ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ በአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ በአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ   (AFP or licensors)

ካርዲናል ፓሮሊን፣ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ሊባክን የማይችል ዕድል መሆኑን ገለጹ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባዘጋጀው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ በመገኘት ንግግር አድርገዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ቅድስት መንበር እንደ አገር በፓሪሱ ስምምነት ላይ ያላትን ተሳትፎ ለጉባኤው ተካፋዮች በመግለጽ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮትን ለመቅረፍ ዓለም አቀፋዊ እና ቀጣናዊ ትብብር ሊኖር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ከዚህም ጋር በማያያዝ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጉባኤው ተካፋዮች ጋር እንደሚተባበሩ፣ ድጋፍን በማድረግ ብርታትን መመኘታቸውን አረጋግጠውላቸዋል። ከጥቂት ቀናት በፊት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በባሕሬን ባስተላለፉት መልዕክት፣ ጉባኤው መልካም ውጤቶችን ይዞ እንደሚወጣ ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ ሳይዘገይ ወጣቱን ትውልድ ግምት ውስጥ በማስገባት በተጨባች እና ብልህ ምርጫዎች አማካይነት አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሚሄድ ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ቅድስት መንበር እ. አ. አ ከ2050 ዓ. ም. በፊት የተጣራ የአየር ልቀትን ወደ ዜሮ ለመቀነስ የገባችውን ቁርጠኝነት በማስታወስ፣ በዋናነት ሥነ-ምህዳር ትምህርትን ለማስፋፋት ያላትን ቁርጠኝነት ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት "የግል እና የጋራ ተሃድሶ" እና "ሊራዘም የማይችሉ ተጨባጭ ውሳኔዎችን" የማድረግ አስፈላጊነትን አጉልተው ተናግረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ እና የሰው ልጅ

በተለይም የአየር ንብረት ለውጥ በሰው ልጅ ላይ ሊያስከትል ለሚችለው አደጋ ትኩረት የሰጡት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ “በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርሱትን ተደጋጋሚ እና ከባድ ሰብዓዊ ተጽዕኖዎች ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት ተጨባጭ እርምጃ የመውሰድ የሞራል ግዴታ አለብን” ብለዋል። ከዚህም ጋር በተያያዘ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት መፈናቀል እና ስደት እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ ምልክት መሆኑን ጠቁመው፣ ይህን ችግር ለማስወገድ በማይቻልበት ወቅት ለስደተኞች የሚሆን መደበኛ የጉዞ መንገዶችን ማመቻቸት እና ተደራሽነትን ማሳደግ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ቆሞ አይጠብቀንም!

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን የዓለም አቀፍ ክስተቶች አደገኛነት በመጠቆም ባቀረቡት ማስጠንቀቂያ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው የግጭቶች እና የጦርነት ክስተቶች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አገራት ጥረቶችን ፈተና ላይ መጣሉን ገልጸዋል። “ይህ እንዲሆን መፍቀድ የለብንም” ያሉት ብጹዕነታቸው በሌላ በኩል "የአየር ንብረት ለውጥ ቆሞ የማይጠብቀን አደጋ ነው” በማለት አስጠንቅቀዋል።

“ዓለም አቀፋዊ እና ቀጣናዊ ትብብር” እንደሚያስፈልግ አጥብቀው የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ “ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችንም ጭምር ኃላፊነት የሚሰማን፣ ደፋር እና መልካም የወደፊት ሕይወት ፈላጊዎች መሆን አለብን” ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በግላስጎው ተዘጋጅቶ ለነበረው የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ያስተላለፉትን መልዕክት ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ “የፖለቲካ ፍላጎታችን መመራት ያለበት፣ የመጣብንን አደጋ ማሸነፍ የሚቻለው በኅብረት ስንሆን፣ ካልሆነም የምንጎዳው በጋራ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።

ሌላ ዕድል ካለ!

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን የፓሪሱን ስምምነት ዓላማዎችን ለማሳካት ያለውን ውስብስብነት አምነው፣ ይህንንም ቢሆን ለማስተካከል ያለው ጊዜ እያጠረ መሄዱን አስታውቀዋል። "የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ሊባክን የማይችል ሌላ ተጨማሪ ዕድል እንደሚሰጠን የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፣ የቅድስት መንበር ቁርጠኝነት እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፣ ይህን ጉዞ በጋራ በመጓዝ፣ ለሰው ልጅ የጋራ ጥቅም እና በተለይም ወጣቶችን በመወከል የዛሬውን እና የወደፊቱን ትውልድ እንድንከባከብ የሚሹ መሆኑን አስረድተዋል።

09 November 2022, 16:58