ፈልግ

የድሆች ቀን ኢየሱስን በወንድሞቻችን እና እህቶቻችን መካከል ለማግኘት እንደሚያስችል ተገለጸ

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኅዳር 4/2015 ዓ. ም. ለስድስተኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን ምክንያት በማድረግ በቫቲካን በሚገኝ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለድሆች የታቀዱ የዕርዳታ አገልግሎቶች መጀመራቸውን በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚዳንት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ገልጸው፣ በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ልዩነት እየጨመረ በመጣበት በዛሬ ዓለማችን ድሆችን ማገልገል ተጨባጭ የቤተ ክርስቲያን ምስክርነት መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከታወጀ ስድስት ዓመታትን ያስቆጠረውን ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ኅዳር 4/2015 ዓ. ም በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ከድሆች ጋር በሚያቀርቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የሚከበር መሆኑ ታውቋል። ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን እንዲከበር፣ በምሕረት ዓመት ኢዮቤልዩ ማገባደጃ ላይ ማለትም እ. አ. አ. በ2016 ዓ. ም. ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ማወጃቸው ይታወሳል። ዓላማው ክርስቲያኖች በሙሉ በተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ውስጥ ወድቀው ወደሚገኙ ሰዎች ዘንድ ደርሰው  የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር በተጨባች አገልግሎት እንዲገልጹ ለማበረታታት በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት በየዓመቱ የሚከበር መሆኑን የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ፕሬዚዳንት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ አስረድተዋል።

ድሆች የቅዱስ ወንጌል ምስክሮቻችን ናቸው!

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ለድሆች የጤና አገልግሎቶችን ለማቅረብ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተቋቋሙ ክሊኒኮችን ኅዳር 1/2015 ዓ. ም. መርቀው በከፈቱበት ሥነ ሥርዓት እንደተናገሩት፣ ድሆች ወደ እግዚአብሔር የቀረቡ ብቻ ሳይሆን የእርሱ ምስክሮች መሆናቸውንም አስረድተዋል። በማከልም ድሆች ለሚያምኑት ሆነ ለማያምኑት የወንጌል ትርጉም በዛሬው ዓለም አቅመ ደካማ ለሆኑት ሰዎች አገልግሎት መስጠት መሆኑን እንድንረዳ ያግዛሉ ብለዋል።

ድህነት በዓለም እየጨመረ ይገኛል

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ኅዳር 1/2015 ዓ. ም. ተመርቆ የተከፈተው ክሊኒክ በተለያዩ ሕመሞች ማለትም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና ኤችአይቢን ጨምሮ በሌሎች ሕመሞች ለሚሰቃዩ ድሃ ማኅበረሰብ ነጻ የምርመራ እና የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመ መሆኑ ታውቋል። ነጻ አገልግሎቱ የድሆች ቁጥር በአሥር እጥፍ እየጨመረ ባለበት በዚህ ወቅት ይበልጥ አንገብጋቢ መሆኑን ገልጸው፣ ችግሩ በሮም እና አካባቢዋ የሚኖሩ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ የሚገኙትም ጭምር መሆኑን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ አስረድተዋል።

ጤና ፣ ምግብ ፣ ገንዘብ

ቫቲካን በሮም እና አካባቢዋ ለሚገኙ ድሆች ምግብ ማደል ብቻ ሳይሆን ወርሃዊ ወጭዎችንም የሚሸፍንላቸው መሆኑን፣ ይህን ዕርዳታ ምንም ለሌላቸው ድሆች ብቻ ሳይሆን ከወር ወር መድረስ ለማይችሉ ቤተሰቦችም የሚያቀርብ መሆኑን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ አስረድተዋል። በጣሊያን ብቻ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ተረጂዎች እናዳሏቸው ያስታወቁት አቡነ ፊዚኬላ፣ ጣሊያን ከስድስት ሃብታም አገሮች መካከል አንዷ መሆኗን ገልጸው፣ በማደግ ላይ በሚገኙ የእስያ፣ የላቲን አሜሪካ እና የአፍሪካ አገራት መካከል ችግሩ ምን ያህል ሊበረታ እንደሚችል መገመት ይቻላል ብለዋል።

ከባዱ ፈተናችን ድህነት ነው!

ከዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሀገር ጎብኚዎች ወደ ቫቲካን እንደሚመጡ የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊዚኬላ፣ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ሲደርሱ የቦታውን ውበት ከማድነቅ በተጨማሪ በአደባባዩ የተቋቋሙ የነጻ ሕክምና መስጫ ክሊኒኮችን ሲመለከቱ ድህነት ዓለማችንን ምን ያህል እንደጎዳው እና ከባዱ ፈተናችን መሆኑን በቀላሉ ሊገነዘቡት ይችላሉ ብለዋል።

12 November 2022, 16:12