ዓ. ም. በተከሰተው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ከ47,000 የሚበልጡ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፣ የሶርያ ከተማ በሆነችው አሌፖ ውስጥ ባደረጉት የሁለት ቀናት ጉብኝት፣ በክርስቲያን፣ በሙስሊም እና በሕዝባዊ ተቋማት ሕንፃዎች ውስጥ በጊዜያዊነት የተጠለሉ በርካታ ቤተሰቦችን የጎበኟቸው ሲሆን፣ በመከራ ውስጥ የሚገኙትን በተለይም እናቶችን፣ የአካል ጉዳተኞችን እና ረዳት የሌላቸው አረጋውያንን በማጽናናት ብርታት ሰጥተዋል።

አብያተ ክርስቲያናትን ያካተተ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ከሚገኝባት የአሌፖ ከተማ በተጨማሪ፣ በባሕር ዳርቻዎች፣ በላታኪ አካባቢዎች እና በኢድሊብ አውራጃ የሚገኘውን የሰብዓዊ ዕርዳታ ጣቢያን ጎብኝተዋል። የሶርያ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የበጎ አድራጎት አገልግሎት ኮሚሽን እና ደማስቆ ከተማ ከሚገኝ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት በመተባበር ቀጣይነት ያለው ሰብዓዊ ዕርዳታ የማስተባበር ሥራን በማካሄድ እንደሚገኙ ታውቋል።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ሃላፊ፣ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፣ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በቱርክ እና በሶርያ ያደረጉት ጉብኝት በዋናነት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልካም ምኞት፣ ቡራኬ እና አጋርነት በማስተላለፍ ላይ ያተኮረ እንደነበር፣ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያን በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ሕዝቦች ለመርዳት የምታደርገውን ጥረት ለማስረዳት እንደነበር አስረድተዋል። በተለይ በሶርያ ግጭቶች ባሉበት የጦርነት ቀጣናዎች አስፈላጊውን ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ጠቁመው፣ በሶርያ እየደረሰ ያለው ስቃይ፣ ለአሥራ ሁለት ዓመታት የዘለቀው ጦርነት ኅብረተሰቡን መከፋፈሉን ገልጸው፣ በአካባቢው አስቸኳይ እርቅ እና ሰላም ሁሉም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የጋራ ተጠቃሚነት መንገድ መሆኑን አስረድተዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ አክለውም፣ ሶርያ ውስጥ ሰዎች ሙሉ በሙሉ በወደሙ፣ የጤና አገልግሎት፣ የትምህርት እና የሥራ ዕድሎች በሌሉባቸው አካባቢዎች ለመቆየት እንደሚገደዱ ገልጸው፣  በእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት በተጣለው ማዕቀብ ምክንያት መገለል ተባብሶ እንደቀጠለ ጠቁመዋል። የብዙኃን መገናኛን በነቀፉት አስተያየታቸው፣ ሶርያ ውስጥ ሕዝቡን የሚገጥመውን አስከፊ መከራ ብዙ ሰዎች እንደማያውቁት እና “ሶርያን ስለደረሰባት መከራ ማንም ሰው አይናገርም” በማለት ተናግረዋል።

በሁለቱም አገራት የሚገኙ የአደጋው ሰለባዎችን በመጎብኘት ያጽናኑት እና ብርታትን የተመኙት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፣ የሶርያ ችግሮች ዓለም አቀፍ ግንዛቤ እንዲኖረው እና የፖለቲካውን እውነታ በጥልቀት ማሰብ እንደሚገባ አሳስበው፣ ሁሉ ወደ መልካም ተለውጦ የአስቸኳይ ጊዜ ሰብዓዊ ዕርዳታ፣ ችግር ውስጥ ለሚገኝ ሕዝብ እንዲደርሰው ጥሪ አቅርበዋል።

 

06 March 2023, 14:54