ፈልግ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን  (AFP or licensors)

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ከሞስኮ በኩል የሚቀርብ የውይይት ፍላጎት እንደሚጠብቁ ገለጹ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ በአንድ የመጽሐፍ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት የሚቆምበትን መፍትሄ ለማግኘት ከሩሲያው ፕሬዚደንት ቪላድሚር ፑቲን ጋር ተገናኝተው ለመወያየት እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ኪሪል ጋር ላደረጉት የቪዲዮ ውይይት ከሞስኮ ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት በኩል ምላሽ የተሰጠ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሞስኮ ለመጓዝ ዝግጁ መሆናቸውን፣ ቅድስት መንበርም በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲቆም የምትችለውን ሁሉ እንደምታደርግ፣ ነገር ግን ይህን ምኞቷን ለማሳካት ከሞስኮ በኩል የሚቀርብ በጎ ምላሽ የምትጠብቅ መሆኗን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ገልጸዋል። በመጽሐፉ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን መልስ የሰጡ ሲሆን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ኮሪዬረ ዴላ ሴራ” ከተሰኝ የጣሊያን ዕለታዊ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡበትም ተጠይቀዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፣ እንደማስበው፣ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሞስኮ ተጉዘው ከፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመገናኘት ፈቃደኛ መሆናቸውን ከመግለጽ የበለጠ ሌላ እርምጃ የለም” በማለት ካስረዱ በኋላ ከሞስኮ በኩል የሚሰጥ ምላሽ እንደሚጠባበቁ ገልጸው፣ “ቅዱስነታቸው ከዚህ በላይ ተጨማሪ እርምጃ መውሰድ አለባቸው ብዬ አላምንም” ብለዋል። ከሁለት ወራት በላይ በዩክሬን ላይ ሲሰነዘር የቆየ የጦር መሣሪያ ጥቃት ለማስቆም የሚያግዝ ገንቢ የውይይት ሂደት ለመጀመር በሩ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጣሊያኑ ዕለታዊ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ለውይይት ዕድል እንደሚሰጡ ተስፋን በማድረግ ቅድስት መንበር ለክሬምሊን የላኩትን ደብዳቤ አስታውሰዋል።

መጋቢት 7/2014 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቪዲዮ ጥሪ አማካይነት ውይይት ባደረጉበት ወቅት  የሞስኮ ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ኪርል "በተሳሳተ የድምጽ ቃና" መልዕክት ሲለዋወጡ የሚገልጽ የምስል ማስታወሻ መመዝገቡ ይታወሳል።  ይሁን እንጂ ከዚህም ባሻገር በጦርነት የተጎዳውን ዓለም አቀፍ ሚዛን መልሶ ለመገንባት ፍላጎቱ አሁንም እንዳለ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቀናት በፊት መናገራቸው እና "ዓለም ሰላምን እንደምትፈልግ እና ሰላምን መተንፈስ ሰላምታን መለዋወጥ ነው" ብለው፣ ውሎ አድሮ የወንድማማችነት ጥንካሬ ሊሰፍን እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

05 May 2022, 17:41