ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በጦርነት ወቅት ባሕሬንን መጎብኘታቸው የውይይት ምልክት መሆኑ ተገለጸ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከጥቅምት 24-27/2015 ዓ. ም. ድረስ በባሕሬን የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት የቅድስት መንበት ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ከቫቲካን ሚዲያ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። አስቸጋሪ በሆነ የታሪክ አጋጣሚ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በባሕሬን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የእርስ በርስ ውይይትና የአንድነት ምልክት እንደሆነ አስረድተው፣ ንጉሥ ሃማድ ቢን ኢሳ አል ካሊፋን እና በአገሪቱ የምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳትን ለግብዣቸው አመስግነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ከሐሙስ ጥቅምት 24-27/2015 ዓ. ም. ድረስ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በባሕሬን እንደሚያካሂዱ የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ማስታወቁ ይታወሳል። በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ሁለቱን ከተሞች እነርሱም ማናማንና አዋሊን ጉብኝተው፣ “የምሥራቁ እና የምዕራቡ ዓለም የሰው ልጆች አብሮ መኖር” በሚል ርዕሥ በባሕሬን ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል። የባሕሬን ጉብኝታቸው በብሔራዊ ስታዲዬም የሚያሳርጉትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓትንና በቅዱስ ልበ ኢየሱስ ትምህርት ቤት ውስጥ ከወጣቶች ጋር የሚያደርጉትን ስብሰባ የሚያካትት መሆኑ ታውቋል።

የቅድስት መንበት ዋና ጸሐፊው ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን “ሎዘርቫቶሬ ሮማኖ” ከተሰኘ ዕለታዊ የቅድስት መንበር ጋዜጣ እና ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ “ዓለማችን በውጥረት፣ በተቃውሞ እና በግጭት ውስጥ በሚገኝበት ወቅት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በባሕሬን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማካሄድ የሚሳተፉባቸው መድረኮች የአንድነት፣ አብሮ የመኖር እና የሰላም መልዕክቶች" ናቸው ብለዋል። ንጉሡ ቅዱስነታቸው ባሕሬንን እንዲጎበኙ በግል ደረጃ ያቀረቡትን ግብዣ ሕጋዊ ማድረጋቸው ሲታወቅ፣ ጉብኝታቸውም “የምሥራቁ እና የምዕራቡ ዓለም ለሰው ልጆች አብሮ መኖር” በሚል ርዕሥ በባሕሬን ለመጀመሪያ ጊዜከበሚዘጋጀው የውይይት መድረክ ጋር በተመሳሳይ ወቅት የሚካሄድ መሆኑ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስታውቀዋል። 

ንጉሡ ባደረጉላቸው ግብዣ ላይ በባሕሬን የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ የሆኑት የብጹዕ አቡነ ሂንደር ግብዣ መታከሉን አስታውቀው፣ አጋጣሚውን በመጠቀም ሁለቱንም ወገኖች ማለትም ግርማዊ ሃማድ ቢን ኢሳ አል ካሊፋን፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናትን እና በአገሪቱ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርቲያንን ብጹዓን ጳጳሳትን ለግብዣቸው አመስግነው፣ የቅዱስነታቸውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት እያደረጉት ላለው ዝግጅት እና ለሚደረግላቸው መልካም አቀባበል ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ምስጋናቸውን በድጋሚ አቅርበውላቸዋል።

“በባሕሬን ከተዘጋጀ የውይይት መድረክ የሚወጣው መልዕክትና የቅዱስነታቸው ተሳትፎ ግልጽ ይመስለኛል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ “በታሪካችን ውስጥ በተለይ ውስብስብ እና አሳዛኝ በሆነው በዚህ ወቅት ላይ የቅዱስነታቸው ጉብኝት የአንድነት ምልክት ነው” ብለዋል። በምሥራቅ እና በምዕራብ መካከል ሰላማዊ ግንኙት እንዲኖር የሚጋብዝ የውይይት መድረኩ፣ ብዙ ሕዝቦች፣ ባሕሎች እና ሃይማኖቶች በሚገኙባት ባሕሬን፣ አብሮ በሰላም የመኖር እና የመተባበር መልዕክትን የሚያስተላልፍ እንደሚሆን በማከል አስረድተዋል። በተጨማሪም በዚያው አጋጣሚ ከሙስሊም ሽማግሌዎች ምክር ቤት በኩል በሃይማኖቶች መካከል መከባበር እና በጋር መወያየት እንዲኖር የሚያደርጉ ሁለት ስብሰባዎች እንደሚካሄዱ አስታውቀዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከተለያዩ አገራት የተወጣጡ የአብያተ ክርስቲያናት ወካዮች ስብሰባ እንደሚካሄድ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ በውጥረት፣ በልዩነት እና በግጭት ውስጥ በሚገኝ ዓለማችን ውስጥ አንድነት እና በሰላም አብሮ መኖርን በማሳሰብ መልዕክቱ ሁሌም አንድ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከመስከረም 3-5/2015 ዓ. ም. በካዛኪስታን ያደረጉትን 38ኛው ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝትን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ባለፈው ዓመት በኢራቅ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ ከዚያም በፊት በአረብ ኤሚሬቶች፣ በሞሮኮ፣ በግብፅ እና በአዘርባጃን ያደረጉትን ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝቶችንም አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በእነዚህ አገራት ያደረጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶች፣ እግዚአብሔር እና የሕዝቦች ጥላቻ፣ ሐይማኖት እና አመጽ፣ ፍጹም የማይጣጣሙ እና ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው ነገሮች ባሉበት ወቅት መሆኑን አስታውሰው፣ ጥላቻን እና አመጽን የሚደግፍ ትክክለኛውን የሃይማኖት ተፈጥሯዊ አቋምን የሚያዛባ መሆኑን አስረድተዋል። 

