ፈልግ

የገዳማት አለቆች የበይነ መረብ ላይ ስብሰባ የገዳማት አለቆች የበይነ መረብ ላይ ስብሰባ  

ገዳማውያት የማኅበራዊ መገናኛዎች አጠቃቀምን በተመለከተ የመጀመሪያ ስብሰባቸውን አካሄዱ

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ የልዩ ልዩ ገዳማውያት በማኅበራዊ መገናኛዎች አጠቃቀም ላይ ያላቸውን ተሳትፎ የተመለከተ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ ስብሰባ ተካሄደ። ዓላማው ገዳማውያቱ ወንጌላዊ የሕይወት ተሞክሮአቸውን በማኅበራዊ መገናኛዎች አማካይነት እንዴት በመመስከር በሕዝቦች መካከል ግንኝነት መፍጠር እንደሚቻል ለመረዳት እንደሆነ ታውቋል። የቅድስት መንበር መገናኛዎች ዋና ተጠሪ አቶ ፓውሎ ሩፊኒ ስብሰባውን በማስመልከት እንደተናገሩት፣ ቤተ ክርስቲያን የምታድገው ስለ እራሷ ማንነት በመናገር ሳይሆን በተግባር የምትኖረውን ሕይወት ለሌሎች በመግልጽ እንደሆነ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የገዳማውያት ተወካዮቹ የአውታረ መረብ ላይ ስብሰባቸውን ያካሄዱት፣ በተለያዩ መንፈሳዊ ተቋማት እና ገዳማት መካከል ያለውን ትስስር በማጠናከር፣ ወንጌልን በተግባር ለመመስከር እና ግንኙነቶችን ለማሳደግ በሚል ዓላማ በሚቀጥለው ዓመት ኅዳር ወር ላይ ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የገዳማውያት የበላይ አለቆች ኅብረት ጉባኤ ዝግጅት እንዲሆናቸው በማሰብ እንደሆነ ታውቋል።

የመልዕክቱ ማዕከል የሰው ልጅ ነው

የዓለም አቀፍ የገዳማውያት የበላይ አለቆች ኅብረት ፕሬዝዳንት እህት ናዲያ ኮፓ፣ በማኅበራዊ መገናኛዎች በኩል የሚተላለፉ ቃላት፣ ምስሎች እና ሃይማኖታዊ ምልክቶች በሰዎች መካከል ግንኙነትን እና አንድነትን  የመፍጠር ሃይል እንዳላቸው፣ በጥንቃቄ ከተመረጡ ሰላምን መፍጠር፣ አለመግባባቶችን ማስወግድ እና አስተሳሰብን መለወጥ እና በአጠቃላይ ለውጥን ማምጣት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

በዚህ መካከል የመልዕክቱ ዋና ማዕከል የሰው ልጅ መሆን አለበት ያሉት ኅብረት ፕሬዝዳንት እህት ናዲያ፣ መል ዕክቱን በማስተላለፍ ዲጂታል መገናኛዎች ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ፣ በእርግጥ የዲጂታል መገናኛዎች ከኃላፊነት ጭምር ታላቅ የእግዚአብሔር ስጦታዎች እንደሆኑ ገልጸው፣ ግንዛቤን ማስፋት እንደሚችሉ፣ ልብን በመክፈት እና ለመንገዳችን ብርሃን በመሆን፣ ምናባዊ እውነታን ሳይሆን ለሕይወት ጉዞ ብርሃን በመሆን የሚረዱ መሆናቸውን እህት ናዲያ ተናግረዋል።

