ፈልግ

ዘንድሮ በእንግሊዝ ውስጥ የተካሄደ የላምቤት ኮንፈሬንስ ተካፋዮች ዘንድሮ በእንግሊዝ ውስጥ የተካሄደ የላምቤት ኮንፈሬንስ ተካፋዮች  

ብጹዕ ካርዲናል ታግለ፣ ሰብዓዊ ቤተሰብን እና ፍጥረትን ለማሳደግ እንደሚያልሙ ገለጹ

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲና ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ በእንግሊዝ ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 2-2014 ዓ. ም. ሲካሄድ ለሰነበተው ዓለም አቀፍ ጉባኤ መልዕክት አስተላልፈዋል። በእንግሊዝ ውስጥ ላምቤት ኮንፈሬንስ ውስጥ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ማኅበራዊ ሕይወትን የተመለከቱ በርካታ ርዕሠ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው መሆኑ ታውቋል። ከርዕሠ ጉዳዮቹ መካከል ስደትን እና ሰባዓዊ ቤተሰብን የሚመለከት እንደሚገኙበት ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ራሳቸውን ሕዝባዊ ነን የሚሉት ክፍሎች ሃይማኖትን ለጥቅማቸው ለማዋል ፈልገው ማኅበራዊ ግንኙነቶችን እና ሰብዓዊ ቤተሰብ ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ለማደናቀፍ መሞከራቸው ያሳዘናቸው መሆኑንም ብጹዕ ካርዲና አንቶኒዮ ታግለ ገልጸዋል። ዓለም አቀፍ ጉባኤውን በቅድስት መንበር የሃይማኖቶች የጋራ ውይይት አስተባባሪ ምክር ቤት ዋና ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክን በመወከል ብጹዕ አቡነ አንጦንዮስ ኩረር ተካፍለዋል።

ዘንድሮ ለተካሄደው የአንግሊካን ጳጳሳት ሕብረት ጉባኤ የተመረጠው መሪ ሃሳብ "የሐዋርያው ጴጥሮስ የመጀመሪያ መልዕክት እና መጪዎቹ አሥርት ዓመታት" የሚል መሆኑ ታውቋል። የላምቤት ኮንፌረንስ በመባል የሚታወቀው ጉባኤ በየአሥር ዓመታት የሚካሄድ ሲሆን የጉባኤው ሥፍራም የአንግሊካን ብጹዓን ጳጳሳት ኅብረት ዋና መቀመጫ በሚገኝበት በካንተርበሪ መሆኑ ታውቋል።

የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስን መልዕክት መሠረት ያደረጉት ካርዲናል አንቶንዮ ታግል፣ ሐዋርያው ለቤተ ክርስቲያን እና ለዛሬው ዓለም በላከው መልዕክት ላይ መሠረት በማድረግ ሃሳባቸውን ያካፈሉ መሆኑን አስረድተዋል። በዚህም መሠረት ብጹዕነታቸው፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ በመጀመሪያ መልዕክቱ 1:1 ላይ፥ በመጻተኝነት የምትኖሩ የእግዚአብሔር ምርጦች፤ በቁ. 2 እና 11 ላይ ፥ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመታዘዝ በደሙ የተረጫችሁና በመንፈስ አማካይነት የተቀደሳችሁት፣ በምዕ. 2:9 ላይ ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የተጠራችሁ ቅዱስ ሕዝብ፣ በምዕ. 2:4-5 በጻፈውም በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈሳዊ ቤት ውስጥ የተገነቡ ሕያዋን ድንጋዮች ያለውን በመጥቀስ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።  

እንደ ክርስቲያን ምላሽ መስጠት

ብፁዕ ካርዲናል አንቶንዮ ታግለ ከእነዚህ ጥቅሶች በተጨማሪ በመጀመሪያው የጴጥሮስ መልዕክት ምዕ. 2:22 ላይ፥ “እርሱ ኃጢአት አላደረገም፤ በአፉም ተንኰል አልተገኘበትም፣ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም።” የሚለውን፣ በምዕ. 3:8 ላይም ሁላችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፤ እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ፤ እንደ ወንድማማቾች ተዋደዱ፤ ርኅሩችና ትሑታን ሁኑ።” በም. 3:15 ላይ፥ እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያት ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁል ጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት።” የሚሉትን በመጥቀስ፣ እንዲሁም በምዕ. 1:3 ላይ፥ “ከታላቅ ምሕረቱ የተነሣ በኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሣት ምክንያት ለሕያው ተስፋ በሚሆን አዲስ ልደት” ያለውን እና በምዕ. 2:12 ላይ “ምንም እንኳ ክፉ እንደምትሠሩ አድርገው ቢያሟችሁም ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ መልካሙን ሥራችሁን ዓይተው እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ፣ በአሕዛብ መካከል በመልካም ሕይወት ኑሩ።” ያለውን በመጥቀስ፣ ለጥያቄዎች በሙሉ እንደ ክርስቲያን ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ሰብዓዊ ቤተሰብን ለመገንባት ያለው ህልም