ቅዱስነታቸው በካዛኪስታን ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ውስጥ የሚገኙ ሁለት ነጥቦችን ማስታወስ አስፈላጊ እንደሆነ የገለጹት ብጹዕነታቸው፣ በአንድ በኩል ሐይማኖትን የአመጽና የጦርነት መሣሪያ በማድረግ፣ ሥልጣንን በመጠቀም ለጭቆና ከመጠቀም ፈተና ነጻ ለመውጣት ቅዱስነታቸው ማሳሰባቸውን፣ በሁለተኛ ደረጃ ሐይማኖቶች ከዚህ አንጻር ተባብረው መሥራት ከቻሉ፣ ማንኛውንም አለመግባባት በማስወገድ፣ ዘወትር የእርቅ፣ በሰላም አብሮ የመኖር እና የመተሳሰብ መንገድ እንዲሆን ማድረግ የሚቻል እንደሆነ መወያየታቸውን አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የመኖር፣ የአንድነት እና የምድርን ሃብት በፍትሃዊ መንገድ በጋራ መካፈልን ከብዙ ሰዎች መሠረታዊ መብቶች ጋር በማዛመድ እንደሚመለከቱ ገልጸው፣ በዚህም ቢሆን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ድምጻቸው ለታፈነባቸው ድምጽ በመሆን፣ በአንዳንድ መልኩ ከማኅበረሰቡ ከተገለሉ ሰዎች ጋር ለመገናኘት በልዩ ልዩ አገራት ሐዋርያዊ ጉብኝት ማካሄዳቸውን አስታውሰዋል።

ባሕሬን በእስላማዊ መንግሥት የምትተዳደር አገር እንደሆነች የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ በአገሪቱ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ቁጥር ከጠቅላላው ሕዝብ መካከል አሥር በመቶ እንደሆነና ከእነዚህም ውስጥ የካቶሊክ ምዕመናን ቁጥር ከ80 እስከ 100 ሺህ እንደሚደርስ ገልጸዋል። ባሕሬን ከቅድስት መንበር ጋር ግንኙነት የመሠረተችው እ. አ. አ በ2000 ዓ. ም. እንደሆነ ገልጸው በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነትም ጥሩ እንደሆነ አስረድተዋል። መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ ካቶሊክ ምዕመናንና ለሐዋርያዊ እንደራሴ የሚሰጠው አክብሮትና ትብብር ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸው፣ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝትም ከዚህ ማኅበረሰብ ጋር ለመገናኘት እና በሕይወት ምስክርነቱ ለማበረታታት እንደሆነ አስረድተዋል።

በባሕሬን አዋሊ ከተማ የተገነባው “የአረቡ ዓለም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል” ፣ በአገሪቱ የሚገኝ ካቶሊክ ማኅበረሰብ እምነቱን የሚለማመድበትን ሥፍራ በማመቻቸት ከፍተኛ ድጋፍ ከማድረጉ በተጨማሪ የአገሪቱ መንግሥት ለክርስቲያን ማኅበረሰብ የሚሰጠውን ትኩረትና አክብሮት በማሳደግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አስረድተዋል። ካቴድራሉ የባሕሬን መንግሥት ለክርስቲያን ማኅበረሰብ እስካሁን ያለውን አመለካከት በማጉላት፣ ለምንመኘው መልካም ምልክት እና ተጨባጭ ግንኙነት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን፣ የቅድስት መንበት ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ከቫቲካን ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

02 November 2022, 16:45