ቅድስት መንበር፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ለሰው ልጅ የጋራ ጥቅም እንዲውሉ አሳሰበች
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በመገናኛው ዓለም የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕድገት የዜጎችን የጋራ ተጠቃሚነት እና ፍላጎቶቻቸውን መሠረት በማድረግ ማዳመጥ እንደሚገባ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መናገራቸውን በማስታወስ፣ ማዳመጥ የመጀመሪያው አስፈላጊ የውይይት እና የመልካም ግንኙነት አካል እንደሆነ መግለጻቸውን፣ ዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ማኅበር ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ የተገኙ የቅድስት መንበር ኡካን መሪ እህት ራፋኤላ ፒዬትሪኒ ገልጸዋል።
በዓለም ዙሪያ ያሉ የቴሌኮሙኒኬሽን ማኅበራትን ማስተባበር
በጄኔቭ የሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ኤጀንሲ እና ታሪካዊው የዓለም አቀፍ ቴሌኮሙኒኬሽን ኅብረት፣ የሬዲዮ ሞገድን እና የሳተላይት ምህዋር ዓለም አቀፍ አጠቃቀምን በጋራ ለማስተባበር ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል። ሁለቱ ድርጅቶች ዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ደረጃዎችን በማውጣት እና ለመረጃ ልውውጥ አስፈላጊ የሆኑ የተቀናጁ የቴክኖሎጂዎች ፍትሃዊ እና ተመጣጣኝ ተደራሽነትን በማበረታታት ላይ መሆናቸው ታውቋል።
የማኅበራዊ ትስስር እና የአብሮነት መድረኮችን ማስተዋወቅ
አስቸጋሪ ፈተናዎች ያጋጠሟቸው ብዙ መንግሥታት በዓለም አቀፍ ትስስር የወደፊት አቅጣጫዎች ላይ በሚወያዩበት እና በሚከራከሩበት ሰፊ ዓለም አቀፍ አውድ ውስጥ የቫቲካን ልኡካን መካፈሉ ልዩ ዕድል መሆኑን የገለጹ እህት ራፋኤላ፣ መርሆቹ ቅድስት መንበር እና የቫቲካን ከተማ አስተዳደር በዲጂታል ቴክኖሎጂ ልማት እና ተጨባጭ አጠቃቀም ላይ መተግበር የሚፈልጓቸው መሆኑን አስረድተዋል። በተለይም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ደጋግመው እንደሚናገሩት፣ ጉዳዩ ውጤታማ የማኅበራዊ ትስስር እና የአብሮነት መሣሪያ የሆኑትን የዓለም አቀፍ የመገናኛ መድረኮችን ዕድገት ማስተዋወቅ ነው ብለው፣ በተለይ ለሴቶች፣ ለወጣቶች እና ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት በመስጠት፣ ሰብዓዊ መብቶችን፣ ባሕላዊ ወጎችን በማክበር፣ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ የሆኑ የአንድነት መንገዶችን ለማዘጋጀትን ማቀድ ያስፈልጋል ብለዋል።
የቅድስት መንበር መርሆችን ወደ ቴክኒካል ዘርፎች ማምጣት
በውሳኔ ሰጪ አካላት መካከል የቅድስት መንበር ዓለም አቀፍ ውክልና በዲጂታል እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘመን የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን እና አደጋዎችን ወደ ዓለማዊ ዘርፎች ለማምጣት ጉባኤው መልካም ዕድሉ ማዘጋጀቱን አባ ሉቾ አድሪያን ሩዊዝ ገልጸዋል። የሰውን ልጅ ማዕከላዊነት ፣ ግንኙነቶችን ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን የማካተት አስፈላጊነትን የተናገሩት አባ ሉቾ አድሪያን፣ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ሕፃናትን፣ ወጣቶችን እና አዛውንትን ከጉዳት መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ ዘላቂነት፣ አካታችነት፣ ልማት እና አዳዲስ ዕድሎች በቴክኖሎጂ መስክ መሠረታዊ በሆኑ መርሆች በመመራት ለሰው ልጅ ሕይወት፣ ለሥራ ክብር እና ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እንክብካቤ፣ በሦስተኛው ሺህ የዲጂታል ለውጥ ውስጥ ቅድስት መንበር ወሳኝ ሚና መጫወት የምትችል መሆኑን አስረድተዋል።