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰብዓዊ ቤተሰብን እና ፍጥረታ ለመንከባከብ እና ለማሳደግ እንደሚመኙ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል አንቶንዮ ታግለ፣ ይህ ሕልም እና ምኞት ሊኖረን ይገባል ብለዋል። የመጀመሪያው የሐዋርያው ጴጥሮስ መልዕክት ከሁሉ አስቀድሞ ለክርስቲያኖች መጻፉን የገለጹት ብጹዕነታቸው፣ ለስደት የተዳረጉ ቤተሰቦችን አስታውሰው፣ "አንዳንድ ጊዜ በመንገዶቻችን እና በእቅዶቻችን ላይ ብቻ በመመራት እና ስለ ራስ ብቻ በማሰብ የመኖሪያ አካባቢዎች፣ የሕዝቦች እና የሃሳቦች ባለቤት እንሆናለን" ብለዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ “በተለያየ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ካሉ ህዝቦች ጋር ቀጣይነት ባለው ግንኙነት ውስጥ መንፈሳዊ ቤት የሆነች እና በጉዞ ላይ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን” በማለት መናገራቸውንም ብጹዕ ካርዲናል አንቶንዮ አስታውሰዋል።

ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች

ብጹዕነታቸው በዛሬው ዓለማችን የሚፈናቀሉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን በማስታወስ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በግዳጅ የሚሰደዱን፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ የሚሆኑትን፣ ለጭፍን ጥላቻ የሚዳረጉትን፣ ለጦርነት እና ለአካባቢ አደጋዎች የሚጋለጡትንም አስታውሰዋል። የስደተኞች ሕይወት በሚደርሱበት አገር ውስጥ እንደማይለወጥላቸው የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል አንቶንዮ ታግለ፣ ምክንያቱም እንግዶች እንደመሆናቸው መጠን ብዙውን ጊዜ መገለል እንደሚገጥማቸው እና በማኅበረሰቡ መካከል ለሚከሰቱት ችግሮች እና ክፋቶች ተጠያቂ ስለሚሆኑ ነው ብለዋል። በመሆኑም እንደ ቤተ ክርስቲያን እና እንደ ሰው፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቤት የሌላቸውን ሰዎች ችግር እንዴት ማቃለል ይገባል በማለት ጠይቀዋል። ዋናው ጥያቄ “ሌሎችን ወይም ከእኛ የተለዩትን እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል?” የሚል እንደሆነ እና "በጋራ መኖሪያ ምድራችን ግንባታ ላይ የብዝሃነትን ጥያቄ እንደገና መመልከት ያስፈልጋል ብለዋል።

በ "መንፈሳዊ ቤት" ላይ የተደቀኑ አደጋዎች

“በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሳይቀር የብሔር እና የባሕል ጉዳዮች መንፈሳዊ ቤትን በማበላሸት ላይ እንደሚገኙ በሐዘን ገልጸው፣ ለዘመናት በዘለቀው ቸልተኝነት፣ ብጥብጥ እና ጦርነት በተከሰቱ አሰቃቂ ትዝታዎች ምክንያት የጋራ ሰብዓዊ ቤተሰብን ማለም ለመጪው ትውልድ እንኳን አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል።

የሕዝባዊነት ወቅታዊ ፈተና

“ማኅበራዊ ግንኙነትን ለመገንባት ‘ሕዝባዊነት’ እየተባለ የሚጠራው ርዕዮተ ዓለም ወቅታዊ ፈተና መሆኑን ያብራሩት ካርዲናል አንቶንዮ ታግለ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በማለት ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው በቁ. 157 ላይ ሕዝባዊነት ማኅበራዊ ችግሮችን ለመተንተን የሚያስችል ዋና መንገድ አድርገው ስለሚቆጥሩት 'ሰዎች' የሚለውን ቃል ሕጋዊ ትርጉም ችላ ይሉታል” በማለት የተናገሩትን አስታውሰዋል።