ዲጂታል መገናኛዎችን በአግባቡ መጠቀም

ከዚህ አንፃር ስብሰባው የሚካሄድበት እና ዓመቱን ሙሉ ከሚሰጡ የመሰናዶ ኮርሶች ዓላማዎች መካከል አንዱ ገዳማውያትን በብዙኃን መገናኛዎች እና በማኅበራዊ ድረ-ገጾች አጠቃቀም ላይ ማሰልጠን እንደሆነ የገለጹት እህት ናዲያ፣ ይምህ በምንኩስና ሕይወታቸው ውስጥ አስፈላጊ ክፍል በመሆኑ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ማወቅ እንደሚፈልጉ ተናግረው፣ በዲጂታል መገናኛዎች አማካይነት የምንኩስና ሕይወትን እና ታማኝ የምሥክርነት ምልክቶችን በተሻለ መንገድ ለሌሎች ማስተላለፍ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። ማኅበራዊ መገናኛዎች ሐዋርያዊ ተግባራትን ለማስተላለፍ ጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ፣ የጸሎት ሥነ-ሥርዓቶችን ለማስተባበር፣ መልካም የሐሳብ ልውውጦችን ለማድረግ፣ የልዩ ልዩ ገዳማዊ ማኅበራት ተልዕኮ እና ራዕይ እንዲታወቅ ለማድረግ እና በገዳማቱን በኩል የሚቀርቡ አገልግሎቶችን እና እውነተኛ ገጽታቸውን ለተመልካች ወይም ለአድማጭ በማቅረብ ከፍተኛ እገዛን ማድረግ እንደሚችሉ አክለው አስረድተዋል።

ልምዶችን መመስከር

የቅድስት መንበር መገናኛዎች ዋና ተጠሪ አቶ ፓውሎ ሩፊኒ በሌላ በኩል፣ ቤተ ክርስቲያን የምታድገው ስለ እራሷ ማንነት በመናገር ሳይሆን በተግባር የምትኖረውን ሕይወት ለሌሎች በማሳየት እንደሆነ ገልጸው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዓለም አቀፍ ማኅበራዊ መገናኛ ቀን መልዕክታቸው፣ “እርስ በርስ በመቀራረብ ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን እንዴት እንኖረዋለን” ማለታቸውን በማስታወስ፣ ጉዞአችንን ለሌሎች ማጋራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ዓላማው የመገናኛ ባለሙያዎች ለመሆን ቢሆንም፣ ነገር ግን በሙያው ልዩ ቴክኒካዊ ብቃት እንዲኖረን ለማድረግ ሳይሆን አንድነትን በመፍጠር ሕይወትን የሚቀይር ልምድን ለመመስከር እንደሆነ አስረድተዋል።

የ "ጴንጤቆስጤ" ፕሮጀክት

“ያለ ማኅበራዊ ግንኙነት አንድነት የለም፤ ያለ አንድነት ማኅበራዊ ግንኙነት የለም” ያሉት የቅድስት መንበር መገናኛዎች ዋና ተጠሪ አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣ ይህ ማለት ግን የተደረጉትን፣ የተባሉትን ወይም የሚባሉትን ነገሮች መዘርዘር ማለት እንዳልሆነ፣ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ዕርዳታ በመለመን በቅዱስ ወንጌል በእውነት ላይ ማተኮር ማለት እንደሆነ አስረድተዋል። ይህም በገዳማውያቱ እና በጽ/ቤታቸው አንደነትን በመፍጠር በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እና ለመመስከር እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል። በዚህ ረገድ ወደ ኅብረት እና ውህደት የሚያመጣውን የዓለማችን ጠንካራ የግንኙነት ሥርዓትን መመሥረት፣ በጽ/ቤታቸው የተቋቋመውን የ "ጴንጤቆስጤ" ፕሮጀክት ምኞት እንደሆነ ገልጸው፣ በፕሮጀክቱ ዙሪያ በርካታ መነኮሳት ቀድሞውኑ በኃላፊነት ቦታ ላይ ሆነው፣ በቫቲካን መገናኛዎች ውስጥ ዓለም አቀፍ የመነኮሳት ድምጽ አውታረ መረብን በመፍጠር በምስክነት፣ በተባባሪነት እና በተርጓሚነት እየሠሩ እንዳሉ ገልጸው፣ ዓላማው በጉዞ ላይ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያንን ለሌሎች መመስከር እንዲያስችል በመገናኛ ብዙሃን፣ በተለያዩ ቋንቋዎች እና ባሕሎች አማካይነት በኅብረት መሥራት እንደሆነ አስረድተዋል።

25 January 2023, 17:05