ፈልግ

ቅዱስነታቸው በባሕሬን ከሙስሊም ምክር ቤት አባላት ጋር ያደረጉት ስብሰባ ቅዱስነታቸው በባሕሬን ከሙስሊም ምክር ቤት አባላት ጋር ያደረጉት ስብሰባ   (Vatican Media)

ብጹዕ ካርዲናል አዩሶ፣ በሐይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት የህልውና መግለጫ መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በባሕሬን ከጥቅምት 24-27/2015 ዓ. ም. ድረስ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስታወስ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ አስተያየታቸውን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የጋራ ውይይት፣ እርስ በርስ መከባበር፣ ወንድማማችነት እና ሰላም የሚሉ አራት ቁልፍ ርዕሠ ጉዳዮችን መሠረት በማድረግ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በባሕሬን ባደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ላይ ያላቸውን አስተያየት ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በባሕሬን ያደረጉት የአራት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪ ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ውጭ አገር ያደረጉት 39ኛ እና ሁለተኛው የባሕረ ሰላጤው ክልል ሐዋርያዊ ጉብኝት መሆኑ ታውቋል። ያለፉትን ጥቂት ቀናት የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት መለስ ብለው የተመለከቱት፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ፣ በሙስሊም እና ክርስቲያን ሐይማኖቶች መካከል በቀጣይነት የተካሄደው ውይይት አስፈላጊ እና ጥልቅ የህልውና ብቃትን የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል።

በሌሎችም የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ፍጻሜ ላይ አዎንታዊ የሆኑትን ውጤቶችን እንደሚያገኙ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል አዩሶ፣ የባሕሬንን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት ባቀረቡት አስተያየት ፣ ሐዋርያዊ ጉብኝቱ የተካሄደው ዓለማችን በግጭት ውስጥ በሚገኝበት ወቅት በመሆኑ እጅግ የረኩበት መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከሲቪል ማኅበረሰቦች ተወካዮች፣ ከዲፕሎማሲ አካላት እና ከክርስቲያን ማኅበረሰብ ጋር የተደረገው ስብሰባ አስደሳች እንደነበር የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል አዩሶ፣ በተለይም በአገሪቱ ብሔራዊ ስታዲዬም ውስጥ ከባሕሬን እና ከመላው የባሕረ ሰላጤ አካባቢ አገራት ከመጡት ክርስቲያን ማኅበረሰብ ጋር የቀረበው የጋራ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ያስደሰታቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ከልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ጋር የተካሄደው ስብሰባም በጣም አስፈላጊ እንደ ነበር የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል አዩሶ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደተመኙት ሁሉ ግልጽነት ያለው የውይይት፣ የመተዋወቅ እና የወንድማማችነት ጉዞ ስብሰባ እንደ ነበር ገልጸዋል። በባሕሬን ውስጥ በሐይማኖቶች መሪዎች መካከል የተደረገው ስብሰባ ከዚህ በፊት በክርስቲያኖች እና በሙስሊሞች መካከል ሲካሄድ የቆየው የጋራ ውይይት ቀጣይ ምዕራፍ እንደነበር ገልጸው፣ በሐይማኖቶች መሪዎች መካከል የሚደረግ የጋራ ውይይት በየቀኑ የሚኖሩት የህልውና ብቃት መግለጫ መንገድ መሆኑን አስረድተዋል።

በባሕሬን ከሙስሊም ሽማግሌዎች ምክር ቤት አባላት ጋር የተደረገው ስብሰባ አስደሳች እንደነበር የገለጹት ብጽዕ ካርዲናል አዩሶ፣ ተቋሙ በአገሪቱ ውስጥ ዕውቅና ያለው መሆኑን ተናግረው፣ በሂደት ላይ የሚገኘውን የእስልምና እና የክርስትና እምነቶች ውይይቶችን ለማሳደግ እና ለማስቀጠል፣ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብን ለመጥቀም በተጀመሩ የዕቅድ መርሃ ግብሮች ላይ ለመተባበር እና በልዩነት ውስጥ አንድነትን ለመፍጠር ፍላጎት ያለው ተቋም መሆኑን ገልጸው፣ ከዚህም በተጨማሪ ለሐይማኖቶች ውይይት እና በተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ በተለይም በሙስሊሙ ዓለም መካከል ውይይቶችን ለማካሄድ ፍላጎት ያለው ተቋም መሆኑን አስረድተዋል።

የግብጽ አል አዛር መስጊድ ታላቁ ኢማም ፕሮፌሰር ሙሐመደ አህመድ አል ጣይብ በባሕሬኑ ስብሰባ ላይ በድጋሚ መገኘታቸውን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል አይሶ፣ ፕሮፌሰሩ ለስብሰባው ተካፋዮች ባቀረቡት ግልፅ መልዕክት፣ በሙስሊሙ ዓለም በሺዓዎች እና በሱኒዎች መካከል መቀራረብ ሊኖር እንደሚችል ገልጸው፣ ይህንም በስብሰባው ላይ ከቀረቡ ጠቃሚ መልዕክቶች መካከል እንደ አንዱ በመውሰድ፣ የጋራ ውይይቱ ቀጣይነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

በባሕሬኑ ስብሰባ ላይ የቁንስጥንጥንያው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ በርተሎሜዎስ መገኘት በጣም አስፈላጊ እንደ ነበር የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል አዩሶ፣ ይህም ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ያላቸውን የወዳጅነት እና የወንድማማችነት ኅብረት ማደሳቸውን የሚገልጽ እንደ ነበር አስረድተዋል። በእስልምና እምነት ውስጥ በሺዓዎች እና በሱኒዎች እንዲሁም ከሌሎች የሙስሊሙ ዓለም አካላት መካከል ጠቅላላ ውይይት እንዲኖር እንፈልጋለን ያሉት ብጹዕ ካርዲናል አዩሶ፣ በክርስቲያናው ዓለምም በተለያዩ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች መካከል የአብያተ ክርስቲያናት ውይይት ሊኖር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በዚህም መሠረት የቁንስጥንጥንያው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ በርተሎሜዎስ፣ መጓዝ ያለብንን አቅጣጫ እንደሚጠቁሙ ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ በርተሎሜዎስ ጋር ያላቸው አንድነት በአብያተ ክርስቲያናት መካከል የሚደረገውን ውይይት ለማሳደግ የሚረዳ መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በባሕሬን ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት “ውይይት” በሚለው ቃል ማጠቃለል እንደሚቻል የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል አዩሶ፣ በሰላም ጎዳና በእውነት ለመጓዝ ከፈለግን የጋራ ውይይቶችን ማስፋፋት፣ አንዱ ሌላውን የማክበር ባሕልን ማሳደግ እና “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ላይ በሰፊው የተገለጸውን ወንድማማችነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ አስተያየታቸውን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

08 November 2022, 16:15