ቀደም ሲል በተከፋፈለ ማኅበረሰብ ውስጥ ልዩነትን ማሳደግ

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲና ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ በንግግራቸው ማጠቃለያ፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎች "ሕዝባዊነት" ለሚለው ቃል በሚሰጡት የዕለት ተዕለት ትርጉም ተጽእኖ ማሳደራቸውን ገልጸው፣ በዚህም ምክንያት "ቃሉን ዋጋ በማሳጣት እና ቀደም ሲል በተከፋፈለው ማኅበረሰብ ውስጥ ተጨማሪ ልዩነቶችን በማሳደግ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል። ብጹዕነታቸው ከዚህ ጋር በማያያዝ ራሳቸውን ሕዝባዊ ነን የሚሉት ክፍሎች ሃይማኖትን ለጥቅማቸው ለማዋል ፈልገው ማኅበራዊ ግንኙነቶችን እና ሰብዓዊ ቤተሰብን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ለማደናቀፍ መሞከራቸው ያሳዘናቸው መሆኑንም ብጹዕ ካርዲና አንቶኒዮ ታግለ ገልጸዋል።

ዲጂታል ቴክኖሎጂ እና የትውልድ ዕድገት

በቤተሰብ ውስጥ ያለውን የትውልዶች "ልዩነት" ችላ ልንል አንችልም ያሉት ብጹዕ ካርዲናል አንቶንዮ ታግለ፣ ስለ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ሲናገሩ፣ በሰው ሠራሽ የማሰብ ችሎታ ዘመን፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካይነት የሰውን ማንነት፣ የሰውን ሥራ እና የሰውን ግንኙነት እንደገና የመቅረጽ ወይም የመግለጽ ዝንባሌ መኖሩን ገልጸው፣ የመጀመሪያው ተሐዋርያው ጴጥሮስ መልእክት፣ ክርስቲያኖች የመንፈሳዊ ቤት ሕያዋን ድንጋዮች እንድንሆን የሚያሳስብ መሆኑን አስረድተዋል።

የትህትና ምንጭ

ሰዎች በትሕትና አብረው እንዲጓዙ የጋበዙት ብጹዕ ካርዲናል አንቶንዮ ታግለ፣ ለግል ነፃነት ብቻ ሳይሆን ሰዎች በባሕሎቻቸውም የሚለያዩ መሆናቸውን አብራርተዋል። ባህልን ማወቅ ማለት የራስን ባሕል ከማወቅ በተጨማሪ ሌሎች ሰዎች በባሕሎቻቸው አማካይነት እንዴት ሰብዓዊነትን እንደሚገልጹ መረዳት እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል። በሂደቱ መካከል ሁሉም ሰው የበላይነት እና የባሕል ጭፍን ጥላቻን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የብዙ ባህሎች እውቀት ባይኖረንም በማናውቀው ባሕል ላይ አለመፍረድ ትህትናን ይጠይቃል" ብለዋል።

የሃይማኖት መሪዎች ሚና

ብጹዕ ካርዲናሉ አንቶንዮ ታግለ በማከልም የሃይማኖት መሪዎች ሌሎችን ባሕሎች የሚያደንቁት በማኅበረሰ ጥናት ችሎታ ብቻ ሳይሆን ግንዛቤን እንዲያዳብሩ ጠቁመው፣ “በባህሎች መካከል የሚደረግ የጋራ ጉዞ ፍርሃትን እንደሚቀንስ እና ባሕሎች እራሳቸውን እንዲያንጹ እና አንዳቸው ለሌላው መልካም ሆነው እንዲገኙ ያስችላቸዋል ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ የራሱ ባሕል ያለው ሰው እንደነበር ያስታወሱት ብጹዕነታቸው፣ ነገር ግን የአምላክን “ባሕል” ወደ ሰው ልጆች ባሕሎች ዘንድ ማምጣቱን አስታውሰዋል። “የተሰቀለው ከተማው ቅጥር ውጭ እንደነበር፣ ከቆሰለው ጎኑ ለእንግዶች እና ለስደተኞች የሚሆን መኖሪያ መወለዱን እና ሰውነቱም ቤተ ክርስቲያን እንድትሆን የሚፈልግ መሆኑን አስረድተዋል። በእርሱ ላይ እንደ ሕያው ድንጋይ በመሆን ደቀ መዛሙርቱ የተስፋ እና የደስታ ምክንያቶችን ያገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

08 August 2022, 16:34